1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮ-ጀርመን የባህልና የስፖርት ፌስቲቫል በዳርምሽታት

ቅዳሜ፣ ግንቦት 24 2011

የኢትዮ ጀርመን የስፖርት እና የባሕል ፌስቲቫል በዳርምሽታት ከተማ በመካሔድ ላይ ይገኛል። ፌስቲቫሉን ያዘጋጀው የኢትዮ-ዳርምሽታት ወዳጆች ማኅበር ሲሆን ለሁለት ቀናት ይቆያል። ከተለያዩ የጀርመን ከተሞች የተውጣጡ 12 ክለቦች ይሳተፉበታል።

https://p.dw.com/p/3JbMp
Ähiopisch-deutsches Sportfestival in Darmstadt
ምስል DW/E. Fekade

የኢትዮ-ጀርመን የባህልና የስፖርት ፌስቲቫል

የዘንድሮውን የኢትዮ-ጀርመን የስፖርትና የባህል ፌስቲቫል ያዘጋጀው የኢትዮ ዳርምሽታት ወዳጆች ማህበር ሲሆን ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚሁ መርሐ-ግብር ለመሳተፍ ከመላው ጀርመን የተውጣጡ 12 የስፖርት ክለቦችና ደጋፊዎቻቸው እንዲሁም ከአጎራባች የአውሮፓ አገራት የመጡ ኢትዮጵያውያን ዳርምሽታት ከተማ ጌህሜርቬግ አካባቢ በሚገኘው የስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከል /ስታዲየም/ ተሰባስበው በዝግጅቱ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ:: ይኸው የኢትዮጵያውያን ዓመታዊ ፌስቲቫል የሚካሄድበት ቦታ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የተዋበ ሲሆን በልዩልዩ ብሔረሰቦችና በአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለማት የተሸለሙ አልባሳትን የለበሱ ኢትዮጵያውያንም ለስፖርት ማዕከሉ ልዩ ድምቀትን ሰጥተውታል:: ከዚህ ሌላ በየዝግጅቱ ጣልቃ የሚሰሙት ባህላዊ ሙዚቃዎች እና የየክለባቱ ደጋፊዎች ሆታና ጭፈራም ለፕሮግራሙ ልዩ ድባብን እና አስደሳች ገጽታን ፈጥረውለታል::
 
የዘንድሮውን የኢትዮ-ጀርመን የስፖርትና የባህል ፌስቲቫል አገራችን በለውጥ ጎዳና ላይ በምትገኝበት እንዲሁም በዘርና በፖለቲካ ምክንያት ለበርካታ ዓመታት ተከፋፍሎ የቆየው ሕዝባችን በአንድነት እና በጋራ ተሰባስቦ አገሩን እና ሕዝቡን እያሰበ የሚያከብረው ዝግጅት በመሆኑ ከፍተኛ ደስተኛ እንደተሰማቸው የመርሐ-ግብሩ አስተባባሪዎች የኢትዮ ዳርምሽታት ወዳጆች ማህበር አመራሮች ገልጸዋል:: ይህ ዓይነቱ ዝግጅት በውጭው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ልዩነታቸውን አስወግደው አገራዊ አንድነታቸውን ብሎም አብሮ ተረዳድቶ የመኖር በጎ ልማዳቸውን እንዲያጠናክሩ ዘመን ተሻጋሪ ባህላዊ ዕሴቶቻቸውን እንዲጠብቁ እንዲሁም የሚኖሩበትን ሃገር ሕግ እና ሥርዓት አክብረው እንዲኖሩ ከማድረጉም ሌላ ከደባል ሱሶች ርቀው በስፖርታዊ ጨዋነት እንዲታነጹም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው ብለዋል ታዳሚዎቹ:: ለረጅም ዘመን በስራ እና በቦታ እርቀት የተለያዩ ወዳጆችን በማቀራረብ ልዩ ተሰጥዖ ያላቸውንም ኢትዮጵያውያን በማበረታታትና የደከም አዕምሮንም በማነቃቃት በኩልም እንዲህ ዓይነቱ ሁሉን አሳታፊ ዝግጅት ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው የገለጹልንም ነበሩ:: በተለይም በውጭው ዓለም ለሚወለዱ ሕጻናት አገራዊ ፍቅር እንዲኖራቸው በማንነታቸው እንዲኮሩና ታሪክ ቋንቋና ባህላቸውን ጠንቅቀው እንዲገነዘቡ በማድረግ ረገድም ቢሆን ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው የፌስቲቫሉ ታዳሚዎች ያስረዳሉ::

Ähiopisch-deutsches Sportfestival in Darmstadt
ምስል DW/E. Fekade

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ የተንሰራፋው ድህነት የህክምና አገልግሎት እጥረት ደረጃና ጥራቱን የጠበቀ የትምህርት አሰጣጥ ችግር ንፁህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትና እንደ መንገድ ያሉ የመሰረተ ልማቶች በተገቢው መልኩ አለመስፋፋት አገሪቱ ካላት አኩሪ ታሪክ ጋር አብረው የማይሄዱና የማይጣጣሙ መሆናቸውን በማውሳት በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችና ታዳጊዎች ለአገራቸውና ለወገናቸው እንዳያስቡ በቅርቡ በድጋሚ ጥሪ አቅርበው ነበር:: በዳርምሽታቱ የኢትዮ-ጀርመን የባህልና የስፖርት ፌስቲቫል የታደሙ ኢትዮጵያውያንም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አገራዊ ጥሪ በጎ ምላሽ ለመስጠት ቁርጠኛ መሆናቸውን ነው የገለፁልን:: በዛሬው የዳርምሽታቱ የኢትዮ-ጀርመን የስፖርትና የባህል ፌስቲቫል የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ከመላው ጀርመን የመጡ 12 የእግርኳስ ክለባት የማጣሪያ ውድድር ያደረጉ ሲሆን ማምሻውን አሸናፊዎቹ ተለይተው በነገው ዕለት የዋንጫ ውድድር እንደሚያካሂዱ ታውቋል:: ከዚህ ሌላ ግጥሞችና ልዩልዩ ሥነ ጽሁፎችን ጨምሮ የሕጻናት ስፖርታዊ ውድድሮችና ሌሎችም ዝግጅቶች በነገው የማጠቃለያ መርሐ-ግብር እንደሚቀርቡ አስተባባሪዎቹ ይፋ አድርገዋል:: ይህ በእንዲህ እንዳለ በአውሮፓ ደረጃ የዘንድሮው 17ተኛው የኢትዮጵያውያን የስፖርት እና የባሕል ፌስቲቫል በስዊዘርላንድ ዙሪክ ከተማ በመጪው ወር መጨረሻ ከጁላይ 31 እስከ ኦገስት 3, 2019 ዓ.ም በድምቀት ለማካሄድ ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ከአውሮፓ የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን መረጃ ለማወቅ ችለናል :: 

እንዳልካቸው ፈቃደ

እሸቴ በቀለ