1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

"የእርጅና ቅናሽ" ሲቀር የመኪና ዋጋ ጨመረ

ሐሙስ፣ ግንቦት 15 2011

ኢትዮጵያ ያገለገሉ ዕቃዎችና ተሽከርካሪዎች ወደ ገበያው ሲገቡ ከሚከፈልባቸው ታክስ በእርጅናቸው ምክንያት የሚቀነሰውን የገንዘብ መጠን አስቀርታለች። የገቢዎች ሚኒስቴር ውሳኔውን በይፋ ለመኪና ነጋዴዎች ባያሳውቅም ተፅዕኖ ማሳደር ግን ጀምሯል። ገበያውን የሚያውቁ የቪትዝ ዋጋ እስከ 70 ሺሕ፤ የኮሮላ እስከ 90 ሺሕ ብር ሊጨምር ይችላል ብለዋል

https://p.dw.com/p/3Iyyn
Äthiopien Addis Abeba
ምስል DW/E. Bekele

ውሳኔውን መንግሥት ለነጋዴዎች በይፋ አላሳወቀም

የገቢዎች ሚኒስቴር ያገለገሉ ዕቃዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ከሚከፈልባቸው ቀረጥ በእርጅናቸው ምክንያት ይደረግ የነበረውን ቅናሽ አስቀርቷል። ውሳኔው በቀጥታ ከሚመለከታቸው መካከል ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች አስመጪዎች ውሳኔው በይፋ እጃቸው አልደረሰም። አውቶ ኢቲ የተባለው የተሽከርካሪ መገበያያ ድረ-ገጽ መሥራች እና ባለቤት አቶ እዮብ ከበደ የገቢዎች ሚኒስቴር ውሳኔ ለገበያው "ዱብ እዳ ሆኗል" ሲሉ ይናገራሉ። "አገር ውስጥ መኪና ያስገቡ ሰዎች በአዲሱ ቀረጥ እንዲቀርጡ እየተደረገ ነው። ዛሬ ጉምሩክ ብትሔድ [መኪና አስመጪዎች] በአዲሱ ነው የምትስተናገዱት ተብለው መኪና እንዳይወጣ ተይዟል" የሚሉት አቶ እዮብ ቀደም ብለው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ ተሽከርካሪዎች ላይ ጭምር አዲሱ ውሳኔ ተፅዕኖ ማሳደሩን ተናግረዋል።

የገቢዎች ሚኒስቴር ውሳኔውን በይፋ ካላሳወቃቸው የተሽከርካሪ ነጋዴዎች መካከል አንዱ አቶ ኑረዲን ሬድዋን ናቸው። "በስሚ ስሚ ነው የሰማንው። ፎቶ የተነሳ ወረቀት ምናምን እንጂ ሙሉ መረጃው ወይም መመሪያው የለም" ሲሉ ይናገራሉ።

አቶ ሬድዋን የጠቀሱት እና በገቢዎች ሚኒስቴር ምኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ግንቦት 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ተፈርሞ የወጣ የተባለ ደብዳቤ በማኅበራዊ ድረ-ገፆች ሲዘዋወር ታይቷል። "የጸደቁ መመሪያዎች ስለመላክ" የሚል ርዕስ የተሰጠው ይኸው ደብዳቤ ለጉምሩክ ኮሚሽን የተላከ እንደሆነ ይጠቁማል። በደብዳቤው "ማንኛውም ያገለገለ ዕቃ ተሽከርካሪን ጨምሮ ወደ አገር ውስጥ በሚገባበት ጊዜ ቀረጥና ታክሱን ለመወሰን ምንም አይነት የእርጅና ቅናሽ አይደረግም።" የሚል ሐሳብ ተካቶበታል።

እስካሁን በነበረው በኢትዮጵያ መንግሥት አሰራር መሰረት የተሽከርካሪ ቀረጥ በመኪናው የሲሲ መጠን፣ በተመረተበት ጊዜ እና በተገዛበት ዋጋ ይተመናል። ከተመረተ አንድ አመት የሞላው ተሽከርካሪ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ከሚከፈለው ታክስ 10 በመቶ በእርጅና ሳቢያ ይቀነስለታል። ከተመረተ ሁለት አመት የሞላው ተሽከርካሪ የእርጅና ቅናሽ 20 በመቶ ነበር። ከሶስት አመት በላይ የሆናቸው ተሽከርካሪዎች ከሚከፈልባቸው ታክስ 30 በመቶ ቅናሽ ሲቀነስላቸው ቆይቷል።

Äthiopien Addis Ababa Bushaltestelle
ምስል DW/Eshete Bekele Tekle

ይኸ አሰራር በድንገተኛው ውሳኔ ሲቀየር በኢትዮጵያ ጎዳናዎች በብዛት የሚታየው ቪትዝ የተባለ መኪና ዋጋ በ70 ሺሕ ብር ገደማ፤ ኮሮላ በአንፃሩ 90 ሺሕ ብር ገደማ እንደሚጨምር አቶ እዮብ ተናግረዋል። አቶ እዮብ "ኢትዮጵያ ውስጥ ከድሮው በበለጠ ተሽከርካሪ የቅንጦት ነው የሚሆነው። አነስተኛ መኪና ከ500 ሺሕ ብር በታች አትገዛም። አንዲት ትንሽዬ መኪና 500 ሺሕ ብር ገዝቶ ሊጠቀም የሚችለው ምን ዓይነት ሰው ነው? ሲሉ ይጠይቃሉ።አቶ ኑረዲን በበኩላቸው በዚህ ውሳኔ ምክንያት "አሁን ገበያ ላይ ያሉት መኪኖች ዋጋ ይጨምራል" ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በቅርቡ ከአምስት አመት በላይ ያገለገሉ መኪኖች ወደ ገበያው እንዳይገቡ ልታግድ ትችላለች።  የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች "የሚያስከተሉትን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳትን ለመቀነስ" በተዘጋጀ ረቂቅ የውሳኔ ሐሳብ ላይ ይመለከታቸዋል ካላቸው ጋር በትናንትናው ዕለት ውይይት አካሒዷል። አቶ እዮብ በኢትዮጵያ ተሽከርካሪ በመገጣጠም እና ያገለገሉትን ከውጪ አገራት ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ መሳተፋቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።ረቂቅ የውሳኔ ሐሳቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቼ እንሚቀርብ የተረጋገጠ ነገር የለም። አቶ እዮብ ግን በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ሒደቱ ተጠናቆ ሥራ ላይ ሊውል ይችላል የሚል ግምት አላቸው።

እሸቴ በቀለ 

ተስፋለም ወልደየስ