1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«በምሥራቅ ወለጋ የእሥረኞች የፍርድ ሂደት ተጓቷል»ኦፌኮ

ሰኞ፣ ሰኔ 22 2012

የምስራቅ ወለጋ የኦፈኮ ጽ/ቤት ኃላፊ እንዳስታወቁት ነቀምቴ ከተማን ጨምሮ በዞኑ ሀሮ ሊሙ፣ ኤባቱ በተባሉ እና ሌሎችም አካባቢዎች የድርጅታቸው ደጋፊዎች ታስረዋል፡፡የምስራቅ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳር አቶ አዝመራ ኢጃራ በበኩላቸው በምስራቅ ወለጋ የተለያዩ አካባቢዎች ወንጀል ሰርተዋል ተብሎ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ለህግ እንዲቀርቡ ተደርጓል ብለዋል፡፡

https://p.dw.com/p/3eW4C
12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

በምስራቅ ወለጋ ነቀምቴ ከተማ ከወራት በፊት የታሰሩ ሰዎች የፍርድ ሂደት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት በመጓተቱ  ለችግር መጋላጣቸውን የታሳሪ ቤተሰቦች ተናግረዋል፡፡ በምስራቅ ወለጋ የተለያዩ ወረዳዎች ከሚያዚያ ወር አንስቶ  አባላቱን ጨምሮ እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ 56 ሰዎች መታሰራቸውን የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስም  አስታውቀዋል፡፡  የምስራቅ ወለጋ የኦፌኮ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፈቃዱ አያና በተለያዩ ገዜያት እስር እና ማንገላታት ተጠናክሮ መቀጠሉን በስልክ ተናግረዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል የምስራቅ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አዝመራ ኢጃራ በበኩላቸው የመንግስት አመራሮችን ጨምሮ በወንጀል የተጠረጠሩ እና የህዝብን ሰላም የሚያውኩ አካላት  በዞናቸው በተለያዩ ጊዜያት ለህግ እንዲቀርቡ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ወ/ሮ ፍረዘር መሰለ የነቀምቴ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ ባለቤታቸው በሚያዚያ ወር መታሰሩንና በወቅቱ የአባ ቶርቤ አስተባባሪ ነህ ተብሎ በፖሊስ መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡ ባለቤታቸው አቶ ኃይሌ ሰለሞን የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አባል መሆኑን የገለጹ ሲሆን ከዚህ በፊት ቀዶ ጥገና ተደርጎላቸው እንደነበርም አክለዋል፡፡ ባለቤታቸው ከታሰረ በኃላ ቤተሰባቸውን ለማስተዳዳር  የሚሆን ገቢ በማጣታቸው ለከፍ ችግር መጋለጣቸውን አስረድተዋል፡፡ በከተማው ኮከት በተባለ ጣቢያ አቶ ኃይሌን ጨምሮ  42 ሰዎች ታስረው   እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡ 
የምስራቅ ወለጋ የኦፈኮ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፈቃዱ አያና በበከላቸው እንዳስታወቁት ነቀምቴ ከተማን ጨምሮ በዞኑ ሀሮ ሊሙ፣ ኤባቱ በተባሉ እና ሌሎችም  አካባቢዎች የድርጅታቸው ደጋፊዎች እንደታሰሩ ገልጸዋል፡፡ በምስራቅ ወለጋ ዞን  የተለያዩ ወረዳዎች ከታሰሩ ሰዎች ከሶስት ወር በላይ የሆናቸው እንዳሉም  ተናግረዋል፡፡ የድርጅቱ አባል በመሆናቸው በርካታ ሰዎችን በየቦታው  ማሰር፣  ማስፈራሪያዎችና ዛቻም እየደረሰባቸው  ይገኛል ብለዋል፡፡ የታሰሩት አብዛኞቹም በነቀምት ከተማ፣ከኤበንቱና ሃሮሊሙ  ሲሆን ከታሰሩት መካከከልም በዞኑ የድርጅቱ የወጣቶች ሊግ የነበሩትን አቶ ሐይሌ ሰለሞን እና ሌሎችም በንግድ ስራ የተሰማሩ ግለሰቦች  እንደሚገኙበት ጠቁመዋል፡፡ 
የምስራቅ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳር አቶ አዝመራ ኢጃራ በዚው ጉዳይ ላይ በሰጡት ማብራሪያ በምስራቅ ወለጋ የተለያዩ አካባቢዎች ከዚህ በፊት ወንጀል ሰርተዋል ተብሎ የተጠረጠረጡ ግለሰቦች ለህግ እንዲቀርቡ ተደርገዋል፡፡ በምስራቅ ወለጋ ኤባንቱ የተባለው ወረዳም በግድያ ወንጀል የተጠረጠሩ ሰዎች ለህግ መቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡ የዞኑ አስተዳደር ባለው መዋቅር ህግ ያስከብራል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው በዞናቸው በወንጀል ሳይጠረጠር በፖለቲካ አባልነቱ የታሰረ ማንም ሰው የለም ብለዋል፡፡ ማንም የፖለቲካ ድርጅትም ሆነ ግለሰበ ከመወነጃል ይልቅ የደረሰበት በደል ካለ ለዞናቸው ማቅረብ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡


ነጋሳ ደሳለኝ 

ኂሩት መለሰ