1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የሶስትዮሽ ስብሰባ በአዲስ አበባ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 29 2010

ከህዳሴ ግድብ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የሚመለከተው የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የሶስትዮሽ ብሔራዊ ኮሚቴ ከትናንት በስቲያ ሚያዝያ 27 ስብሰባውን በአዲስ አበባ አካሄዷል፡፡ ሶስቱ ሀገራት ግድቡ የሚያስከትለውን ተጽእኖ እንዲያጠና የሰየሙት አማካሪ ድርጅት ባቀረበው የመነሻ ሪፖርት ላይ ለመወያየት አቅደው የነበረ ቢሆንም ለቀጣይ ስብሰባ ገፍተውታል፡፡

https://p.dw.com/p/2xKCL
Äthiopien Grand Renaissance Staudamm
ምስል Reuters/T. Negeri

ሶስቱ ሀገራት አስተያየታቸውን እንዲያዋህዱ ሀሳብ ቀርቧል

ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን በአባይ ግድብ ላይ የጀመሩትን ውይይት አሁንም አንድ መቋጫ ሊያበጁለት አልቻሉም፡፡ በባለሙያዎች ደረጃ በመካሄድ ላይ ያለው ውይይት አንድ ሁለት እያለ 19ኛ ላይ ቢደርስም ግድቡ በሚያስከትለው ተጽዕኖ ላይ ወደሚደረገው ዋና ውይይት እንኳ አልተዘለቀም፡፡ ግድቡ የሚያስከትላቸውን ተጽዕኖዎች እንዲያጠና የተመረጠው የፈረንሳይ አማካሪ ተቋምም እስካሁን በይፋ ያቀረበው የመነሻ ሪፖርት ብቻ ነው፡፡ 

አርቲላ እና ቢ አር ኤል የተባሉ ድርጅቶች ጥምረት የሆነው የፈረንሳዩ አማካሪ ተቋም ያዘጋጀውን የመነሻ ሪፖርት ለሶስቱ ሀገራት ካስረከበ ቆየት ቢልም ከሶስቱ ሀገራት የሚሰጠውን ዝርዝር ግብረ መልስ ለመቀበል ገና እየተጠባበቀ ነው፡፡ ባለፈው ቅዳሜ ሚያዝያ 27 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተሰባሰቡት የሶስቱ ሀገራት የባለሙያዎች ኮሚቴ አባላት በሪፖርቱ ላይ ያላቸውን አስተያየት ለማቅረብ ቀጠሮ ይዘው ነበር፡፡ የፈረንሳዩ አማካሪ ድርጅት በስብሰባው ላይ ቢሳተፍም ሶስቱ ሀገራት ግን በሪፖርቱ ላይ ያላቸውን የልዩነት ሀሳብም ሆነ እንዴት መሻሻል አለበት የሚሉትን ዝርዝሮች ለአማካሪው ድርጅት ሳያቀርቡ ቀርተዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የሶስትዮሽ ብሔራዊ ኮሚቴ ውስጥ የኢትዮጵያን የባለሙያዎች ቡድን በሊቀመንበርነት የሚመሩት ኢንጂነር ጌዲዮን አስፋው “የአንድ ቀን ስብሰባ ስለነበር የቀረቡትን ሀሳቦች በሙሉ ማየት አልተቻለም” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ በሱዳን በኩል የቀረበው ሀሳብ ተቀባይነት በማግኘቱ ጉዳዩ በቀጣይ ቀጠሮ በይደር እንዲታይ መገፋቱን ያስረዳሉ፡፡

“በእዚህ የመነሻ ሪፖርቱ ላይ ያለመስማማት ላይ በመድረሳችን መነሻ ሪፖርቱ እንዲስተካከል በየሀገሩ ሀሳብ ቀርቦ ነበር፡፡ ያንን አንድ ላይ አዋህዶ ለመላክ ሀሳቦቻችን የተለያዩ ስለነበሩ በዚህ ስብሰባ ላይ አልተቻለም፡፡ ሱዳን ያቀረበው ሀሳብ በመነሻ ሪፖርቱ (inception report) ላይ ሀሳቦቻችንን አንድ አድርጎ ለመሄድ የሚረዳ ነው፡፡ እንግዲህ በሚቀጥለው ስብሰባችን ላይ እናያዋለን ብለናል” ብለዋል። 

ሱዳን ያቀረበችው የተዋሃደ ሪፖርት የማቅረቡ ጉዳይ የቴክኒክ ባለሙያዎች እና የየሀገራቱ የውሃ እና መስኖ ሚኒስትሮች በሚገኙበት በመጪው ግንቦት 6 እንደገና እንደሚታይ አቶ ጌዲዮን ይናገራሉ፡፡ በኢትዮጵያ በኩል በአማካሪ ድርጅቱ የመነሻ ሪፖርት ላይ የሚቀርበው ተቃውሞ ምን እንደሆነ ለተጠየቁት ደግሞ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

Infografik Karte Grand Ethiopian Renaissance Dam ENG

“ከፈረምነው የኮንትራት ውል ውጭ ያስገባቸው ስራዎች ስላሉ፣ የተዋቸው ስራዎች ስላሉ በእኛ በኩል በተፈረመው ኮንትራት መሰረት አስተካክል ነው [የምንለው]፡፡ እና በተሰጠው terms of reference መሰረት የሚስተካከሉ ነገሮች አሉ፡፡ ሳይስተካከሉ ቢሄዱ ጥናቱ ጥሩ ውጤት አይኖረውም ከማለት አኳያ ነው፡፡ እንግዲህ ጥናቱ የህዳሴ ግድብ በታችኞቹ ሀገራት ላይ ያለውን ተጽእኖ ነው የሚያጠናው፡፡ ይህን ተጽዕኖ ሲያጠና የተጽዕኖዎቹ መለኪያ የ1959ቱ በሱዳን እና በግብጽ ያለው ስምምነት መሆን የለበትም ነው፡፡ እኛ አማራጭ ሀሳቦች እያቀረብን በእነዚያ የመፍትሄ ሀሳቦች ላይ ተመስርተን እንስራ ነው [የምንለው]፡፡ ተጽዕኖዎቹን ከምን አኳያ መለካት አለበት የሚለውንም እየተወያየን ነው” ይላሉ አቶ ጌዲዮን፡፡    

የፈረንሳዩ አማካሪ ድርጅት በሶስቱ ሀገራቱ መካከል ያለውን የውሃ አጠቃቀም ለመፈረጅ በመነሻነት የተጠቀመው በጎርጎሮሳዊው 1959 በግብጽ እና ሱዳን መካከል የተደረገው ውል መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ይህን አካሄድ ኢትዮጵያ አትስማማበትም ይላሉ አቶ ጊዲዮን፡፡  በአባይ ግድብ ላይ እየተካሄደ ያለውን ውይይት ወደፊት አላራምድ ካሉ ጉዳዮች ውስጥ ቁልፉ ይኸው የውሃ አጠቃቀም እና የቆየ የሁለቱ ሀገራት ውል እንደሆነም ያብራራሉ፡፡

“ኢትዮጵያ አባል ባልሆነችበት፣ ውለታ ባልፈረመችበት ጉዳይ ውስጥ ከዚያ ተነስቶ ተጽዕኖ እለካለሁ የሚለው አንደኛው እና ዋነኛው ነው፡፡ እና ብዙውን ጊዜ ክርክሩ የሚደረግበት፤ ሁሉም ሀገር ከጥቅሙ አንጻር ዳታዎችን ስለሚያቀርብ፤ በአንዴ ስምምነት ሊደረስ አይችልም፡፡ የእዚህ ወሰን-አለፍ ወንዞች ጉዳይ ምንጊዜም ቢሆን አከራካሪ ነው፡፡ እኛ አሁን በዓለም ህግም ቢሆን በሀገሪቱ አቅድም መሰረት ውሃን ጨምሮ በሀገሪቱ ክልል ውስጥ ባሉ ተፈጥሮአዊ ሀብቶች የመጠቀም መብት አለን ነው፡፡ ስንጠቀም ግን ጉልህ ተጽዕኖ አናደርስም ነው፡፡ እኛ ጥናቱ ይምጣና ‘ተጽዕኖው ጉልህ ነው፣ አይደለም የሚለውን እንይ ነው’ የምንለው፡፡ ያኔ ውይይት ሊደረግ ይችላል፡፡ ምናልባት በግብጽ በኩል ‘ውሃችን አንድ ጠብታ አይነካም’ እንደዚህ የሚል ዛቻ አለ፡፡ እኛ ያንን ተከትሎ ለመሄድ ስምምነት ላይ መድረስ አልቻልንም፡፡ በሚቀጥለው ስብሰባ ላይ ጥናቱ እንዲካሄድ ሙከራ እናደርጋለን፡፡” 

በቅዳሜው የአዲስ አበባ ስብሰባ ከባለሙያዎች ሌላ የሶስቱም ሀገራት የውሃ እና መስኖ ሚኒስትሮች ተገኝተው ነበር፡፡  

ተስፋለም ወልደየስ 

ኂሩት መለሰ