1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእስራኤልና ፍልስጤም መበቃቀል

ሰኞ፣ ሰኔ 30 2006

የዘመነ-ዘመናቱ ፀሎት፤ ድርድር፤ የዲፕሎማሲ ጥረት ብዙዎች ብዙ ጊዜ እንዳሉት«ከልብ እና ፍትሐዊ» ሥላልሆነ---ሠላም የለም።ከልብ የሚደረገዉ ፖለቲካዊ መደባባት፤ ወታደራዊ መገዳደል፤እና መበቃቀል ግን ጥንትም-ድሮም ዘንድሮም አለ።

https://p.dw.com/p/1CXUX
ምስል DW/A. Samara

የእስራኤልና የፍልስጤም መሪዎች ቫቲካን ድረስ ተጉዞዉ ለሠላም ፀልየዉ ነበር።ፕሬዝዳንት ሼሞን ፕሬዝና ፕሬዝዳንት ማሕሙድ አባስ የሸምጋዮችን ሐሳብ እንደሚቀበል መሪ፤ እንደ-ሠላም ወዳድ ፖለቲከኛ፤ለፈጣሪ እንደሚገዛ አስተዳዳሪ በጋራ-መፀለይ-ለሠላም ቃል መግባታቸዉ በተስማ በሰወስተኛዉ ሳምንት ግን፤ ሔብሮን፤ጋዛ፤እየሩሳልም ደም እየጎረፈ እስከሬን ይለቀምባቸዉ ያዘ።ጋዛ-ምዕራባዊ ዮርዳኖስ ወንዝዳርቻ በቦምብ-እየወረደባቸዉ ይወድማሉ፤ ሰዉ እየታፈስ-ይታጎርባቸዋል።ደቡባዊ እስራኤል የሮኬት አረር ይጤስባታል።የእስራኤል ፍልስጤሞች የመበቃቀል ዑደት የዝግታችን ትኩረት ነዉ-ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

ሰኔ-12 2014 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያን አቆጣጠር ነዉ) ሰወስት አይሁድ-እስራኤላዉያን ወጣቶች ጉሽ ኤትፅዮን ከተባለዉ አካባቢ መታገታቸዉ ተሰማ።የእሥራኤል ባለሥልጣናት አጋቾቹ የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊ ቡድን የሐማስ አባላት መሆናቸዉን ለመናገር ለበቀል እርምጃም አላመነቱም።ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ዋናዉ ናቸዉ።

«ከእገታዉ ጥቂት ጊዜ በኋላ እገታዉን የፈፀሙት የሐማስ አሸባሪዎች መሆናቸዉን ተናግሬ ነበር።ዛሬ ደግሞ የእስራኤል የሥለላ አገልግሎት ይሕን መጥፎ ወንጀል የፈፀሙትን የሁለት ሰዎች ሥም አትሟል።»

ወጣቶቹ መታገታቸዉ ከተነገረበት-የእስራኤል የሥለላ ድርጅት ሁለት ፍልስጤማዉያንን በአጋችነት መወንጀሉን በይፋ እስካስታወቀበት ደርስ-ሁለት ሳምንት ተቆጥራል።ጠቅላይ ሚንስትሩ ኔታንያሁ እንዳሉት የሥለላ ድርጅታቸዉ መረጃ መታተሙ መረጃዉ ይፋ ከመሆኑ በፊት የተናገሩትን ለማረጋገጥ እንጂ አጋቾቹ-ኋላም ገዳዮቹ የሐማስ አባላት ለመሆናቸዉ መረጃ-ማጣቀስ መጠበበቅም አላስፈለጋቸዉም።

ወጣቶቹ ከታገቱበት-የእስራኤል የሥለላ ድርጅት በአጋጅነት የወነጀላቸዉን ፍልስጤማዉንን ሥም በይፋ እስካስታወቀበት ጊዜ በነበረዉ ሁለት ሳምንት፤ ኔታንያሁ ያዘመቱት ጠንካራ ጦር አምስት ፍልስጤማዉያንን ገድሏል፤በርካታ አቁስሏል።ከስወስት መቶ ሐምሳ በላይ ፍልስጤማዉንን አስሯል።

Jerusalem Palästinenser Proteste Ausschreitungen 03.07.2014
ምስል DW/A. Samara

ከሔብሮን እስከ-ጋዛ የሚገኙ የፍልስጤም መንደሮችን፤ የእርሻ ማሳዎችን፤መደብሮችን፤ መኖሪያ ቤቶችን አዉድሟል።«ከፈለገን» አሉ ኔታንያሁ በእሥራ-ሰባተኛዉ ቀን-«እርምጃዉ እስከምንፈልግበት» ድረስ ይቀጥላል።

«የእስራኤል መከላከያ ሐይል በቅርብ ቀናት ዉስጥ ጋዛና እዚሕም የሚገኙ የሐማስ ታላሚዎችን (እየመታ) ነዉ።እስፈላጊ ከሆነ-እስፈላጊ እስከሆነበት ድረስ ዘመቻዉን እናስፋፋለን።»ዘመቻዉ ቀጠለ።በመሐሉ የታገቱት ሰወስት እስራኤላዉያን ወጣቶች ተገድለዉ አስከሬናቸዉ ሔብሮን አጠገብ ተጥሎ ተገኘ።የእስራኤል ሕዝብ-በግድያዉ ቁጣ፤ ሐዘን፤ የበቀል ዛቻዉን ሲገልጥ የፖለቲካ ተንታኞች ደግሞ የወጣቶቹን ገዳይ ማንነት፤ የግድያዉን ዓላማና የመዘዙን እንዴትነት ያስተትኑ ነበር።በጀርመን የአረብ ዓለም ጉዳይ ጥናት ተቋም ሐላፊ ፕሮፌሰር ጉንተር ማየር አንዱ ናቸዉ።

«ማገት አንድ ነገር ነዉ።መግደል ግን ፍፁም የተለየነዉ።ግድያ መጥፎ መዘዝ እንደሚያስከትል፤እስራኤል በሐማስ ላይ ጠንካራ አፀፋ እርምጃ እንደምትወስድበት ሐማስ በትክክል ያዉቃል።ሥለዚሕ የእነዚሕ ወጣቶችን መገደል ሐማስ የሚፈልገዉ አይደለም።»

ሐማስ ፈለገዉም፤ አልፈለገዉ ወጣቶቹ ተገድለዋል።ወጣቶቹ ተገደሉም- ታገቱ-ወንጀለኛዉን ከንፁሁ፤ ታጣቂዉን ከሠላማዊዉ ፍልስጤማዉ የማይለየዉ የእሥራኤል ምሕረት የለሽ የሐይል እርምጃ አልተቋረጠም።

ከአምስት ሺሕ የሚበልጡ ፍልስጤማዉያን እስራኤል ወሕኒ ቤት ዉስጥ ታጭቀዋል።ሰወስቱ ወጣቶች ከታገቱ-መገደላቸዉ እስከተነገረበት በቆጠረዉ እስራ-ስምንት ቀን ዉስጥ ደግሞ እስራኤል ስድስት መቶ ፍልስጤማዉያንን አስራለች። ሰባት ገድላለች።የቆሰለዉ ብዙ ነዉ።ወትሮም የመከራ ኑሮ-የሚገፋዉ ፍልስጣማዊ በተለይ የጋዛ ነዋሪዋሪ የነበረቺዉ ጥሪት ወድማለች፤ተላዉሶ መስራት አይችልም። ከመታሰር፤ ከመገደል መቁሰል ከተረፈ በምግብ-መጠለያ እጦት መሰቃየት ግዱ ነዉ።የመብት ተሟጋቾች የእስራኤልን እርማጃ «ጅምላ ቅጣት» ይሉታል።

ጅምላ ቅጣቱ-በአረመናዊ የብቀላ ቅጣት ታጀበ።የሰወስቱ እስራኤላዉያን ወጣቶች አስከሬን መገኘቱ በተነገረ-በሠወስተኛዉ ቀን አንድ ፍልስጤማዊ ታዳጊ ወጣት እየሩሳሌም ዉስጥ ታግቶ፤ ተደብድቦ፤ ተገደሎ አስከሬኑ ወድቆ ተገኘ።አሥራ-ስድት ዐመቱ ነበር።የወጣቱ ግዳዮች፤ የሰወስቱን አይሁዳዉያን ወጣቶች ደም ለመበቀል ያለሙ አይሁዳዉያን መሆናቸዉን የጠረጠረ የለም።

Jerusalem Palästinenser Proteste Ausschreitungen 03.07.2014
ምስል DW/A. Samara

አሜሪካዊዉ የሟቹ ወጣት የእሕት ወይም የወንድም ልጅ ወደ እየሩሳሌም የተጓዘዉ ከሟች ጋር ለመጫወት፤ ዘመድ ወዳጆቹን ለመጠየቅ ነበር።15 ነዉ።የእሥራኤል ፀጥታ አስከባሪዎች ይዘዉ ቀጠቀጡት።

«ፊቴ ላይ ደበደቡኝ፤ በጣም ደበደቡኝ አቅሌን ስቼ እስክወድቅ ደበደቡኝ»

ሰወስቱን እስኤላዉያን ወጣቶችን በታገቱ ማግሥት ለእገታዉ ሐማስን ለመወንጀል የእስራኤል ባለሥልጣናት አላመነቱም።የሟቹን የፍልጤማዉዊ ወጣት ገዳዮች፤ ወይም የተራፊዉን ደብዳቢዎች ለመያዝ አይደለም እርምጃዉን ለማዉገዝ እንኳን ዕለታት ፈጅተዋል።የገዳዮችን ማንነት ለማወቅ ደግሞ ጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ እንዳሉት የመካከለኛዉ ምሥራቅ ብችኛ ሐያል ሐገር ገና «እያጣራች» ነዉ።

«የፖሊስ ምርመራ እንደቀጠለ ነዉ።ግድያዉን የፈፀሙት ወገኖችን አላማና ማንነት ገና አላወቅነዉም።ግን እናዉቀዋለን።ይሕን ወንጀል የፈፀሙት ምንም ቢሆኑ ለፍርድ እናቀርባቸዋለን።ግድያ፤በቀልና ለጥፋት መቀስቀስ በኛ ዴሞክራሲ ዉስጥ ሥፍራ የላቸዉም።»

ኔታንያሁ «የኛ» ያሉት ዴሞክራሲ በዓለም የፖለቲካ ሥርዓት ከመታወቁ ከብዙ ዓመታት በፊት አይሁዶች፤ ክርስቲያኖች፤ሙስሊሞች ከዚያ ምድር ከበቀበሉበት ጊዜ ጀምሮ እንደየሐይማኖታቸዉ አስተምሕሮ እየሩሳሌም ላይ ለዘመነ-ዘመናት ፀልየዋል።እንደ ፖለቲካዉ ወግ አንዳቸዉ ከሌላቸዉ ተወዳጅተዉ፤ አንዳቸዉ በሌላቸዉ ላይ ተመሳጥረዋል።እንደ ጦረኛ ለሥልጣን፤ ለግዛት ወይም ለእምነት የበላይነት ተጋድለዋል---ብዙ ሺሕ ዓመታት።

Jerusalem Papstbesuch Yad Vashem 26.05.2014
ምስል Reuters

የብዙ ሺሕ ዓመታቱ ፀሎት-ምሕላ፤የፖለቲካ መመሳጠሩም ሆነ፤ መዋጋት መገዳደሉ-ለዚያ ምድር ሠላም፤ ለሠወስቱ እምነት ተከታዮች ደሕንነትም በርግጥ የተከረዉ ነገር የለዉም።ኔታንያሁ የኛ ዴሞክራሲ ያሉትን ፖለቲካዊ ሥርዓት እንደምትከተል የሚነገርላት እስራኤል በ1948 ስትመሠረት አዲስ መልክና ባሕሪ የተላበሰዉን ጠብ ቁርቁስ በአሸናፊነት ለመወጣት የሠዉ ልጅ-አዕምሮ ሊፍጥረዉ የቻለዉ ምርጥ ጦር መሳሪያ፤ የሥለላ ጥልፍልፍ፤ ምርጥ ወታደር የተካፈሉበት ጦርነት ተድርጓል።

አንዴ-አይደለም፤ ሁለቴ ሰወስቴም አይደልም፤ አራቴ ከባድ ጦርነቶች ተደርገዋል። በመቶ ሺሕ የሚገመት ሕዝብ-አልቋል።በሚሊዮን የሚቆጠር ተሰዷል።በቢሊነ-ቢሊዮናት ዶላር የሚቆጠር ሐብት ንብረት ወድሟል።ባንድ በኩል እስራኤልን እስካፍጫዋ እያስታጠቀች በሌላ በኩል እስራኤልን ከአረቦች እስታርቃለሁ የምትለዉ ዩናይትድ ስቴት ለግራ-አጋቢ መርኋ የምታወጣዉ ገንዘብም ለእስራኤል አረቦች ከምታስታጥቀዉ ጦር መሳሪያ ወጪ ብዙ አይተናነስም።

የዩናይትድ ስቴትስ መሪዎች ሥልጣን በያዙ ቁጥር እስራል-አረቦችን ማስታረቅ-ብሎ አባባልን የየበዓለ ሲመታቸዉ ንግግር ማድመቂያ ካደረጉት ብዙ አመታት አስቆጠሩ።እስካሁን የመጨረሻዉ ቃል ገቢ ባራክ ኦባማ ናቸዉ።የመጨረሻ የሠላም ጥረት ዘዋሪ ጆን ኬሪ።ፕሮፌሰር ማየር እንድሚሉት የኬሪ የሠላም ጥረት ከሳቸዉ በፊት የነበሩ ብዙ ዲፕሎማቶች እንደሞከሩት ብዙ ጥረቶች ሁሉ ሞቷል።

Mahmoud Abbas mit Tariq Khdeir in Ramallah 07.07.2014
ምስል Reuters

«የሠላም ሒደቱ ሞቷል።ኔታንያሁ ገና ከመጀመሪያዉ ጊዜ ጀምሮ በግልፅ ተናግረዉ ነበር።የሠላም ሒደቱን የፍልስጤሞች መንግሥት እንዲመሠረት እስራኤልን የሚገፋፋ ነዉ በማለት ዉድቅ አድርገዉት ነበር።በዚሕም ምክንያት የኬሪ ጥረት ባለፈዉ ግንቦት እንዲጨናጎል (ኔታንያሁ) ሁሉንም ነገር አድረገዋል።ባሁኑ ሠዓት የሠላም ሒደት የለም።ይሕ ደግሞ (በሐይል በተያዙት ግዛቶች) የአይሁድ ሠፈራ መንደሮችን ለመገንባት የሚደረገዉን እንቅስቃሴ ለሚደግፉት ጥሩ አጋጣሚ ነዉ።የሐገር ዉስጥ ጉዳይ ሚንስሩ እንዳስታወቁትም የሠፈራ መንደር ግንባታዉ ተጠናክሮ ይቀጥላል።»

አንጋፋዉ የእስራኤል ፖለቲከኛ ሼሞን ፔሬስ በመጨረሻ የፕሬዝዳት ዘመነ-ሥልጣናቸዉ ለሠላም ፀሎት ወደ ቫቲካን የተጓዙት የሠላም ሒደቱ እንደከሸፈ እያወቁ ነበር።ቫቲካን ላይ ግን ሠላም ፀሎትን ብቻ ሳሆን ፅናት-መስዋዕትነትን እንደሚጠይቅ አስታወቁ።«ሠላም ዝም ብሎ አይገኝም።መስዋዕትነት መክፈልና ሰጥቶ-መቀብልን ይጠይቃል።ሰላም ከሌለ ጎዶሎ ነን።»

ከያሲር አረፋት ሞት በኋላ እስራኤል-አሜሪካኖችን ማሳመን፤ አረቦችን ከጎናቸዉ ማሠለፍ ቀርቶ ፍልስጤሞችን እንኳ ማስተባበር ያቃታቸዉ ማሕሙድ አባስም ወትሮም ለይስሙላ የተጀመረዉ የሠላም ሒደት ጨርሶ መሞቱን ያዉቁታል።ለፈጣሪ እንደሚገዛ መሪ ግን ቫቲካን ዉስጥ ለሠላም ፀለዩ።«ፍትሕዊ ሠላም፤ለሕዝባችን ሠብአዊነት የተከበረበት ኑሮና ነፃነትን ለማስፈን እንሻለን።»

Polizeikontrollen in Jerusalem 02.07.2014
ምስል DW/K. Shuttleworth

ሼሞን ፔሬስ ወደ እስራኤል፤ ማሕሙድ አባስ እስራኤል ወደ ምትቆጣጠረዉ ምዕራባዊ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ በየፊናቸዉ ተመለሱ።ቫቲካን ድረስ ያጓዛቸዉ የሠላም ፀሎት-እየሩሳሌም ላይ ለዘመነ ዘመናት እንደተደረገዉ ፀሎት ሁሉ፤ በእስራኤላዉያኑ ወጣቶች መታገት ሰበብ፤ ባፍጢሙ ሲደፋ ፔሬስ ሥልጣናቸዉን እስረክበዉ የጡረታ-ዘመናቸዉን አንድ ሁለት-ይቆጥሩ፤ ማሕሙድ አባስ ከሐማስ ጋር የመሠረቱትን አዲስ ካቢኔ የሚያጠናክሩበትን ብልሐት ያዉጠነጥኑ ነበር።

የዘመነ-ዘመናቱ ፀሎት፤ ድርድር፤ የዲፕሎማሲ ጥረት ብዙዎች ብዙ ጊዜ እንዳሉት«ከልብ እና ፍትሐዊ» ሥላልሆነ---ሠላም የለም።ከልብ የሚደረገዉ ፖለቲካዊ መደባባት፤ ወታደራዊ መገዳደል፤እና መበቃቀል ግን ጥንትም-ድሮም ዘንድሮም አለ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ