1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ተሸላሚው ኢትዮጵያዊ መሀንዲስ

ረቡዕ፣ ኅዳር 21 2009

ለሽልማት አዲስ አይደሉም። በተሰማሩበት የምህንድስና ዘርፍ በተደጋጋሚ ተሸላሚ ኾነዋል። ኢትዮጵያዊው መሀንዲስ ዶክተር ያዕቆብ አስታጥቄ። የዕውቁ የጃዝ ሙዚቃ ጠበብት፣ የኢትዮ ጃዝ አባት፦ ሙላቱ አስታጥቄ ታናሽ ወንድም። ዘንድሮ ሲሸለሙ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ቀደም ሲል የዓመቱ ጥቁር መሐንዲስ በሚል በሚኖሩበት ዩናይትድ ስቴትስ ለሽልማት በቅተዋል።

https://p.dw.com/p/2TUQf
2016 GEDC Airbus Award  Dr Yacob Asitatike
ምስል Airbus Group 2016 via Dr Yacob Asitatike

የኤርባስ ኩባንያ ተሸላሚው ኢትዮጵያዊ መሀንዲስ

ኢትዮጵያዊው መሀንዲስ ዶክተር ያዕቆብ አስታጥቄ በበረራ ሥነ-ቴክኒክ፣ በኅዋ እና በመከላከያ ነክ ቁሳቁሶች አገልግሎት በመላው ዓለም ቀዳሚው እና ግዙፉ ኩባንያ ኤርባስ ቡድን ሽልማታቸውን ተቀብለዋል። የኤርባስ ቡድን ከዓለም የምሕንድስና ዲኖች ካውንስል ጋር በመተባበር ሴውል ደቡብ ኮሪያ ውስጥ የሰጣቸው ይኽ ሽልማት ከ17 ሃገራት የተውጣጡ 40 መሀንዲሶች የተሳተፉበት ነበር። በውድድሩ እስከ መጨረሻው የገፉ ብቸኛው ጥቁር ተወዳዳሪም ዶክተር ያዕቆብ አስታጥቄ ነበሩ። 

ዶክተር ያዕቆብ አስታጥቄ ዩናይትድ ስቴትስ ቦልቲሞር ሜሪላንድ በሚገኘው ሞርጋን ስቴት ዩኒቨርሲቲ የምሕንድስና ክፍል ተባባሪ ዲን ናቸው። በዚህ ዩኒቨርሲቲ ምህንድስና ያስተምራሉ። ማስተማር ብቻም አይደለም ለየት ያለ ነገር ሲመለከቱ ለሀገሬ ተማሪዎች ይጠቅማል በሚል ያገኙትን አዲስ ነገር ለኢትዮጵያውያን በፍጥነት ያቀብላሉ። በኤሌክትሪካል ምህንድስና ዘርፍ ኢትዮጵያ እና አፍሪቃ ውስጥ የሚያበረክቱት አስተዋጽዖም ለሽልማት አብቅቷቸዋል። ለሽልማት ስላበቃቸው ሥነ-ቴክኒክ እንዲህ ያብራራሉ።

ይህ ለምህንድስና ተማሪዎች የተግባር ልምምድ ጠቃሚ የሆነ አነስተኛ ቁስ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2009 ዓ.ም. ተሠርቶ ሲወጣ «ሞባይል ስቱዲዮ ቦርድ» ይባል ነበር። በአሁኑ ወቅት አምስት ኩባንያዎች በትብብር አነስተኛ ቁሱን በማሻሻል «አናሎግ ዲስከቨሪ» የሚል ስያሜ ሰጥተውታል። አነስተኛ የልምምድ ቁሱ ቤተ-ሙከራ ሳይኖር በየትኛውም ቦታ ልምምድ ለማድረግ ያስችላል።

የዶክተር ያዕቆብ የሥራ ዕቅድ (project) በዋናነት ያተኮረው ለኤሌክትሪካል ምህንድስና የተግባር ልምምድ የሚጠቅም አነስተኛ ቁስ በዝቅተኛ ዋጋ፤ በፍጥነት እና በስፋት እንዲዳረስ ማስቻል ላይ ነው።

ራሼል ሽሮይደር ዶክተር ያዕቆብን ከሸለሙት ሁለት ድርጅቶች የአንደኛው ማለትም የግዙፉ ኤርባስ እና ኤርባስ ቡድን የሠራተኛ ቅጥር ገበያ ጥናት ኃላፊ ናቸው።  ዶክተር ያዕቆብ በውድድሩ ወቅት ባቀረቡት ዝርዝር የሥራ ዕቅድ እና ትግበራ ከተወዳዳሪዎቹ ልቀው የተገኙትበትን ምክንያቶች ሲገልጡ «ዶክተር ያዕቆብ አስታጥቄ ጎልተው የወጡት በአነስተኛ ወጪ በርካታ ነገር በመሥራታቸው ነው።» ብለዋል።

ዶክተር ያዕቆብ አስታጥቄን የሸለመው የኤርባስ ኩባንያ ዓርማ
ዶክተር ያዕቆብ አስታጥቄን የሸለመው የኤርባስ ኩባንያ ዓርማምስል picture-alliance/dpa/C. Charisius

«በእውነቱ በትንሽ ወጪ ኢትዮጵያ ውስጥ በሺህዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎችን በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች አግኝተው እገዛ ሲያደርጉ መመልከት ይደንቃል። ያን ያደረጉትም በጣም ትንሽ በሆነ ወጪ ነው። እንደውም ለዚህ ውድድር የሥራ ዕቅዳቸውን ያስገቡ ሰዎች በአጠቃላይ ማለት ይቻላል የሳቸውን ተግባር ከልብ አድንቀዋል። በእውነቱ ለስብጥርነት ጽንሰ-ሐሳብ ከልብ ነው የሠሩት። በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪቃ የሚገኙ መሀንዲሶችን አቅም በመገንባትም ድጋፍ አድርገዋል» ሲሉም አክለዋል።

ከመላው ዓለም የተውጣጡ መሀንዲሶች በተሳተፉበት የኤርባስ ቡድን እና የዓለም አቀፉ የምህንድስና ዲኖች ምክር ቤት ውድድር ከዶክተር ያዕቆብ ጋር ለፍጻሜ ከቀረቡት ሁለት ሰዎች አንደኛዋ ከታላቋ ብሪታንያ ናቸው። ሌላኛዋ ደግሞ ካናዳን ወክለው ነው የቀረቡት። አፍሪቃን ወክለው ከቀረቡ ተወዳዳሪዎች መካከል ከዶክተር ያዕቆብ በተጨማሪ አንዲት ደቡብ አፍሪቃዊት ቢገኙበትም ወደ ፍጻሜው ግን መምጣት አልቻሉም። በአጠቃላይ ከቺሌ፣ ከፈረንሣይ፣ ከዩናይትድ ስቴትስ እና ከሌሎችም ሃገራት በርካታ ሰዎች የተሳተፉበት ውድድር ነበር። በውድድሩ ከ17 ሃገራት የተውጣጡ 40 ምሁራን የሥራ ዕቅዳቸውን አቅርበዋል።

ሁሉም ተወዳዳሪዎች ሥራዎቻቸውን በዓለም አቀፍ የመሀንዲሶች ጉባኤ ላይ በአካል አቅርበው እንዲያብራሩ ሴውል ደቡብ ኮሪያ ተጋብዘዋል። ሥራዎቻቸውን ያቀረቡትም በዓለም አቀፍ ዳኞች ፊት ነው። በጽሑፍ ያቀረቡት የሥራ ዕቅድ ምን እንደሆነ፣ ከዚህ ቀደም ምን እንደሠሩ፣  የሥራ ዕቅዱ ምን ተጽዕኖ እንደሚፈጥር በመረጃ አስደግፈው ለዳኞቹ አቅርበዋል።

ዶክተር ያዕቆብን አስታጥቄ አሁን ለሽልማት መብቃታቸውና ሀገራቸውን ማስጠራታቸው ብቻውን በቂያቸው አይደለም። ዘንድሮ ለሽልማት በበቁበት ዘርፍ በሚቀጥለው ዓመትም መሳተፍ ይፈልጋሉ። እስከዚያው ድረስ በዓለም መድረክ አወድሰዋቸው የሸለሟቸው ኤርባሶችም የምህንድስና ማዕከላትም የዶክተሩን ሥራ  እየተከታተሉ እስከሚቀጥለው ዓመት ይዘልቃሉ።

«ሽልማቱን የጀመረው ኤርባስ ሲሆን፤ የበለጠ እንዲዳብርም ከዓለም አቀፉ የምህንድስና ዲኖች ምክር ቤት ጋር ተገናኘ። ያን ያደረገውም በሁሉም አይነት የምሕንድስና ትምህርት ዘርፎች ስብጥርን ለማጎልበት እንዲቻል በተግባር አንዳች ነገር የሠሩ ሰዎችን ዕውቅና ለመስጠት በሚል ነው። የሽልማቱ ዋነኛ ዓላማም ብዙ ሰወች በምህንድስና እንዲማሩ እና በምህንድስና ዲግሪ እንዲመረቁ ማስቻል ነው። ትምህርቱም ልዩ ችሎታ ያላቸውን የበለጠ በማበረታታት የተሰባጠረ ልዩ ተሰጥዕ እንዲዳብር ማስቻል አለበት።»

የኤርባስ ቡድን ባልደረባዋ ስብጥር ሲባል የጾታ፣ የዘር፣ የባሕል ብሎም የአስተሳሰብ በአጠቃላይ ሁሉንም አይነት ስብጥርነት የሚያካትት ሰፋ ያለ ትርጓሜ ያለው ነው ብለዋል።  

2016 GEDC Airbus Award  Dr Yacob Asitatike
ከግራ ወደቀኝ 4ኛ ረድፍ ላይ ዶክተር ያዕቆብ አስታጥቄ ሽልማታቸውን ይዘውምስል Airbus Group 2016 via Dr Yacob Asitatike

ዶክተር ያዕቆብ አስታጥቄ ኢትዮጵያ ውስጥ በመመላለስ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላፕቶፖችን እንዲሁም ሌሎች የትምህርት አጋዥ ቁሳቁሶችን በመስጠትም ድጋፍ አድርገዋል። በተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት በመጓዝም ለምህንድስና ትምህርት መቀላጠፍ አስተዋጽዖ አበርክተዋል።

በውድድሩ አሸናፊ በመሆናቸውም ዶክተር አስታጥቄ የ10 ሺህ ዶላር ተሸላሚ ሆነዋል። ከምንም በላይ ግን በሽልማቱ ለአሸናፊዎች ዕውቅና መስጠት  የውድድሩ ዓላማ እንደነበር የኤርባስ አውሮፕላን ኩባንያ ተወካዩዋ ገልጠዋል። 

«እነዚህ ሰዎች ማድረግ ያለባቸውን ቀድሞውኑ አድርገዋል። ግን ለእነሱ ዕውቅና መስጠቱ ጠቀሜታው በሌሎች ዘንድ በደንብ እንዲታወቁ ማድረጉ ላይ ነው። ሥራቸው በሌሎች ዘንድ ታይቶ ተቀባይነት እንዲያገኝ፣ ሌሎች በተመሳሳይ እንዲሠሩት ለማድረግ በሚል ነው የተሸለሙት። ለውድድሩ ፍጻሜ የደረሱት ተወዳዳሪዎች በሠሩት ሌሎች እንዲማሩበት፤ ሁሉንም ባይሆን እንኳን በከፊል መልሰው እንዲሠሩት ለማድረግም ታስቦ ነው መሸለሙ ያስፈለገው።»

ኢትዮጵያዊው መሀንዲስ ዶክተር ያዕቆብ አስታጥቄ ቀደም ሲልም እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2013 ዓ.ም. በማስተማር ልቀው ለወጡ መምህራን የሚሰጠውን የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ ሽልማት አግኝተዋል።

ዘንድሮ በመላው ዓለም በብዛት ነጮች እና ወንዶች በሚሳተፉበት የምህንድስና ዘርፍ ከሁለት አውሮጳውያት ሴቶች ጋር ለፍጻሜ ቀርበው ለድል በቅተዋል። ለከርሞ ምን እንደሚሆን አይታወቅም። ምናልባትም ታላቅ ወንድማቸው፥ የጃዝ አባቱ ሙላቱ አስታጥቄ በሙዚቃ ቅንብሩ «የከርሞ ሰው» እንዳለው የከርሞን ለማየት እኛም «የከርሞ ሰው ይበለን» እንላለን።

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

ኂሩት መለሰ