የኢጣልያ አዲስ መንግሥት እና ስደተኞች 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:13
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:13 ደቂቃ
12.06.2018

ኢጣልያ እና ስደተኞች

ኢጣልያ እና ማልታ ወደ ወደቦቻችን አይምጡብን  ብለው የከለከሏቸው ከ600 በላይ የሚሆኑ ስደተኞች ችግር በስጳኝ ፈቃደኝነት ከተፈታ በኋላ አዲሶቹ የኢጣልያ ባለሥልጣናት ውጤቱን በጉዳዩ ላይ በያዙት ጠንካራ አቋም እንደተገኘ ድል የቆጠሩት ነው የሚመስለው።

አዲሱ የኢጣልያ መንግሥት ህገ ወጥ በሚላቸው ተሰዳጆች ላይ ጥብቅ እርምጃዎችን እንደሚወስድ ሲያሳውቅ ጊዜ አልወሰደበትም፣ተግባራዊ ሲያደርግም እንደዚሁ። የዛሬው አውሮጳ እና ጀርመን ዝግጅታችን የኢጣልያ መንግሥት በፍልሰተኞች ላይ የያዘውን ጠንካራ አቋም እና የተነሱበትን ትችቶች ያስቃኘናል። ለቅንብሩ ኂሩት መለሰ
በኢጣልያ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ አዲስ መንግሥት ከተመሰረተ 12 ቀናት ተቆጥረዋል። ፍለሰተኞች ኢጣልያ እንዳይገቡ እናደርጋለን ሀገር ውስጥ ያሉትንም እናባርራለን ሲሉ ይዝቱ የነበሩት አዳዲሶቹ የኢጣልያ መንግሥት ባለሥልጣናት አሁን ከዛቻ ወደ ተግባር ተሸጋግረዋል። ለዚህ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው ኢጣልያ ባለፈው እሁድ የህይወት አድን መርከብ የታደጋቸውን ከ600 መቶ በላይ ፍልሰተኞችን ወደ ሀገርዋ ላለማስገባት እስከመጨረሻው በእምቢተኝነትዋ መጽንታዋ ነው። ኢጣልያ እነዚህን ስደተኞች ማልታ መውሰድ አለባት ስትል አጥብቃ ተከራክራለች ። ስደተኞቹን ያሳፈረችው መርከብ የነበረችበት ስፍራ ከኢጣልያ ይልቅ ለማልታ ቢቀርብም ስፍራው ከሮም በሚታዘዘው በሊቢያ የፍለጋ እና የህይወት አድን አካባቢ ነው የሚገኘው ስትል ማልታ የእኔ እዳ አይደሉም ብላ ሃላፊነቱን ወደ ኢጣልያ ገፍታለች። በሁለቱ ሀገራት ውዝግብ ምክንያት 123 ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች፣ 11 ህጻናት እና 7 ነፍሰ ጡሮች የሚገኙባቸው 629 ስደተኞች  ሜዴትራንያን ባህር ላይ ሲንገላቱ ውለው አድረዋል። የታደጋቸው አክዋርየስ የተባለው የፈረንሳይ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መርከብ እንዳለው ከመካከላቸው 50ው በአስቸጋሪ የጤና ይዞታ ላይ ነበር የሚገኙት። ኢጣልያ እና ማልታ ሲፎካከሩ የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን ሁለቱ ሀገራት ለችግሩ በሰብዓዊነት እንዲደርሱ ተማጽኖ ነበር። የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ማርጋሪቲስ ሺናስ  ሜዴትራንያን ባህር ላይ በታደጋቸው መርከብ  ሁለት ቀናት የቆዩትን ስደተኞች ከአደጋ ለማዳን ፈጣን ርምጃ እንዲወስዱ ነበር የጠየቀው ። 

«

Italien Sizilien Flüchtlinge auf dem Schiff Aquarius im Hafen von Catania

ለአውሮጳ ኮሚሽን ቀዳሚው እና ዋናው ነገር ሰብዓዊው ጉዳይ ነው። የምናወራው ሕፃናትን ጨምሮ ስለ600 ሰዎች ነው። የሁለቱ ሃገራት ባለስልጣናት ማስቀደም የሚኖርባቸው እነዚህ ሰዎች አስፈላጊው ክብካቤ ማግኘት መቻላቸው መሆን ይኖርበታል።»
ይሁን እና ሁለቱም ሀገራት ለኮሚሽኑ ጥሪ ጆሮ ዳባ ልበስ በማለታቸው ስጳኝ በፈቃደኝነት ስደተኞቹን  ወደቧ ለማሳረፍ ተስማምታለች፤«ሰብዓዊ እልቂትን ለማስቀረት እገዛ ማድረግ እና ደህንነቱ ወደ ተረጋገጠ ወደብ መውሰድ ግዴታችን ነው ስትል። የስደተኞች ጫና በዝቶብኛል የምትለው ኢጣልያ አጋጣሚውን ችግሩን ማሳያ አድርጋ የተጠቀመችበት ነው የሚመስለው። ቀደም ሲል የኢጣልያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የኤኮኖሚ የልማት እና የሠራተኛ እና ማህበራዊ ፖሊሲዎች ሚኒስትር ሉዊጂ ዲ ማዮ ባለፉት ሁለት ቀናት በሜዴትራንያን ባህር ላይ የተከሰተው አጋጣሚ ሀገሪቱ የምትገኝበትን ችግር በቅጡ የሚያስረዳ ነው ሲሉ ተናግረው ነበር።
«የአክዋርየስ ጉዳይ እኛ ስንል የቆየነውን በቀላሉ የሚያሳይ ነው። እኛ ለዓመታት አሳዛኝ ሰብዓዊ ክስተቶችን ስንጋፈጥ ቆይተናል። ሌሎች ደግሞ በራሳቸው ጉዳይ ብቻ ነው የተጠመዱት አሁን እምቢ መባያው ጊዜ ደርሷል። ይህን የምናደርገው አስፈላጊ ከሆነው ስሜት እና ሰብዓዊነት ጋር ነው። ወደ አክዋርየስ መርከብ ዶክተሮችን ያሳፈሩ ጀልባዎች ወዲያውኑ ልከናል። እናም አሁን በዚህ ምክንያት በአውሮጳ ደረጃ መልስ እንጠብቃለን።»
ዲ ማዮ ለማስረዳት የሞከሩት በስተደቡብ የአውሮጳ ህብረት ድንበር የሆኑት ኢጣልያን የመሳሰሉ የሜዴትራንያን ባህር የሚያዋስናቸው ሀገራት በቅርብ ዓመታት የበርካታ ስደተኞች መዳረሻ እና መተላለፊያ ሲሆኑ ሌሎች አባል ሀገራት ችግሩን በጋራ ለመፍታት ከመተባበር ይልቅ ችላ ማለታቸውን ነው። የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ማትዮ ሳልቪኒም የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት

Italien Rom Guiseppe Conte

ለችግሩ መፍትሄ ፍለጋ አለመተባበራቸውን ከዚህ በላይ መታገስ አንችልም ሲሉ አምረው ነበር የተናገሩት። በተለይ በሜዴትራንያን ባህር ላይ በሕይወት አድን ሥራ የተሰማሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ የጀርመን የብሪታንያ የኔዘርላንድስ ወይም የስጳኝ ባንዲራ የሚያውለበልቡ መርከቦች ማልታን አልፈው ኢጣልያ መምጣታቸውን ከአሁን በኋላ ኢጣልያ እንዲሁ በቸልታ የምታልፈው ጉዳይ አይሆንም ነው ያሉት። ኢጣልያ እና ማልታ ወደ ወደቦቻችን አይምጡብን  ብለው የከለከሏቸው ከ600 በላይ የሚሆኑ ስደተኞች ችግር በስጳኝ ፈቃደኝነት ከተፈታ በኋላ አዲሶቹ የኢጣልያ ባለሥልጣናት ውጤቱን በጉዳዩ ላይ በያዙት ጠንካራ አቋም እንደተገኘ ድል የቆጠሩት ነው የሚመስለው። የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማትዮ ሳልቪኒ  የመንግሥታቸውን እርምጃ አንድ ወሳኝ ምልክት  እና ጅማሪ ነው ብለውታል።
«ኢጣልያ ብቻዋን ይህን ግዙፍ ሸክም ይዛ መቀጠል እንደማትችል የሚያሳይ የመጀመሪያው ወሳኝ ምልክት ነው። ባለፉት ጥቂት ሰዓታት ከአክዋይረስ ሴቶችእና ህጻናትን ለመውሰድ ፈቃደኛ መሆናችንን ገልጸን ነበር። ይህን የምለው «ዘረኛ» «ፋሺስት» እና ሌላ ሌላም ስም ለሚሰጡን ነው። ግልጽ ነው ዓላማችን በሜዴትራንያን ባህር ጉዞ ሳይጀምሩ የሰዎችን ህይወት ማዳን ነው። አኳርየስ ነፍሰ ጡሮችን እና ህጻናትን ለመውሰድ ላሳየነው በጎ ፈቃደኝነት መልስ አልሰጠም። ሆኖም ለስጳኝ መንግሥት ቸርነት ምስጋና ይግባው እና ችግሩ ተፈቷል። በግልጽ ለመናገር የአውሮጳ ህብረት በዚህ መንገድ ሊቀጥል አይችልም። እናም ከዛሬ ጀምሮ አዲስ ቀን መቁጠር እንጀምራለን አዲስ ጅማሬ»
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴም ለስጳኝ መንግሥት ምስጋናቸውን አቅርበው በአሳሳቢው እና ጊዜ በማይሰጠው የስደተኞች ጉዳይ ላይ ህብረቱን ሀገራቸውን እንደከዚህ ቀደሙ

Italien | Matteo Salvini

ለብቻዋ ሳይተው ሃላፊነቱን እንዲወስድ ጥሪ አስተላልፈዋል።  
«ስደተኞችን ለተመለከተው አስቸኳይ ሁኔታ አውሮጳ እንደ ቀደሙት ዓመታት ለብቻችን እንዳይተወን ሃላፊነቱን እንዲወስድ ጠይቀናል። ይህ ምልክት በዚያ አቅጣጫ የሚሄድ ነው። ስለዚህ የስጳኝ መንግሥት ጥሪአችንን በመቀበሉ ማመስገን ብቻ ነው የምችለው። » 
ወደ ኢጣልያ በብዛት የሚገቡ ስደተኞች ጉዳይ ሊግ የተባለው ቀኝ ጽንፈኛው ፓርቲ ብዙ ድምጽ ለማግኘቱ ዐብይ ምክንያት ነበር። ፓርቲው ከተመረጠ ወደ ሀገሪቱ የሚመጡ ህገ ወጥ የሚባሉ ስደተኞችን ለምስቆም  እና ሀገር ውስጥ ያሉትንም ለማባረር ቃል ገብቷል። ፓርቲው ከባለአምስት ኮከቦች ንቅናቄ ጋር ከተጣመረ በኋላም መሪው ሳልቪኒ የፓርቲውን ቃል ለማስፈጸም የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር እንደሚሆኑ ባሳወቁት መሠረት ነው ሃላፊነቱን የተረከቡት። ኢጣልያን በስደተኞች ምክንያት ከተፈጠረባት ጫና ለማላቀቅ ትኩረት ሰጥቼ እሰራለሁ የሚለው የአዲሱ የኢጣልያ መንግሥት ባለሥልጣናት በየሄዱበት ጉዳዩን እያነሱ ነው።  በቅርቡ ሲሲሊ በተገኙበት ወቅት ግዛቲቱ ወደ ስደተኞች መጠለያ ሰፈርነት ተቀይራለች ሲሉ ለደጋፊዎቻቸው የተናገሩት ሳልቪኒ ለስደተኞች የሚሰጠውን እርዳታ ለመቀነስ ስደተኞችን ወደ ማዕከላት እየወሰዱ ለማጎር እንዲሁም 500 ሺህ ያህሉን ወደ መጡበት ለመመለስ ቃል ገብተዋል። ይሁን እና ባለሞያዎች እንደሚሉት ይህ ሀገሪቱን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዩሮ የሚያስወጣ ከመሆኑም በላይ ኢጣልያ ከሀገራቱ ጋር ስደተኞችን መልሶ መላክ የሚያስችል ስምምነቶች ስለሌሏት ተግባራዊ ሊሆን

Italien Regierungsbildung | Luigi Di Maio

የማይችል ባዶ ፉከራ ነው ሲሉ አጣጥለውታል። ምንም እንኳን ቀኝ ጽንፈናውን ፓርቲ የሚደግፉ ሚኒስትሩ የሚሉትን ቢቀበሉም በርካታ ኢጣልያውያን ግን በበጎ አያዩትም። ከመካከላቸው አንዱ እኚህ ጣሊያናዊ ናቸው። 
«ጠንካራ ቃላት እጅግ ጠንካራ ሆኖም ባዶ ተስፋዎች ናቸው። ግማሽ ሚሊዮን ሰዎችን ማባረር አይቻልም። የወደፊቱ ጊዜ ለሁሉም ከባድ ነው። ለስደተኞችም ለኢጣልያኖችም» 
ሳልቪኒ በንግግራቸው አንዳንድ መንግሥታትንም አለአግባብ መውቀሳቸው አልተወደደላቸውም። በቅርብ ጊዜው የሲሲሊ ጉብኝታቸው ቱኒዝያ ወንጀለኞችን በጀልባ አሳፍራ ትልክብናለች ማለታቸው ከመካከላቸው አንዱ ነው። ሳልቪኒ አሁንም ከምርጫ ዘመቻው መንፈስ አልተላቀቁም የሚሉት እኚህ ሴት ንግግራቸው የተቆጠበ ሊሆን ይገባ ነበር ይላሉ።
«እኛ ለመካከለኛው ምሥራቅ ቅርብ ነን። በተለያዩ ጉዳዮች ላይም እንሳተፋለን። ለመራጮቻችን ሆነ ለውጭ መንግሥታት የምንለው በሰል ያለ ንግግር መሆን አለበት። »
ሳልቪኒ ስለ ቱኒዝያ የተናገሩት የቱኒዝያን መንግሥት አስቆጥቶ በቱኒዝያ የኢጣልያውን አምባሰደር አስጠርቶ እስከማነጋገር ደርሶ ነበር። የኢጣልያ መንግሥት ስደተኞችን አስወጣለሁ እያለ በሚፎክርበት በአሁኑ ጊዜ የ 34 ዓመቱን ናይጀሪያዊውን ኡዶ የመሳሰሉ ስደተኞች ኑሮን ለማሳካት ደፋ ቀና ይላሉ። የሁለት ልጆች አባት ኡዶ በጎዳና ጽዳት ነው የሚተዳደረው። የሚያገኘው ገንዘብ በቂ ባይሆንም ከመለመን ይሻላል ይላል።
«  ለብዙ ሰዎች ሥራ እንደምፈልግ እነግራቸዋለሁ። እድሉን ካገኙ እንደሚጠሩኝ ይነግሩኛል። መለመን አልፈልግም።»
ኡዶ  ማትዮ ሳልቫኒ በጀቱን ሊቀንሱ በሚፈልጉት በተፋፈገ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ አንድ ዓመት ቆይቷል። አሁን በቀን በሚያገኘው እስከ 15 ዩሮ በሚደርስ ገንዘብ ቤተሰቡን ያስተዳድራል።እርሱ እንደሚለው ሰርቶ በማደሩ ባለመለመኑ ኢጣልያውያን ያከብሩታል። ኡዶ ስለ አዲሱ መንግሥት ሲጠየቅ ብዙም የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ነው የተናገረው። ይሁን እና የሮምዋ የዶቼቤለ ዘጋቢ ሜጋን ሊያምስ እንዳለችው በመጪዎቹ ወራት ኡዶና መሰል ስደተኞች ከአዲሱ የኢጣልያ መንግሥት ብዙ የሚሰሙት ነገር እንደሚኖር መገመት አያዳግትም። 

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

ተዛማጅ ዘገባዎች