1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢድ አል አድኻ አከባበር

ሐሙስ፣ መስከረም 13 2008

የኢድ አል አድሐ (አረፋ) በዓል ዛሬ በመላዉ ዓለም ሙስሊሞች ዘንድ በመንፈሳዊ ሥርዓት ተከብሮ ዋለ።ከሁለቱ የሙስሊሞች ትላልቅ በዓላት አንዱ የሆነዉ የኢድ ዓል-አድሐ በዓል ዘንድሮ ሲከበር ለ1436ኛ ጊዜ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1GdC7
ምስል DW/G. Tedla

[No title]

በዓሉ ኢትዮጵያ ዉስጥም በድምቀት ተከብሯል ። በተለይ በአዲስ አበባ ስታድዮም በርካታ ሙስሊሞች በተገኙበት በጋራ ፀሎትና ስግደት ነው የተከበረው ። ከፀሎትና ስግደት በኋላም የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት እንዲሁም የአዲስ አበባ ከንቲባ ለበዓሉ ታዳሚዎች ንግግር አድርገዋል ። ዘንድሮ በአዲስ አበባ ስታድዮም የተገኘው ሙስሊም ቁጥር ከበፊቶቹ ዓመታት ጋር ሲነፃፀር ያነሰ እንደሆነ የአዲስ አበባው ወኪላችን ጌታቸው ተድላ ኃይለ ጊዮርጊስ ዘግቧል ።የኢድ አልአድሃ በዓል የእርድ በዓል ነው ። አቅሙ ያለው ለበዓሉ በግ ወይም ከብት አርዶ ከድሆች ጋር ተካፍሎ መብላት ይጠበቅበታል ። በየቤቱ አቅም እንደፈቀደ ምግብ አዘጋጅቶ ከዘመድ ወዳጅ ከጎረቤት ጋር መብላት መጠጣትም በዚህ በዓል የተለመደ ነው ። የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው ሙስሊሞች በዓሉን ያከበሩት ድሆችንም በመርዳት ጭምር መሆኑን ተናግረዋል ። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ምዕመናን በየዓመቱ የሃጂ ጉዞ በሚያደርጉባት በሳውዲ አረቢያ ዛሬ የደረሰው የሞት አደጋ በበዓሉ ላይ ጥላ አጥልቷል ። መካ አቅራቢያ በምትገኘው በሚና ከተማ በተፈጠረ መጨናነቅ ና ግፍያ ከ700 በላይ ሰዎች መሞታቸውን መንግስት አስታውቋል።

Saudi-Arabien Hadsch Massenpanik in Mina
ምስል picture-alliance/AP Photo

በአደጋው ከ800 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውም ተነግሯል ። የሳውዲ መንግሥት እስካሁን የሟቾቹን ዜግነት አላሳወቀም ። ኢራን ግን 41 ዜጎቿ በአደጋው መሞታቸውን አስታውቃለች ።በሙስሊሞቹ ቅዱስ ሥፍራ መካሕና እና አካባቢዉ ሕይወት ያጠፋ አደጋ ሲደርስ ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ዉስጥ የዛሬዉ ሁለተኛዉ ነዉ።ከአስራ-ሁለት ቀን በፊት በታላቁ የመካሕ መስጂድ ላይ የግንባታ ክሬን ወድቆ ከአንድ መቶ አስር በላይ ሰዎች ሞተዋል።በርካቶች ቆስለዋል።ለዘንድሮዉ ሐጂ 2 ሚሊዮን ያሕል ምዕመን ለዚያራ ተጉዟል።ሳውዲ አረቢያ ስለ በዓሉ ድባብና ስለ ደረሰው አደጋ መጠን ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክን አነጋግረናል ። በርካታ ኢትዮጵያውያን በሚገኙበት በዋሽንግተን ኢድ አል አድሃ እንዴት እንደሚከበር መክብብ ሸዋ ዘገባ አለው ።

ጌታቸው ተድላ ኃይለ ጊዮርጊስ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

ነበዩ ሲራክ

መክብብ ሸዋ

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ