1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤሌክትሮኒክስ ትምህርት በአፍሪቃ

ሰኞ፣ ግንቦት 25 2006

ባለፈው የሳምንት መጨረሻ በዮጋንዳ መዲና ካምፓላ በተካሄደው 9ኛ «የኤሌክትሮኒክስ ወይም የኢ-ለርኒንግ ትምህርት በአፍሪቃ» ጉባኤ ላይ ከ68 ሀገራት የተውጣጡ 1400 የሚጠጉ ሰዎች ተገኝተዋል።

https://p.dw.com/p/1CAhm
Internet in Entwicklungsländern
ምስል imago stock&people

የዓመቱ የውይይት ርዕስ « ለነገ ድርድይ ማበጀት» ይሰኝ ነበር። አፍሪቃ ከኤሌክትሮኒክስ ወይም ከኢ-ለርኒንግ ትምህርት ፣ ከመረጃ እና መገናኛ ቴክኖሎጂዎች ትርፋማ በመሆን ላይ ናት ይላሉ ሀሮልድ ኤልትሰን። 1400 ምሁራን የተሳተፉበትን የዘንድሮውን የአፍሪቃ የኢ-ለርኒንግ የጥናት ውጤት ለታዳሚዎቹ ያስተዋወቁት ብሪታንያዊ ።« ኢ-ለርኒንግ በሁሉም መልኩ ትልቅ ለውጥ እያስገኘ ነው። የትምህርቱን ዘርፍ በተመለከተ ብቻ ሳይሆን ኢንዱስትሪውም ጭምር። ኢ-ለርኒንግ ለአፍሪቃ የኢኮኖሚ እድገት እና የማደግ አቅም ዋና ቁልፍ ሆኗል። »

በርግጥ ገበሬዎች ገበያ ሳይሄዱ በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ስለ ዕለቱ የገበያ ዋጋ በስልክ ሊያጣሩ እና በጥሩ ዋጋ ሊሸጡ ችለዋል። እንደ ኤልትሰን ፤ የቱሪዝሙም ዘርፍ ቢሆን በኢ- ለርኒንግ አማካይነት ትርፋማ ሊሆን ችሏል። ሰራተኞች በስልክ አስፈላጊ ስለሆኑ ነገሮች በበቂ ሁኔታ ግንዛቤ መጨበጥ ችለዋል። ሬዲዮ በስልክ መስማት፤ አፍሪቃ ውስጥም አዲስ ነገር መሆኑ ቀርቷል።« ቴክኖሎጂው በተለያየ ዘርፍ ነው አገልግሎት ላይ እየዋለ ያለው። ይህ ሬዲዮ ብቻ ሳይሆን በተለይ ተንቀሳቃሽ ስልክን ይመለከታል። በተለይ እንደ ስማርት ፎን ያሉ ዘመናዊ ስልኮች መስፋፋት ከጀመሩ አንስቶ አቅሙ በጣም እየተጠናከረ ነው ። »

ለጊዜው ግን በአፍሪቃ የተስፋፉት ስልኮች የኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጡ ነገር ግን እጅግ ዘመናዊ የሚባሉት ስልኮች አይደሉም። ይሁንና እውቀትን ለማሰራጨት በቂ ናቸው ይላሉ ኤልትሰን።

ፌስ ቡክ ለምሳሌ እኢአ በ2010 ዓም ኢንተርኔት መጠቀም ለሚችሉ ስልኮች ተስማሚ በሆነ መልኩ ድረ ገፁን ለተጠቃሚዎቹ አቅርቧል። ይህም በአፍሪቃ እጅግ ተቀባይነት በማግኘቱ የተጠቃሚውን ቁጥር ባለፉት 18 ወራት ብቻ እጅጉን ከፍ እንዲል አፍርጓል። ምንም እንኳን በመጀመሪያ ደረጃ ሰዎች ፌስ ቡክን ለማህበራዊ ግንኙነት ቢጠቀሙም « የአፍሪቃ የኢለርኒንግ የጥናት ውጤት እንደሚያሳየው 66 ከመቶ የሚሆኑት የጥናቱ ተሳታፊዎች የማህበራዊ መገናኛውን እዕውቀታቸውን ለማዳበር ጭምርም እንደሚጠቀሙት ገልፀውልናል። ፌስ ቡክ በአፍሪቃ 82 ከመቶ ተወዳጅነት በማትረፍ ከስካይፕ እና ሊንክድኢን በቀደምትነት ቦታ ላይ ይገኛል። ዮጋንዳ ውስጥም ታዋቂ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ነው። ጠበቃ ጌራልድ አቢላ ለምሳሌ በነፃ ለደንበኞቻቸው የህግ ምክር ለመስጠት ፌስ ቡክን ይጠቀማሉ። አቢላ እና ተፎካካሪያቸው ከዚህም ሌላ በኢሜል እና በሳምንት ሁለቴ ደግሞ በስካይፕ- በምስል እየተያዩ የህግ ምክሮችን ይሰጣሉ።

Logo E-Learning Konferenz Nairobi 2007

« ይህ በአሁኑ ሰዓት በምስራቅ አፍሪቃ ያለ ህጋዊ ድረ ገፅ ነው። በዮጋንዳ ብቻ 13000 ሰዎች የፌስኩክ ገፃችንን ወደውልናል። ይህ ደግሞ ምን ያህል ተፈላጊነት እንዳለው እና በስራ ላይ መዋል እንደቻለ ያሳየናል። ያ ነው የማህበራዊ መገናኛው ሀይል።»

የህግ ምክር የሚሰጠው ድረ ገፅ በአሁኑ ሰዓት እንግሊዘኛ ቋንቋ ለማይችሉ ሰዎች ሲባል በሌሎች ሶስት ቋንቋዎች በመተርጎም ላይ መሆኑን አቢላ ገልፀውልናል።ምናልባትም 97 ከመቶ የሚሆነው የዮጋንዳ ጠበቃ በመዲናዋ ካምፓላ በሚኖርበት ሀገር የኤሌክትሮኒክሱ ዕድገት ለዕውቀት ብቸኛው አማራጭ ነው።

ዩልያ ማስ

ልደት አበበ

ነጋሽ መሀመድ