1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤርትራና ሱዳን ግንኙነት

ዓርብ፣ ግንቦት 15 2006

ሱዳን በምሥራቅ ከምትዋሰናቸው ጎረቤቶቿ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጋር ግንኙነቷን ለማመጣጠን እየጣረች መሆኑ ተገለጠ። የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ዖመር ኧል በሽር የኤርትራ መዲና አስመራን በጎበኙ በጥቂት ወራት ውስጥ የኤርትራው አቻቸው ኢሳያስ አፈወርቂ ከሁለት ሣምንታት በፊት ሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ተገኝተው ተነጋግረዋል።

https://p.dw.com/p/1C4mD
ምስል Ashraf Shazly/AFP/Getty Images

በተለይ ከኤርትራ ጋር የኤኮኖሚ ግንኙነቷን በማጠናከር የነዳጅ እና የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ መፈለጓም በወቅቱ ተዘግቧል። አንዳንድ ዘገባዎች ሱዳን ወደፊት ከኢትዮጵያ የምታገኘውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለኤርትራ ልትሸጥ እየተደራደረች ነው በማለት ጠቅሰዋል። እንደ ዓለም አቀፍ የፀጥታ ጥናት ተቋም የምሥራቅ አፍሪቃ የፖለቲካ ተንታኝ አንድሪውስ አታ አሳሞዋም ሱዳን እና ኤርትራ ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማደስ ጥረት እያደረጉ ነው።

«ሁለቱ ሃገራት ግንኙነታቸውን ለማደስ ከመነቃቃታቸውም ባሻገር የኤኮኖሚ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ዕድል የማጠናከር ፍላጎት እያሳዩ ነው።»

Karte Sudan Englisch

ይኽንኑ ግንኑነት ለማጠናከር ከዛሬ አራት ወራት በፊት የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኧል በሽር ኤርትራ መዲና አስመራ ብቅ ብለው እንደነበር የመገናኛ አውታሮች መዘገባቸው የሚታወስ ነው። ፕሬዚዳንቱ በወቅቱ ከሐሙስ ጥር 8 ቀን፣ 2006 ዓም አንስቶ በኤርትራ የሦስት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት አድርገው ነበር። የኤርትራው አቻቸው ኢሳያስ አፈወርቂ በበኩላቸው ለሦስት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ሱዳን መዲና ካርቱም የገቡት ከአራት ወራት ቆይታ በኋላ ሐሙስ፣ ሚያዝያ 30 ቀን፣ 2006 ዓም ነበር።

ፕሬዚዳንቱ ሱዳንን የጎበኙት የሱዳን መንግሥት በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ሊቢያ ድንበር ላይ በሱዳን እና ሊቢያ ወታደሮች መያዛቸውን ይፋ ካደረገ ከሣምንት በኋላ ነበር። ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ካርቱም ከመግባታቸው አንድ ሣምንት ቀደም ብሎ ወደ 30 የሚጠጉ ኤርትራውያን ስደተኞች ለኤርትራ መንግሥት ተላልፈው መሰጠታቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት በወቅቱ ዘግቧል።

ሱዳን እና ኤርትራ ቁጥጥሩን ጥብቅ ለማድረግ በተስማሙበት ድንበራቸው በኩል በየወሩ በአማካይ ወደ 6000 የሚጠጉ ኤርትራውያን ስደተኞች ሱዳን እንደሚገቡ የተመድ የስደተኞች ጉዳይ መሥሪያ ቤት አስታውቋል። የፖለቲካ ተንታኙ አንድሪውስ አታ አሳሞዋ በኤርትራ እና ሱዳን ድበር በኩል ሰዎችን በሕገወጥ መልኩ ከቦታ ቦታ የማዘዋወር እጅግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንዳለ ጠቁመዋል። ይኽ ድርጊት መቆም አለበት፤ ሆኖም ግን ሀገራቸውን ለመልቀቅ የሚገደዱ ሰዎች መኖራቸውም መታወቅ አለበት ይላሉ የፖለቲካ ተንታኙ።

«ጥያቄው ምን አይነት ስደተኞች ናቸው የሚለው ነው። በሠብዓዊ ቀውስ የተነሳ የሚሰደዱትን ከሆነ እንቅስቃሴያቸውን በቀላሉ ልትገድበው አትችልም። ምክንያቱም ለስደት የሚዳረጉት ሀገራቸው በሚገጥማቸው ችግር የተነሳ ነው እንጂ፤ እንደው በዘፈቀደ ለመሰደድ ፈልገው አይደለም። እናም እንደእዚህ አይነት ስደተኞችን ለማስቆም በጣም ከባድ ነው።»

በእስራኤል ኤርትራውያንን ጨምሮ ስደተኞች ለተቃውሞ ወጥተው
በእስራኤል ኤርትራውያንን ጨምሮ ስደተኞች ለተቃውሞ ወጥተውምስል Reuters

ኤርትራውያን ስደተኞች በሱዳን ድንበር ሲሻገሩ አብዛኛውን ጊዜ የሚያቀኑት ወደ ሊቢያ ሲሆን፤ ከእዚያም የተሻለ ኑሮ ይገኛል ወደሚሉበት እስራኤል እና አውሮጳ ነው የሚሻገሩት። በእዚህ ጉዞ በርካቶች በየበረሃው እንደሚሞቱ፤ ድንበር አካባቢም በጅብ እንደሚበሉ ይነገራል። ከ15 ቀናት በፊት ሊቢያ ድንበር ላይ ከሞቱት 10 ሰዎች መካከል አንደኛው ኤርትራዊ መሆኑ በወቅቱ ተዘግቧል።

ሱዳን ከኤርትራ ጋር የኢኮኖሚ ግንኙነቷን እና የድንበር ቁጥጥሯን ማጠናከር ከመፈለጓ ባሻገር የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነትን ለማሻሻል ጥረት በማድረግ ላይ መሆኗን የፖለቲካ ተንታኙ ገልፀዋል።

«በአካባቢው እንደ ሱዳን ያለ ሀገር ሚና ወሳኝ ነው። እንደ እኔ ሱዳን የምታደራድረው ከኢትዮጵያ እና ከኤርትራ ጋር የረዥም ጊዜ ግንኙነት ያላት በመሆኑ ነው። በሁለቱ ሃገራት መካከል የሰፈነው ውጥረት እንዲረግብ ሱዳን ከረዥም ጊዜ አንስቶ ሙከራ ስታደርግ ነበር። በተለይ ከቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንሥትር ሞት በኋላ አዲሱ ጠቅላይ ሚንሥትር በመጡበት በአሁኑ ጊዜ ሙከራው መደረጉ በእራሱ ጥሩ አጋጣሚ ይመስለኛል። ያ በእራሱ የሚጨምረው ነገር ከፍተኛ ነው።»

በኤርትራ የሱዳን አምባሳደር አብዱል ራህማን ሲር አልካቲምን ጠቅሶ የሱዳን ፕሬስ እንደዘገበው ከሆነ ፕሬዜዳንት ኧል በሽር ኤርትራን እና ኢትዮጵያን ለማደራደር እየሰሩ ነው። ኧል በሽር ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር በማድረግ ላይ መሆናቸውም ተዘግቧል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዓርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ