1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእሥያ ፓሲፊክ አካባቢ ሀገሮች ዓቢይ ጉባዔ በባንኮክ

ሰኞ፣ ጥቅምት 9 1996
https://p.dw.com/p/E0gD

በምሕፃሩ አፔክ በመባል የሚታወቀው የእሥያ ፓሲፊክ አካባቢ ሀገሮች የኤኮኖሚ ትብብር ማኅበር ዓቢይ ጉባዔ ዛሬ በታይላንድ መዲና ባንኮክ ተጀመረ። በአፔክ የሚጠቃለሉት ሀያ አንዱ አባል መንግሥታት ከዓለም ሕዝብ መካከል ወደ ግማሽ የሚጠጋውን ይወክላሉ። ዩኤስ አሜሪካም የዚሁ ማኅበር አባል ናት። ትናንት ባንኮክ የገቡት አሜሪካዊው ፕሬዚደንት ጆርጅ ዳብልዩ ቡሽ ዓለም አቀፉ ፀረ ሽብር ዘመቻ በዓቢዩ ጉባዔ ላይ ቀዳሚውን ትኩረት የሚያገኝ ርዕስ እንደሚሆን ገልፀዋል። ቡሽ በዓቢዩ ጉባዔ ላይ ባሰሙት ዲስኩራቸው ላይ፡ “ራሳችንን፡ ሥልጣኔአችንን እና የዓለምን ሰላም እንከላለላለን። በአሸባሪዎችም አንደናገጥም”፡ ብለዋል። የዩኤስ አሜሪካ የልዑካን ቡድን በቀላሉ ሊዘዋወር የሚችለውና ከመሬት ወደ አየር የሚወነጨፈው ሮኬት የሚታገድበትን ሀሳብ ይዞ ነው የፀጥታ ጉዳዮች በይበልጥ ይጎሉበታል ወደ ተባለው የባንኮክ ዓቢይ ጉባዔ የተጓዘው። ከዚህ ሌላም ዋሽንግተን ሽብርተኝነት በእሥያ ፓሲፊክ አካባቢ ሀገሮች ውስጥ የደቀነውን ሥጋት ለመታኣገያ የሚሆን ከአምስት ሚልዮን ዶላር በላይ የያዘ አንድ በጀት የሚዘጋጅበትንም ሀሳብ በዓቢዩ ጉባዔ ላይ አቅርባለች። ገንዘቡ በእሥያ የልማት ባንክ አማካይነት በሽብርተኝነት አንፃር ትግላቸውን ለማጠናከር ለሚሹ ሀገሮች ይቀርባል። በባንኮክ ዓቢይ ጉባዔ ላይ ባካባቢው ወደቦች በሚራገፉ የዕቃ ማጓጓዣዎች ላይ ጥብቁ ፍተሻ በሚደረግበት፡ በአየር ማረፊያዎች የፀጥታው ሁኔታ በሚሻሻልበት፡ በጦር መሣሪያ ንግድ እና በሕገ ወጡ የገንዘብ ዝውውር ላይ ቁጥጥሩ በሚጠናከርበት ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።

ጉባዔው ከመጀመሩ አንድ ቀን በፊት ባንኮክ የገቡት ቡሽ በትናንቱ ዕለት የከተማይቱን ቤተ መቅደስ ጎብኝተዋል፤ በአፍጋኒስታን ከአሜሪካውያኑ ጦር ኃይላት ጎን ከተሰለፉት የታይ ወታደሮች ጋር ተነጋግረዋል፤ ከሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ታካሃሲን ሺናዋትራ ጋርም ተገናኝተው፡ በተለይ የኦሳማ ቢን ላደን መልዕክቶችን የያዙ ቪድዮዎች ከጥቂት ቀናት በፊት በፊት ከወጡ በኋላ የአል ቓይዳ ድርጅታቸው ስለደቀነው ሥጋት ተወያይተዋል። አል ቓይዳ አሁንም ለነፃው ዓለም ሥጋት መሆኑን የገለፁት አሜሪካዊው ፕሬዚደንት ነፃ መንግሥታት ይህንኑ ነፍሰ ገዳይ ድርጅትን ለፍርድ ለማቅረብ ተባብረው መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የታይላንድ መዲና ባንኮክ ለዓቢዩ ጉባዔ መልኳን አሳምራ ከመቅረብዋ ሌላ፡ አሥር ሺህ ፖሊሶችን በማሠማራት የፀጥታውን ጥበቃ አጠናክራለች። በጥቂት ሺህ የሚቆጠሩ የቡሽ አቋም ተቃዋሚዎችምናንት በግዙፍ የፀጥታ ኃይላት አማካይነት ወደ ጉባኤው አዳራሽ አካባቢ እንዳይደርሱ ተደርገዋል። ስድስት ከመቶ ዓመታዊ የኤኮኖሚ ዕድገት ያሳየችው ታይላንድ ከእሥያ ኤኮኖሚያዊ ቀውስ መዘዝ ያገገመች ሀገር መሆንዋን ለማሳየት ነው የምትሞክረው። ጠቅላይ ሚንስትርዋ ሺናዋትራም ከትልቋ የሀገራቸው ተጓዳኝ ዩኤስ አሜሪካ ጎን በመቆም፡ ከጥቂት ወራት በፊት ባካባቢው የአክራሪዎች አሸባሪዎች መሪ የሚባሉትን ሐምባሊን ለዩኤስ ባለሥልጣናት አስረክበዋል። በምላሹም ከዩኤስ አሜሪካ ጋር አማላይ የንግድ ግንኙነት ስምምነት ለማግኘት ተስፋ አድርገዋል። በምሕፃሩ አፔክ በመባል የሚታወቀው የእሥያ ፓሲፊክ አካባቢ ሀገሮች የኤኮኖሚ ትብብር ማኅበር እአአ በ 1989 ዓም ከተመሠረተ ወዲህ አንድ ነፃ የንግድ ዞን ለማቋቋም በመጣር ላይ ይገኛል። በመሆኑም፡ አሁን የሚካሄደው የባንኮክ ዓቢይ ጉባዔ ባለፈው መስከረም በካንኩን ሜክሲኮ የከሸፈው የዓለም የንግድ ድርጅት ድርድር እንደገና የሚነቃቃበት ምልክት እንዲፈነጥቅ ይጠበቃል። ሌላው ዓቢዩ ጉባዔ የሚመክርበት ጉዳይ ሳርስ በመባል የሚታወቀው የሣምባ ምች በሽታ ነው።