1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኤውሮ ምንዛሪ ሕልውና አሥረኛ ዓመት

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 15 2001

ኤውሮ ምንም እንኳ የሕዝብ መገልገያ ሆኖ በሥራ ላይ የዋለው ከሰባት ዓመታት በፊት ቢሆንም በጋራ ምንዛሪነት ሕያው እንዲሆን የማይታጠፍ ውሣኔ ከተደረገ ሣምንት በሚገባው አዲስ ዘመን አንድ አሠርተ-ዓመቱን ይደፍናል። አሥር ዓመት በታሪክ ዘመን ስሌት ጨቅላ ጊዜ ቢሆንም የኤውሮ ዕድገትና ዕርምጃ በአጠቃላይ የታላቅ ስኬት መለያ ሆኖ ነው የሚገኘው።

https://p.dw.com/p/GMWA
የአውሮፓ የጋራ ምንዛሪ ኤውሮ
የአውሮፓ የጋራ ምንዛሪ ኤውሮምስል DW

ሣምንት በሚገባው የጎርጎሮሣውያኑ አዲስ ዘመን መጀመሪያ ከአውሮፓ ሕብረት የትስስር ፕሮዤዎች መካከል ምናልባትም ታላቁና ከባድ የነበረው የኤውሮ ምንዛሪ ክስተት አሥር ዓመት ይሞላዋል። ምንዛሪው የሕዝብ መገልገያ የሆነው ምንም እንኳ ሁለት ዓመታት ዘግየት ብሎ ይሁን እንጂ የኤውሮ ሃገራት አዲሱን ገንዘብ የጋራ ለማድረግ የወሰኑት ጥር 1 ቀን. 1999 ነበር። የጋራ ምንዛሪው ከአውሮፓ የትስስር መንፈስ አንጻር ታሪካዊ ግምት ቢሰጠውም እርግጥ የዕርጋታ ዝቤት እንዳይከተል ስጋት ያደረባቸውና ከብሄራዊ ምንዛሪዎቻቸው መላቀቁ የከበዳቸው የሕብረቱ ነዋሪዎች በጊዜው ጥቂት አልነበሩም።

በዚህ በጀርመን ለምሳሌ እስከዚያው የዕርጋታ ዋስትና ሆኖ የቆየውን ብሄራዊ ምንዛሪ ዴ-ማርክን ወደ ታሪክ መዘክር መሸኘቱ ለብዙዎች የማይዋጥ ነገር ነበር የሆነው። በዕውነትም የተፈራው ችግር ጨርሶ አይዝለቅ እንጂ ለመከሰት ብዙ ጊዜ አልወሰደበትም። ኤውሮ ለተገልጋዮቹ አገራት ዜጎች የኑሮ ውድነት መለያ ይሆናል። በዚህ በጀርመን “ኤውሮ-ቶይሮ”፤ ኤውሮ-ውድ የሚል መጠሪያ ይሰጠዋል። እርግጥም ዛሬ ከቀድሞዎቹ ብሄራዊ ምንዛሪዎች የመግዛት ሃይል ሲነጻጸር ኤውሮ ሰፊ የኑሮ ውድነትን አስከትሎ ነው የሚገኘው። ይሁን እንጂ በአሠርተ-ዓመታት ሂደቱ ከፖለቲካው ትስስር ባሻገር በተገልጋዮቹ ሃገራት ገበያ በኤውሮ ዞን ታላቅ ዕርምጃን ለማስከተል በቅቷል።

ወደ ኤውሮ ጽንሰ-ሃሣብ ታሪክ ከግማሽ ምዕተ-ዓመት በላይ ወደ ኋላ መለስ እንበልና የአውሮፓ እንድነት ያለ ምንዛሪው ውህደት ዕውን እንደማይሆን የተተነበየው ብዙ ቀደም ብሎ ገና በ 1950 ዓ.,ም. ነበር። “የአውሮፓ አንድነት በጋራ ምንዛሪ ዕውን ይሆናል ወይም ጨርሶ አይሳካም”። ይህን በጊዜው የተናገሩት ፈረንሣዊው የፊናንስ ፖሊሲ ባለሙያ ዣክ ረፍ ነበሩ። ከዚያ በኋላ አውሮፓን በምንዛሪ ሕብረት ለማስተሳሰር በማሕበረሰቡ ውስጥ በ 60ና 70ኛዎቹ ዓመታት የመጀመሪያው ማቅማማት ይደረጋል። የቀድሞው የጀርመን ቻንስለር ሄልሙት ሽሚት መለስ ብለው እንደሚያስታውሱት ይሁንና ዕርምጃ የመውሰዱ ግፊት የተጠናከረው ከውጭ ነበር።

“ይህ የቪየትናምን ጦርነትና ያስከተለውን የገንዘብ ወጪ ተከትሎ ነበር የመጣው። የኒክሰን አስተዳደር የዶላርን መጠን በወርቅ የመተመን ግዴታ ብቻ ሣይሆን ከዚሁ ባሻገር በ 1972 እና 1973 በምንዛሪዎች መካከል ያለውን ቁዋሚ የልውውጥ መጠን ግዴታም ያነሳሉ። እርግጥ የፈረንሣይና የጀርመን የፊናንስ ሚኒስትሮች የዚህን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጨረሻ አንስቶ በፍቱንነት ሲሰራበት የቆየውን የብሬተን ዉድስ ስምምነት ያላንዳች ተተኪ አማራጭ መወገድ አልተቀበሉም። ግን ከአሜሪካ የኤኮኖሚ ክብደት አንጻር ዕርምጃውን ልንገታው ሳንችል ቀርተናል”

በነገራችን ላይ በጊዜው የጀርመን የፊናንስ ሚኒስትር የነበሩት ቻንስለር ሄልሙት ሽሚት የዕድሜ ባለጸጋ በመሆን ትናንት ዘጠናኛ ዓመት ልደታቸውን አክብረዋል። እንግዲህ ያኔ ስድሥት የጊዜው የአውሮፓ ማሕበረ-ሕዝብ ዓባል ሃገራት፤ ወደኋላም ዘጠኝ ይሆናሉ፤ የምንዛሪ ትስስር ስምምነት ማድረጋቸው ከአሜሪካ አንጻር የመከላከል ዕርምጃ ነበር ለማለት ይቻላል። መንግሥታቱ የገንዘባቸው ውጣ-ውረድ በራሳቸው መካከል ተገድቦ እንዲወሰን ለማድረግ ግዴታ ይገባሉ። የዚህ የምንዛሪ ግንኙነት ደምብ ዓላማም በአውሮፓው ማሕበረ-ሕዝብ ውስጥ የምርት፣ የአገልግሎትና የካፒታል እንቅስቃሴን ማቃለል፤ ማዳበርም ነበር።

ዕቅዱ ገቢር እንዲሆን የየሃገሩ ማዕከላዊ-ባንኮች ሚና ወሣኝነት ነበረው። አንዱ ምንዛሪ ከመሥመር ሊያፈነግጥ ካለ ጣልቃ መግባት ነበረባቸው። ይህም የሚካሄደው Europian Currency Unit በአሕጽሮት ኤኩ በተሰኘ የምንዛሪ አንድነት መስፈርት ነበር። ቻንስለር ሄልሙት ሽሚት መለስ ብለው ሲያስታውሱ ኤኩ የጋራው ምንዛሪ ጽንስ ይሁን አይሁን ያኔ ገና ግልጽ አልነበረም።

“ኤኩ ዘግየት ብሎ ወደጋራ ምንዛሪ ይለወጥ አይለወጥ ያኔ ሳንነጋገርበት ያለፍነው የግብ ጽንሰ-ሃሣብ ነበር። በመጨረሻ የጋራው ምንዛሪ መሆኑ እንግዲህ ጨርሶ ግልጽ አልነበረም። ከብሄራዊ ምንዛሪዎች ጋር ጎን ለጎን የሚሄድ ሊሆንም ይችል ነበር። ጉዳዩን ወደፊት ያራመዱት ታዲያ ዣክ ዴሎር ነበሩ”

ዴሎር እንደ አውሮፓ ኮሚሢዮን ርዕስነታቸው ለአውሮፓው የምጣኔ-ሐብትና የምንዛሪ ሕብረት ጽኑ መሠረት ይጥላሉ። ዕርምጃቸው ከአሥር ዓመታት በፊት የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ እንዲመሰረትና ኤውሮም የጋራ ምንዛሪ እንዲሆን ቁልፍ ጉዳይ ነበር። በሌላ በኩል የጊዜው የጀርመን ፌደራል ባንክ አስተዳዳሪ ካርል-ኦቶ-ፖህል እንደሚሉት ለኤውሮ ክስተት ተጨማሪ ምክንያት አልጠፋም። ይሄውም በርሳቸው ዕምነት የአንዴው የጀርመን ምንዛሪ የዶቼ ማርክ የስኬት ታሪክ ነው። የጀርመኑ ምንዛሪ እጅግ የተረጋጋ ነበርና በተለይም ትናንሽ ሃገራት ብሄራዊ የገንዘብ ፖሊሲያቸውን እየተዉ ገንዘባቸውን ከዴ-ማርክ ማስተሳሰሩን መርጠዋል። የፌደራል ባንኩ አስተዳዳሪ እንደሚያስታውሱት፤

“ይህ ሆላንድንና ዴንማርክን በመሳሰሉት ሃገራት ዘንድ ተቀባይነት ነበረው። አዎን፤ ትንሽ ከመሆናችን የተነሣ ጀርመኖች አግባብ ያለው የገንዘብ ፖሊሲ ካራመዱ ልንከተላቸው እንችላለን ይላሉ። የምንዛሪው ውህደት መሣካት ለፈረንሣይም እንዲሁ የክብር ጉዳይ ነበር። የጋራ የአውሮፓ ምንዛሪ ሊሰፍን የቻለውም ለዚህ ነው ብዬ ነው የማስበው። ዛሬ በአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ ሸንጎ ውስጥ መላው የሕትመት ባንኮች ይወከላሉ። ማለት የአውሮፓ የፊናንስ ፖሊሲ የሚዘወረው እንቀድሞው በጀርመን ፌደራል ባንክ ሣይሆን ዓባል ሃገራቱን በሚወክል አካል ነው”

ይሄው በዚህ በጀርመን በፍራንክፈርት ከተማ ተቀማጭ የሆነው አካል፤ የአውሮፓው ማዕከላዊ ባንክ እስካሁን ኤውሮን አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ ማንኛውም የፊናንስ ነውጽ ሳያግደው ወደፊት ሊያራምድ በቅቷል። ኤውሮ በንግድ ላይ በዋለበት በመጀመሪያው ዕለት እ.ጎ.አ. ጥር 4 ቀን. 1999፤ ከአሥር ዓመታት በፊት መሆኑ ነው፤ በአንድ ዶላር ከአሥራ ሥምንት ሣንቲም ነበር የተተመነው። ግን ብዙ አልቆየም ዋጋው በተከታታይ እያቆለቆለ በመሄዱ የሕብረቱ የኤኮኖሚ ጠበብትና ፖለቲከኞች ስጋት ላይ ይወድቃሉ። የአዲሱ ሚሌኒየም መግቢያ 2000 ዓ.ም. እስካሁን ዝቅተኛው የኤውሮ መጠን የተመዘገበበት ነበር። አንድ ኤውሮ በ 82 የዶላር ሣንቲም ዋጋ ብቻ ይለወጣል።

ግን ይህ ዛሬ የኋላ ኋላ ሲታይ የዳዴ ዘመን ችግሩ እንደነበር ግልጽ ነው። ምክንያቱም ከዚያን ወዲህ የታየው ጉዞ ወደ ላይ ማሻቀብ ብቻ ነበርና! የጋራው ምንዛሪ ኤውሮ ባለፈው ሐምሌ ወር፤ በትክክል ሐምሌ 15 ቀን. 2008 ዓ.ም. እስካሁን ከፍተኛውን የዕለት ጥንካሬውን በገበያ አስመስክሮ ውሏል። ዕለቱ ተገልጋዩ በአንድ ኤውሮ ልዋጭ አንድ ዶላር ከስልሣ ገደማ ለማግኘት የበቃበት ነበር። እርግጥ የኤውሮ መጠናከርና የዋጋው ማየል ማራኪነቱ ምርቱን ወደ ዶላር አካባቢዎች ለሚልክ ወይም በዚያው ለሚዝናና ቱሪስት ነው።

የጋራው ምንዛሪ የውጭ ዋጋ ሌላውን ወገን ብዙም የሚያስጨንቅ አይሆንም። ይልቁንም ሁሉም የሚያተኩረው በምንዛሪው ውስጣዊ ዕርጋታ ላይ ነው። ከሁሉም በላይ በዚህ በጀርመን ቀደም ሲል እንደጠቀስነው ኤውሮ የውድነት መለያ ነበር። ምንም እንኳ የሰንጥረዦች መረጃ ባይደግፈውም የገንዘብ ተመን መውደቅና የኑሮ ውድነት ስሜት በሕብረተሰቡ ውስጥ አጥብቆ ሥር የሰደደበት ጊዜ ጥቂት አልነበረም። በ 11ዱ የኤውሮ ተገልጋይ ሃገራት በጅምሩ አማካዩ የዋጋ ንረት በዓመት 2,1 ከመቶ ነበር። ይህም የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ ካስቀመጠው ሁለት በመቶ ግብ ጥቂት ላቅ ያለ መሆኑ ነው።

ለማንኛውም ዛሬ 320 ሚሊዮን አውሮፓውያን በጋራው ምንዛሪ ይተማመናሉ። ኤውሮ በወቅቱ በ 15 ሃገራት ውስጥ የክፍያ መሣሪያ ለመሆን በቅቷል። ስድሥት ተጨማሪ ሃገራት ቢቀር አነስተኛ መንግሥታት ደግሞ በዝምታ ይሰሩበታል። ይህም ለስኬቱ አንዱ ምሥክር ነው።

“እንደኔ አመለካከት የአውሮፓን ሕብረት አሟልተን ጨርሰናል ብለን ለማውራት ከፈለገው ተጨማሪ ግማሽ ምዕተ-ዓመት ልንፈጅ እንችላለኝ። ኤውሮ ግን ከአንድ አሠርተ-ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የዓለም ምንዛሪ መሆኑን እንደሚያረጋግጥ አልጠራጠርም”

እርግጥም የቀድሞው የጀርመን ቻንስለር ሄልሙት ሽሚት ዕውነት አላቸው። የኤውሮው ተገልጋይ ሃገራት ገበያ ገና ከዛሬው በዓለም ላይ ጠንካራው ነው። በዶላር ክስረትና ማቆልቆል የተነሣም የተረጋጋ ምንዛሪነቱ በዓለምአቀፍ ደረጃ ይበልጥ ክብደት እያገኘ ሲሄድ ነው የሚታየው።