1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእርሻ ድጎማና የታዳጊው ዓለም ችግር

ረቡዕ፣ መጋቢት 22 2002

የበለጸጉ መንግሥት ለገበሬዎቻቸው የሚሰጡት የእርሻ ድጎማ የገበያ ዋጋን በመጣል ለታዳጊው ዓለም አርሶ-አደር የሕልውና ፈተና መሆኑ የቀጠለ ጉዳይ ነው።

https://p.dw.com/p/MjLC
ምስል picture alliance/dpa

ለምሳሌ የጥጥ ምርትን ብንወስድ የአሜሪካ መንግሥት በ 2008/2009 የምርት ወቅት ለገበሬዎቹ የሰጠው ድጎማ ከሶሥት ሚሊያርድ ዶላር ይበልጣል። ይህን መሰሉን ድጋፍ ለያገኙት ቀርቶ ሊያልሙት እንኳ የማይችሉት የአፍሪቃ ገበሬዎች ታዲያ ድጎማው እንዲያበቃና ፍትሃዊ የገበያ ፉክክር እንዲሰፍን ለዓመታት ሲጠይቁ ነው የኖሩት። ግን ብዙም የተለወጠ ነገር የለም። ይሁን እንጂ የብራዚል መንግሥት አሁን በኤኮኖሚ ማዕቀብ በአሜሪካ ላይ ግፊት ለማድረግ እንደገና እየሞከረ ነው።

ጠንካራ የገበያ ፉክክር፣ የምርታማነት ጉድለትና የአካባቢ አየር ለውጥ ለታዳጊው ዓለም በአጠቃላይና በተለይም ለአፍሪቃ ጥጥ አምራች ገበሬ ፈታኝ ነገሮች ሆነው ነው የቆዩት። ብዙዎች የአፍሪቃ ገበሬዎች ይህን ምርት ማምረት ይተዋሉ ወይም ሌላ ዘር መትከል ይጀምራሉ። የዛምቢያ የጥጥ አምራቾች ማሕበር ሃላፊ ጆዜፍ ኒኮል እንደሚሉት በተለይም በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ትናንሽ ገበሬዎችን ይብስ የሚያስቆጣው ደግሞ የምርታቸው ዋጋ ዝቅተኛነት ነው።

“እኛ እዚህ ትላልቅ ቤተሰቦችን መንከባከብ አለብን። ለዚህም ነው በጥጥ ተክል ተግባር የተሰማራነው። ይህ በመሠረቱ በቂ ገንዘብ ሊያስገኝን በተገባ ነበር። ይሁን እንጂ በዚህ ፍትህ በጎደለው የፉክክር ሁኔታ አናገኘውም”

ለምን ቢባል ለምሳሌ የአሜሪካ መንግሥት ለዓመታት 25  ሺህ ገደማ ለሚጠጉ ጥጥ አምራች ገበሬዎቹ የድጎማ ገንዘብ ሲያፈስ ነው የኖረው። ምክንያቱም የተሰወረ አይደለም። ያለዚህ የገንዘብ ድጎማ የአሜሪካ ጥጥ በዓለምአቀፍ ደረጃ ለፉክክር ብቁ ሊሆን ባልቻለ ነበር። በብዙ ሺህ የሚቆጠር የሥራ ቦታም እንዲሁ አደጋ ላይ በወደቀ! የሆነው ሆኖ ችግሩ የአሜሪካ መንግሥት በድጎማው የዓለም ገበያን ዋጋ መጫኑ ነው። በዚሁ የተነሣ ደግሞ ቁጥራቸው ሃያ ሚሊዮን ገደማ የሚጠጋ የአፍሪቃ ጥጥ አምራች ገበሬዎች ገቢ ይቀንሳል። እርግጥ በጉዳዩ አዘውትሮ ቅሬታ መሰማቱና ትችት መሰንዘሩ አልቀረም። ክፋቱ ግን አንዳች ለውጥ አለመደረጉ ነው። የዓለምአቀፉ ግብረ-ሰናይ ድርጅት የኦክስፋም ባልደረባ ሮሜን ባኒቺዮ እንደሚሚሉት ይህም ያለ ምክንያት አይደለም።

“አሜሪካ ውስጥ ከብሄራዊው ሸንጎ ጋር ጥሩ አግባብ ያለው ጠንካራ የጥጡ ዘርፍ ተጽዕኖ አድራጊ ወገን አለ። እንደኛ አመለካከት ይህ ነው እስካሁን በየጊዜው የተደረጉ የለውጥ ሙከራዎችን ሲያሰናክል የቆየው። እንበል የአሜሪካ መንግሥት ለለውጥ ፍላጎት ቢያሳይ እንኳ በሸንጎው ይሰናከላል”

ይህ ተጽዕኖ አድራጊ ወገን ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ ለምሳሌ የጎርጎሮሣውያኑ  2004  ዓ.ም. ሁኔታ በግልጽ አሳይቷል። ብራዚል በጊዜው የአሜሪካን ድጎማ በመቃወም ዋሺንግተንን በዓለም ንግድ ድርጅት ዘንድ ከሣ ነበር። ክሷ ለነገሩ ተቀባይነት ማግኘቱም አልቀረም። ግን ከዚያን ወዲህ ብዙም የተቀየረ ነገር አለ ለማለት አይቻልም። አሜሪካ ምንም እንኳ አንዳንድ አንቀጾችን ብትቀይርም ድጎማው ዛሬም መፍሰሱን እንደቀጠለ ነው። ይህም ሆኖ የአሜሪካ ብሄራዊ የጥጥ አምራቾች ም/ቤት ጌሪይ አዳምስ ጥፋቱን በሌሎች ላይ ነው የሚላክኩት።

“የዛሬው የጥጥ ዋጋ ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረው 50 በመቶ ከፍ ያለ ነው። አሜሪካ በበኩሏ ምርቷን በሰፊው ቀንሳለች። ብራዚል፣ ሕንድና ቻይና ግን ይበልጥ ብዙ እያመረቱ ነው። እና ይህን ሂደት ሲመለከቱት በኛ አስተያየት የብራዚል ዕርምጃ አግባብ የለሽ ነው”

አዳምስ አግባብ የለሽ ያሉት ብራዚል አሁን እንደገና የያዘችው ዕርምጃ የአሜሪካን ድጎማ ለመግታት የተወጠነ ጥረት ነው። የብራዚል መንግሥት ከነገው ዕለት አንስቶ ወደ አገር በሚያስገባቸው ከመቶ የሚበልጡ የአሜሪካ ምርቶች ላይ የሚያስከፍለውን ታክስ ከፍ ያደርጋል። እርግጥ ይህ የሚሆነውም በዓለም ንግድ ድርጅት ፈቃድ ነው። ዕርምጃው የሚነካቸው የአሜሪካ ኩባንያዎች ታዲያ ብርቱ የንግድ ጦርነትና  እስከ 600  ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ኪሣራ ላይ እንዳይወድቁም መስጋታቸው አልቀረም። በሌላ በኩል አሜሪካ ሕገ-ወጥ የሆነውን ድጎማ ካቆመች ታክሱም መልሶ የሚቀንስ ይሆናል። ሆኖም በዓለም ንግድ ድርጅት መቀመጫ በጀኔቫ የብራዚል አምባሣደር ሮቤርቶ አዜቬዶ እንደሚያስረዱት እስካሁን በዚህ አቅጣጫ የታየ ዕርምጃ ገና የለም።

“አሜሪካውያኑ በዕርምጃችን ያዘኑ መሆናቸውን በይፋ ተናግረዋል። ግን እኛም ያዘንን መሆናችንን በዚህ አጋጣሚ ለመናገር እወዳለሁ። እኛ ታክስ የመጨመር ዕርምጃ ለመውሰድ የተገደድነው እነርሱ አንድም ሌላ ተቀባይነት ሊኖረው የሚችል አማራጭ  ባለማቅረባቸው ነው”

ሁኔታው ባለበት ከቀጠለና አሜሪካ ተገቢውን ምላሽ ካልሰጠች ብራዚል ተጨማሪ የታክስ ጭማሮ ለማድረግ ታቅዳለች። እንግዲህ ሁኔታው የአሜሪካን የጥጥ ተጽዕኖ አድራጊ ወገን የሚወጥር ሲሆን በአንጻሩ ግን በብዙ ሚሊዮን ለሚቆጠሩት የአፍሪቃ ገበሬዎች የተሥፋ ምክንያት የሚሆን ነው። በኦክስፋም ግምት የድጎማው መወገድ ቢሣካ ታላቅ አስተዋጽኦ ነው የሚኖረው። የጥጥ ዋጋ በዓለም ገበያ ላይ እስከ 14 በመቶ ገደማ ሊያድግ ይችላል። በዚሁ የአፍሪቃ ጥጥ አምራች ገበሬ ገቢም ከፍ ይላል ማለት ነው። ቢሆን ፍትሃዊ የንግድ ሁኔታን በማስፈኑ ጥረት ምንኛ ጠቃሚ ዕርምጃ በሆነ ነበር።

Shanta Deverajan, Chefökonom der Weltbank für Afrika
ሻንታ ዴቫራጃንምስል DW

የዓለም ባንክ ሰሞኑን ባወጣው የያዝነው 2010 ዓ.ም. የአፍሪቃ የልማት አመላካች ዘገባ በይፋ ከታወቀው ሙስና ሌላ ጸጥ ያለ ገዳይ ወይም ጎጂ ሙስና ለልማት ጠንቅ ሆኖ መገኘቱን አመልክቷል። ይሄው የሙስና ዓይነት በኤኮኖሚው ወይም በፖለቲካው ዘርፍ እንደተለመደው ከፍተኛ ምዝበራ በሰፊው የሚወራበት አይደለም። ለምሳሌ በሥራ ሰዓት የመምሕራን በትምሕርት ቤት አለመገኝት፣ የሃኪሞች ከሆስፒታል መቅረት፣ የተሳሳቱ መድሃኒቶችን ማከፋፈልና ፈሣሽ ማዳበሪያዎችን  ለድሃ ገበሬዎች ማደል በአፍሪቃ ውስጥ አጥፊ ተጽዕኖውን እያሳየ ነው።

በዘንድሮው የአፍሪቃ ልማት ጠቋሚ ዘገባ ላይ እንደተመለከተው ይህን መሰሉን ሙስና መታገሉም ቀላል ነገር ሆኖ አይገኝም። በአፍሪቃ አካባቢ የዓለም ባንክ ዋና የኤኮኖሚ ባለሙያ ሻንታያናን ዴቫራያን ስለዚሁ ሙስና ሲናገሩ፤

“የዚህ ጸጥ ያለ ሙስና ትርጉም ለድሃው ሕዝብ መሰጠት የሚገባው ማሕበራዊ አገልግሎት ቢከፈልበትም እንኳ አለመድረሱ ላይ ነው። ለምሳሌ አንድ ደሞዝ የሚከፈለው መምሕር ከክፍሉ ሲቀር ወይም እንደዚሁ የሚከፈለው ሃኪምም  በክሊኒኩ ሳይታይ ሲቀር ይህ አገልግሎትን ማጓደል ይሆናል። ግን በጥሞና ሲመለከቱት ሙስናን ነው የሚመስለው። ምክንያቱም የተከፈለው ሰው የሚጠበቅበትን ወይም የተመደበለትን ሥራ አይሰራምና!”

የዓለም ባንክ ጥናት ለምሳሌ በኡጋንዳ መምሕራን ከመደበኛ የሥራ ጊዜያቸው 27  በመቶውን በትምሕርት ቤት የማይገኙ ሲሆን ሃኪሞች 30  በመቶውን ጊዜ የሉም። በምዕራባዊው አፍሪቃ 45  በመቶው ማዳበሪያዎች አደገኛ ፈሣሾች ሲሆኑ በናይጄሪያ ከሚሰራጨው መድሃኒት ቢያንስ ግማሹ ደግሞ ትክክለኛ አለመሆኑ ተደርሶበታል። ታንዛኒያ ውስጥ ለምሳሌ በትምሕርት ቤት ያለው ሁኔታ አሳሳቢነት አጣዳፊ ዕርምጃ እንዲወሰድ አነሳስቷል። የትምሕርትና የሙያ ሥልጠና ሚኒስትሩ ጁማኔ ማጌምቤ በዓመቱ መጀመሪያ የአገሪቱን የትምሕርት ባለሥልጣናት በመላ ጠርተው የሚቀሩትን ብቻ ሣይሆን ጨርሶ ሳይሰሩ ደሞዝ የሚከፈላቸውን ሁሉ ተከታትለው ዕርምጃ እንዲወስዱ ትዕዛዝ አስተላልፈው ነበር።

“ሁለት የሞቱ መምሕራን ከደሞዝ ዝርዝር ላይ አለመሰረዛቸው የታየበት ሁኔታ ነበር። በዚሁ የተነሣም ታንዛኒያ ውስጥ በያንዳንዱ ትምሕርት ቤት እየሄደ የያንዳንዱን መምሕር ማንነት ለዳታ ስብሰባ የሚያዘጋጅ አንድ የሙያተኞች ቡድን አቋቁመናል። ይህ ደግሞ ያለንን ዳታ ለማስፋት የሚጠቅም ነው። የያንዳንዱን ማንነት፣ የት እንዳለና ምን እንደሚሰራ፤ እንዲሁም መቼ ጡረታ እንደሚገባ ወዘተ. ለመለየት ያስችለናል”

ሙስና በጥቅሉ፤ ዋነኛውና ሰወር ያለው ይህን መሰሉም በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም የተባበሩት መንግሥታትን የሚሌኒየም ግቦች ዕውን በማድረጉ ረገድ ከባድ መሰናክሎች ናቸው። የዓለም ባንኩ ባለሙያ ችግሩ ስር የሰደደ በቀላሉ የማይገፋ የፖለቲካ ችግር መሆኑን ቢረዱትም በሌላ በኩል ግን የመፍትሄ ዕድል አይጠፋም ባይ ናቸው።

“አንዱ መፍትሄ አበረታች ለውጥ ማድረግ ነው። በሩዋንዳ ለምሳሌ ሃኪሞች በከተቧቸው ሕጻናት ወይም በመረመሯቸው ነፍሰ-ጡሮች ቁጥር መጠን ተጨማሪ ክፍያ ያገኛሉ። ይህ ደግሞ ሃኪሞቹ በሥራ ቦታቸው እንዲገኙ ስለሚያደርግ እጅግ ጠቃሚ አስተዋጽኦ አለው። በሌላ በኩልም ዶቼ ቬለም እንደሚያደርገው ነዋሪዎች በስርዓቱ ላይ ተጽዕኖ ማድረግ እንዲችሉ የሚያስፈልጋቸውን መረጃ እንዲያገኙ ማብቃት ነው”

የሩዋንዳው ጥረት በአገሪቱ የሚሞቱትን ሕጻናት ቁጥር ለመቀነስ በጣም እንደረዳ ነው የሚነገረው። በዘገባው መሠረት አሃዙ ከ 2005 እስከ 2008 ባለው ጊዜ ውስጥ በሲሶ አቆልቁሏል። እናም በክፍለ-ዓለሚቱ በምሳሌነት የሚታይ ነው።

DW MM/HM