የኢንፎርሜሽን እና ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ኤክስፖ

አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:34 ደቂቃ
04.07.2018

የኢንፎርሜሽንና ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ኤክስፖ

በኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን እና ኮሚዩኒሽን ቴክኖሎጂ ዓውደ ርዕይ ለዘጠኝ ጊዜያት ያህል ተካሂዷል። በባዛር እና ዓውደ ርዕይ ደረጃ ሲደረግ የቆየው ይህ ዓመታዊ ሁነት ካለፈው ዓመት ጀምሮ ወደ ዓለም አቀፍ ኤክስፖ ከፍ ብሏል። ላለፉት አራት ቀናት ለጎብኚዎች ክፍት የነበረው እና ዛሬ የተጠናቀቀው የዘንድሮው ኤክስፖ ምን የተለየ ነገር ነበረው?

እንደተጠበቀው ሶፊያ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ለመጀመሪያ ጊዜ ህዝብ ፊት ስትቀርብ አማርኛ መናገር አልቻለችም። ከአንድ ቀን በኋላ ግን ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ስትገናን በኮልታፋ አንደበትም ቢሆን አማርኛ ቋንቋ ሞካክራለች። 

የሳዑዲ አረቢያ ዜግነት የተሰጣት ሮቦቷ ሶፊያ የሰው ሰራሽ አስተውሎት (artificial intelligence) የደረሰበትን የምጥቀት ደረጃ ከሚያሳዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች አንዷ ተደርጋ ትወሰዳለች። ሮቦቷ ሶፊያ የዚህ ዓመቱ የኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን እና ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ (ICT) ኤክስፖም ዋና መስህብ ሆናለች። 

መነሻውን ከሆንግ ኮንግ ባደረገው ሀንሰን ሮቦቲክስ በተሰኘው ኩባንያ የተሰራችው ሶፊያ የኢትዮጵያውያን የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች አሻራ ያረፈባት ናት። ለዚህም ይመስላል የአሲቲ ኤክስፖው በርካታ ጎብኚዎችን ቀልብ የገዛችው። ባህላዊ ቀሚስ እንድትለብስ ከተደረገችው ከዚህች ታሪካዊ ሮቦት ጋር ብዙዎች ፎቶ ሲነሱ ታይተዋል። በተለይ የወጣቶች እና የአዳጊዎች ጉጉት ያየለ ነበር።

 ሶፊያ የኤክስፖውን ዋና ትኩረት ብትቆጣጠርም ለዕይታ የበቁ ሀገርኛ የቴክኖሎጂ ውጤቶችም በርካታ ጎብኚዎችን አስደምመዋል። የሞባይል መተግበሪያዎች (አፕልኬሽኖች) ሰሪ የሆነው ተመስገን ፍስሀ ባለፈው ቅዳሜ ሰኔ 23 በተከፈተው እና ዛሬ የተጠናቀቀውን ኤክስፖ ከዳር እስከ ዳር ተመልክቷል። ስራዎቻቸውን ይዘው በኢግዚቢሽኑ ላይ ለተሳተፉ የሙያ አጋሮቹም በቦታው በመገኘት እገዛ ሲያደርግ ቆይቷል። በተመልካቾች ዘንድ ይበልጥ መነጋገሪያ ስለሆኑት ኢትዮጵያ ውስጥ ስለተሰሩት አዳዲስ አፕልኬሽኖች ይናገራል። 

እነዚህን አፕልኬሽኖች የሰሩትን ጀማሪ ድርጅቶች (startups) በተለያየ መልኩ የሚያግዙ ኩባንያዎች በዘንድሮው ኤክስፖ ጎላ ያለ ስፍራ እንደተሰጣቸው ተመስገን አስተውሏል። የዛሬ ሰባት ዓመት “አይስ አዲስ” በተሰኘው ድርጅት ፋና ወጊነት በኢትዮጵያ እግሩን የተከለው ጀማሪ ድርጅቶችን የማገዣ ማዕከል (incubation center) ዛሬ ቁጥሩ አድጎ አምስት ደርሷል። በዘንድሮው ኤክስፖ ታዲያ አምስቱን ማዕከላት የመሰረቱት ሁሉም ኩባንያዎች ተሳታፊ ነበሩ። ተመስገን ስለኩባንያዎቹ፣ ስለማዕከላቱ እና ስለሚያቀርቡት እገዛ ያብራራል። 

ኢትዮጵያ በኢንፎርሜሽን ኮሚዩኔኬሽን ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም ያሳየው ይህ ኤክስፖ የተዘጋጀው ጉዳዩ በቀጥታ በሚመለከተው የመንግስት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ነው። የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዲህ አይነቱን ዝግጅት በኤክስፖ ደረጃ ሲያዘጋጅ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ዝግጅቱ ባለፈው ዓመት ወደ ዓለም አቀፍ ኤክስፖ ደረጃ ከማደጉ በፊት በባዛር እና ዓውደ ርዕይ ደረጃ ለዘጠኝ ጊዜያት ያህል ተካሂዷል። በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከተሰናዱ ተመሳሳይ ዝግጅቶች ሶስቱን የታደመው ተመስገን የቀደምቶቹን ከአሁኖቹ ጋር ያነጻጽራል።

እንደ ተመስገን ሁሉ ሶፍትዌሮችን እና የሞባይል አፕልኬሽኖችን የሚሰራው ሀብታሙ ፍቃዲም የኢንፎርሜሽን እና ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ማስተዋወቂያ ዝግጅቱ ወደ ኤክስፖ ደረጃ ከፍ ካለ በኋላ “ለውጦች አሉ” በሚለው ይስማማል። ለውጦቹን እንደሚከተለው ይዘረዝራቸዋል።  

የዘንድሮው ኤክስፖ ካለፈው ዓመት በበለጠ ጎብኚ አስተናግዷል ብሎ የሚያምነው ተመስገን ለዚህም ሮቦቷ ሶፊያን በዋና ምክንያትነት ያነሳል። “ብዙ ሰው እርሷን ለማየት ይመጣ ነበር” ይላል። ከዚህ ቀደም ያልነበሩ አዳዲስ ተሳታፊ ድርጅቶችን መመልከቱን የሚናገረው ተመስገን ኤክስፖው በዚህ ዓመት “ይበልጥ ተሻሻሏል” ባይ ነው። ሀብታሙ ግን ይህን ይቃረናል። ኤክስፖው ከአምናው ጋር ሲነጻጸር “የተቀዛቀዘ ነበር” ይላል። በዝግጅት ረገድም ጉድለቶች እንደተስተዋሉበት ይናገራል። 

ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ 


 

ተዛማጅ ዘገባዎች