1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእስራኤላዉያን-ኢትዮጵያዉያን የቀጠለ ተቃዉሞ

ረቡዕ፣ ግንቦት 5 2007

እስራኤላዉያን-ኢትዮጵያዉያን አይሁዶች ይደርስብናል ያሉትን የዘር መድሎ በመቃወም የሚያደርጉትን የአደባባይ ሠልፍ እንደቀጠሉ ነዉ። ከትናንት በስቲያ በወደብ ከተማይቱ ሐይፋ በመቶዎች የተገመቱ ሠልፈኞች አደባባይ ወጥተዉ የዘር መድሎዉን አዉግዘዋል።

https://p.dw.com/p/1FPQI
Israel Tel Aviv Protestaktion äthiopische Juden Ausschreitungen
ምስል Reuters/Baz Ratner

እስራኤላዉያን-ኢትዮጵያዉያን አይሁዶች ይደርስብናል ያሉትን የዘር መድሎ በመቃወም የሚያደርጉትን የአደባባይ ሠልፍ እንደቀጠሉ ነዉ።ከትናንት በስቲያ በወደብ ከተማይቱ ሐይፋ በመቶዎች የተገመቱ ሠልፈኞች አደባባይ ወጥተዉ የዘር መድሎዉን አዉግዘዋል። ሰላማዊ ሆኖ መጠናቀቁ የተነገረለት ሰልፍ በፖሊስና በተለያዩ አካባቢዎች ይፈፀምብናል ላሉት አድሎ መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ያሳሰበ ነበር። እስራኤላዉያን ኢትዮጵያዉን የሁዲዎች በተከታታይ የተቃዉሞ ሠልፍ ካደረጉ በኋላ የእስራኤል መንግሥት ባለሥልጣናት ተወካዮቻቸዉን አነጋግረዉ ነበር።የሐገሪቱ ፕሬዝደንትም የሠልፈኞቹን ጥያቁ ተገቢነት ጠቁመዉ ነበር።

ኢትዮጵያዊ ቤተእስራኤላዉያን ወደናፈቋት «ሀገራቸዉ» ከገቡ አንስቶ የተለያዩ አንዳንዴም ያልጠበቋቸዉ ነገሮች እንደገጠሟቸዉ ዉስጥ ዉስጡን ይነገር ነበር። ከሳምንታት በፊት በኢየሩሳሌምና በቴልአቪብ ከተሞች ያካሄዱት የተቃዉሞ ሰልፍም ድብቁን ጉዳይ አደባባይ አወጣዉ። ኢትዮቤተእስራኤላዉያኑ ያሰሙት አድልዎ ይቁም የሚል ቁርጥ ያለ ተቃዉሞም የእስራኤል መንግሥት ትኩረት የነፈገዉ ጉዳይ መሆኑን እንዲያምን አደረገ። ለዚህ መነሻ የሆነዉ ደግሞ የደንብ ልብስ እንደለበሰ በሁለት ነጭ እስራኤላዉያን ፖሊሶች ጥቃት የተፈፀመበት ኢትዮጵያዊ እስራኤላዊ ወታደር ነበር። ወታደሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጠርተዉ አነጋግረዉታል። እሱን ማሳያ አድርገዉ አደባባይ ለተቃዉሞ የወጡትን ቤተእስራኤላዉያን ተወካዮችንም እንዲሁ። እስካሁን ግን በተግባር የተደረገ ለዉጥ ሥለመኖሩ ምንም አልተሰማም።ትናንት በእስራኤል የወደብ ከተማ ሐይፋ የተካሄደዉ የቤተእስራኤላዉያኑ ሰልፍም ምላሹ በቶሎ እንዲሰጥ የሚያሳስብ ከኢየሩሳሌምና ቴልአቪቩ ሰልፍ የቀጠለ ነዉ ይላሉ የማኅበረሰቡን ጉዳዮች ከሕግ አኳያ የሚያንቀሳቅሰዉ ጠበቃ የተሰኘዉ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ፈንታሁን አሰፋ ዳዊት።

Israel äthiopische Juden
ኔታንያ ከተማ የሚኖሩ ኢትዮቤተእስራኤላዉያንምስል Getty Images
Benjamin Netanjahu und Damas Pakada
ጠ/ሚ ኔታንያሁና ጥቃት የደረሰበት ኢትዮቤተእስራኤላዊዉ ወታደርምስል picture-alliance/AA/Haim Zach

ለሰሞኑ የኢትዮቤተእስራላዉያን የፀረ ዘረኝነትና አድልዎ ሰልፎች ምክንያት የሆነዉ ቤተእስራኤላዊ ከደበደቡት የእስራኤል ፖሊሶች መካከል ቀዳሚዉ ዱላ ሰንዛሪ ፖሊስ ከሥራዉ እንዲሰናበት በአዛዡ መወሰኑንም አቶ ፈንታሁን አሰፋ ዳዊት ገልጸዉልናል። ሆኖም ከሥራ መባረር ብቻ ሳይሆን ሕግ ፊት ቀርቦ ቅጣት እንዲቀበል መጠየቃቸዉንም አመልክተዋል። አቶ ፈንታሁን በሥራ አስኪያጅነት የሚመሩት ጠበቃ ድርጅት ከሕግ ጉዳዮች በተጨማሪ ከሌሎች ቤተአስራኤላዉያን አኳያ ሲታዩ ጥቅሞችና እድሎቻቸዉ ዉሱን የሆኑትን ኢትዮጵያዊ ቤተእስራኤላዉያን በትምህርትም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ተሳትፏቸዉ ልቆ ያለዉን አጋጣሚ ሁሉ የሚጠቀሙባቸዉን መንገዶች ለማመቻቸትም የሚሠራ መሆኑን ከእሳቸዉ ለመረዳት ችለናል። እስራኤል ዉስጥ እዚያዉ የተወለዱ ከ50 ሺህ የሚበልጡትን ጨምሮ 135,500 ገደማ የሚገመቱ ኢትዮጵያዊ ቤተእስራኤላዉያን እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ