1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያ ጦር የመቀሌ ከተማን እንደተቆጣጠረ ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ

ቅዳሜ፣ ኅዳር 19 2013

ጠቅላይ ምኒስትሩ ዛሬ ማምሻውን በይፋዊ የፌስቡክ ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት "ንጹሐን ዜጎች ዒላማ ሳይሆኑ፣ ከተሞቻችንና ቅርሶቻችን ሳይጎዱ መቀሌ ለመግባት ተችሏል" ብለዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጦሩ "የሰሜን ዕዝን ቢሮ ተቆጣጥሯል፤ የተዘረፉትን መሣሪያዎች እና ቁሳቁሶች እጁ አስገብቷል።" ማለቱን ብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ ዘግቧል።

https://p.dw.com/p/3lxoK
Äthiopien Tigray | Hauptstadt Mekele
ምስል MICHAEL TEWELDE/AFP/Getty Images

የኢትዮጵያ ጦር የመቀሌ ከተማን እንደተቆጣጠረ ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ። ጠቅላይ ምኒስትሩ ዛሬ ማምሻውን በይፋዊ የፌስቡክ ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት "ንጹሐን ዜጎች ዒላማ ሳይሆኑ፣ ከተሞቻችንና ቅርሶቻችን ሳይጎዱ መቀሌ ለመግባት ተችሏል" ብለዋል።

"የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል ብርሀኑ ጁላ ጀግናው ሠራዊታችን መቀሌን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩን አረጋገጡ" የሚል ጽሁፍ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ አስፍሯል።

በመንግሥት የሚተዳደረው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን "ዛሬ [ሕዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም] ከሰዓት በኋላ እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት ባደረገው የተቀናጀ ማጥቃት ከተማዋን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሯል" ሲል ዘግቧል።

ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የደረሰውን መረጃ ዋቢ በማድረግ ብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ "ሠራዊታችን በአሁኑ ሰዓት ጁንታው የተደበቀባቸውን የተጠረጠሩ ቦታዎች በማሰስ እና በመፈተሽ ላይ ይገኛል" የሚል ዘገባ አቅርቧል።

በዘገባው መሠረት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት "የሰሜን ዕዝን ቢሮ ተቆጣጥሯል፤ የተዘረፉትን መሣሪያዎች እና ቁሳቁሶች እጁ አስገብቷል።"

የኢትዮጵያ መንግሥት፦ ህወሓት፣ የክልሉ ልዩ ኃይል እና ሚሊሺያ እጃቸውን እንዲሰጡ የሰጠው የ72 ሰዓታት ቀነ ገደብ ካበቃ በኋላ የኢትዮጵያ ጦር "የሕግ ማስከበር ዘመቻውን" ከትናንት በስቲያ እንደጀመረ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሕብረት ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ሐሰን ኢብራሒም በትናንትናው ዕለት በሰጡት መግለጫ ተናግረው ነበር።

የኢትዮጵያ ጦር የትግራይ ዋና ከተማን መቆጣጠሩን በገለጹበት ጽሁፍ ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ "የመከላከያ ሠራዊት በድል በገሠገሠባቸው የትግራይ አካባቢዎች ሁሉ የትግራይ ሕዝብ ለሀገሩ ያለውን ፍቅርና ለመከላከያ ሠራዊቱ ያለውን ክብር አሳይቷል። ጁንታው ካስታጠቃቸው ጥቂት የክፋት ኃይሎች ውጭ ያለው የትግራይ ሕዝብ መቀሌ እስኪገባ ድረስ ለመከላከያ ሠራዊቱ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ሁሉ አድርጓል። ይህም የሠራዊቱን ድልና የጁንታውን ሽንፈት አፋጥኖታል።" ብለዋል።

ቀደም ብሎ የመቀሌ ከተማ በከባድ መሳሪያ መደብደቧን የትግራይ ክልላዊ መንግሥት አስታወቆ ነበር። የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ከተራድዖ ድርጅቶች የመረጃ ምንጮች በእርግጥም ድብደባው መፈጸሙን እንዳረጋገጠ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ጦር "የመቀሌን ማዕከላዊ አካባቢ በከባድ መሳሪያ መደብደብ ጀምሯል" የሚል መግለጫ መቀመጫውን አሜሪካ ባደረገው ትግራይ ሚዲያ ሐውስ በኩል በፌድራል መንግሥቱ እውቅና የተነፈገው የክልሉ መንግሥት አውጥቷል።

የትግራይ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው መቀሌ "ከባድ ድብደባ" ውስጥ ተገኛለች ሲሉ በአጭር የጽሁፍ መልዕክት እንዳረጋገጡለት ሬውተርስ ዘግቧል።

ከከተማው ነዋሪዎች ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው ሁለት ዲፕሎማቶችም ይኸንንው እንዳረጋገጡለት ሬውተርስ ዘግቧል። ሬውተርስ እንዳለው ከሁለቱ ዲፕሎማቶች አንዱ ሐምዳይ በተባለ አካባቢ ከባድ የፍንዳታ ድምጽ መሰማቱን ተናግረዋል። የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት በበኩሉ ጉዳዩን በከተማዋ ከሚገኙ ሁለት የተራድዖ ድርጅቶች ሠራተኞች ማረጋገጡን አስታውቋል። 

በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ስዩም የኢትዮጵያ ጦር ሰላማዊ ሰዎች የሚኖሩባቸውን አካባቢዎች አይደበድብም ሲሉ ለሬውተርስ ተናግረዋል። ቢልለኔ "በትግራይ እና በመቀሌ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ደሕንነት የፌድራል መንግሥቱ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው" ብለዋል።