1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢድ አል ፈጥር በዓል በጀርመን

ሰኞ፣ ሐምሌ 21 2006

አብዱረዛቅ ሙደሲር በቦንና ኮለን መካከል በምትገኘው ብሩህል ይኖራል። በጀርመን አስራ ሁለት ዓመታትን ለኖረው አብዱረዛቅ የዘንድሮው ረመዳን እንደወትሮው አይደለም። በአውሮጳ የሚታየው የበጋ ረጅም ቀን እንደ አብዱረዛቅ ረመዳንን ለሚጾሙ ፈታኝ ጊዜ ነው።

https://p.dw.com/p/1Ckrq
Deutschland Eid al-Fitr Fest Zuckerfest Mahnzeit
ምስል picture-alliance/dpa

«ጾሙ ከሌላው ጊዜ ትንሽ የበለጠ ይከብድ ነበር። በቀን ወደ አስራ ዘጠኝ ሰዓት ነበር የምንጾመው።ከኢትዮጵያ አንጻር ወይም እዚህ ጀርመን አገር ውስጥ ክረምት ወቅት ከለመድንው በጣም ይረዝማል።» ይላል አብዱረዛቅ። እንደ አብዱረዛቅ ሁሉ በቦን በትልቅነቱ በሚታወቀው መስጊድ የኢድ ሶላት ለተሳተፈው መሃመድም የዘንድሮው ረመዳን ልዩነት አለው።
«ለሊቱ አጭር ስለሆነ ከኢፍጣር በኋላ ከጓደኛ ጋር መገናኘት አይቻልም። ሁለተኛ ነገር ደግሞ የሚሰሩ ሰዎች ድካም አለ።» ረመዳን በእስልምና ተከታዮች ዘንድ ጥልቅ መንፈሳዊ ትርጓሜ አለው። ጾሙ ጸሐይ ወጥታ እስክትገባ ከምግብና መጠጥ መቆጠብ ከወሲባዊ ግንኙነት በመታቀብ ብቻ የሚወሰን አይደለም። ረመዳን ከክፉ ነገር በመታቀብ፤ መልካም ነገር በመፈጸምና የተቸገሩ ሰዎችን በመርዳት ከፍ ያለ ዋጋ የሚሸመትበት ጊዜ ነው።
ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ተሰባስበው በቦንና አካባቢው የሚኖሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች ረመዳንን በጥንካሬ በመጾም ሃይማኖታዊ ግዴታቸውን በመወጣት የኢድ አልፈጢር በዓልን በጋራ አክብረዋል። በቦን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም የዚህ በዓል ተሳታፊ ነበሩ። ኢትዮጵያውያኑ ከኢድ ሶላት በኋላ ደግሞ በጋራ ሰብሰብ ብለው በዓሉን ያከብራሉ። እነ አብዱረዛቅ 1435ኛውን የኢድ አልፈጥር በዓል ሲከብሩ የተቸገሩ ሰዎችን ለመርዳት ገንዘብ በማዋጣት ወደ ኢትዮጵያም ይልካሉ።

እሸቴ በቀለ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ