1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእስራኤል ምርጫና የመካከለኛዉ ምስራቅ ሠላም

ሰኞ፣ የካቲት 9 2001

ጠቅላይ ሚንስትር ይትሳቅ ራቢን እና ሊቀመንበር ያሲር አረፋት በፕሬዝዳት ቢል ክሊንተን ሸምጋይነት በ1993 የሰላም ዉል መፈራረማቸዉ፣ከካፕ ዴቪዱ ስምምነት በሕዋላ እነ ሬጋን የገፉት ሽምግልና እነ ሙባረክ ያቀጨጩት የሰላም ድርድር የማንሰራራቱ ተስፋ ነበር

https://p.dw.com/p/GvRI
ኔታንያሁምስል AP

የፍልስጤሙ ፕሬዝዳት ማሕሙድ አባስ በቅርቡ ለአዉሮጳ ሕብረት ምክር ቤት እንዳሉት እስራል ከፍልስጤሞች ጋር ሰላም ካወረደች ከ57 የአረብ-ሙስሊም ሐገራት በሰላም የመኖር ዋስትና ታገኛለች።አባስ ሽትራስቡርግ ከመግባታቸዉ ከሳምንት በፊት ረመላሕ ላይ ያነጋገሯቸዉ የዩናይትድ ስቴትሱ ልዩ መልዕክተኛ ጆርጅ ሚቼል ወደ መካካለኛዉ ምሥራቅ የሔዱት ሰዉ የሚጭር-የሚያቀጣጥለዉን ጦርነት ማስወገድ አይገድም ከሚል እምነት ጋር ነዉ።የሚቼል እምነት ተልዕኮ፣ የአባስ ተማፅኖ ለዘመናት እያበበ-የሚከስመዉ የሰላም ተስፋ ቢያንስ እስኪከስም የማበቡ ጭላንጭል መሆን-አለመሆኑ ሳይለይ እስራኤሎች መረጡ።ነገ-ሳምቱ።የምርጫዉ ዉጤት፣ መነሻ፣ እንድምታዉ ማጎልመሻ፣ የሰላም ተስፋ-ቀቢፀ ተስፋዉ መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።
ድምፅ

Nahost Wahlen Tzipi Livni Isreael Wahlkampfveranstaltung der Kadima
ሊቭኒምስል AP

ሙሳ አቡ አሊ የስልሳ-አራት አመት አዛዉት ናቸዉ።በዘር-አረብ-በዜግነት እስራኤላዊ።በሙያ ፀጉር አስተካካይ።ደቡባዊ እየሩሳሌም፣ ቤይት ሳፋፋ መንደር ይኖራሉ።በምርጫዉ ዋዜማ ከፀጉር ቤታቸዉ ጎራ ያለዉ ጋዜጠኛ፣ ጠየቃቸዉ። «በነገዉ ምርጫ ድምፅ ይሰጣሉ» አይነት ጥያቄ።በጭራሽ-አሉ።መቀሳቸዉን ማንቀጫቀጩን አቁመዉ።ከጠሉም።

«አልመርጥም፣ እኔ አልመርጥም፣ ባለቤቴ አትመርጥም።ወንድ ልጄ፤ ሴት ልጄም አይመርጡም። ለአይሁዶችም ሆነ ለአረቦች ድምፄን በጭራሽ አልሰጥም።ሁሉም ሁል ጊዜ ቃል ይገባሉ።ቃላቸዉን ግን አያከብሩም።እነሱ ወሬ፣ ወሬ፣ ወሬ ብቻ ነዉ።የተቀየረ ነገር የለም።»

ከሁለተኛዉ የአለም ጦርነት ፍፃሜ ጀምሮ አሜሪካ-እንግሊዝ-ፈረንሳይ ሶቬቶች-ለ-እና በ መካከለኛዉ ምሥራቅ የታታሩ፤-ያስወሰኑ፣ የተዋጉ፣ ያስታጠቁ፣ የሸመገሉት፥የአረብ እስራኤሎች ዉጊያ፥ ግጭት ዲፕሎማሲ ተጎራባች ሕዝቦችን በሰላም ለማኖር፣ በዉጤቱም የአለምን ሠላም ለማስከበር ከነበረ በርግጥ-በፀጉር ቆራጩ ቋንቋ ሁሉም-ሁሌም አወሩት እንጂ አላደረጉትም።

እርግጥ ነዉ የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳት ጂሚ ካርተር፤ የግብፁ አቻቸዉ አንዋር አል ሳዳት እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ሜናሔም ቤገን በ1978 (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ካምፕ-ዴቪድ ላይ ያሉ-የፈረሙት እስከዚያ ዘመን በወሬ-የቀረ የሳተዉን ሥላም ለእዉን ያቃረበ መስሎ ነበር።

ቤገን የሰላም ዉሉን ሲፈርሙ «አያቶቻችን ፒራሚዶችን ለመገንባት ብዙ ደክመዋል አሉ።እኛ ደግሞ እነሱ ከደከሙት በላይ ደክመን እነሱ ከሰሩት በላይ ሠራን።» አሉ። ስምምነቱ ሰላሳኛ አመት ዘንድሮ ሲዘከር የቤገንን መንበር የሚተካዉ ፖለቲከኛ ማንነት፤ የመንግሥቱን መርሕ እንዴትነት የሚበይኑት በማክሰኞዉ ምርጫ የሰወስተኝነቱን ደረጃ የያዘዉ የቀኝ የፅንፈኛዉ የእስራኤል ቤይትኑ ፓርቲ መሪ ናቸዉ። አቪጎር ሊበርማን።

የቀድሞዉ የዳንስ ቤት ዘበኛ ሊበርማን ከቤገን ጋር የትዉልድ ሐገር ይጋራሉ።ሶቬት ሕብረትን። እስራኤል ከመመስረቷ በፊት የብሪታንያን ይዞታዎችን በቦምብ ያጋይ፣ አረቦችን ይገድል የነበረዉን ኢርጉን የተሰኘዉን ጨንካኝ ፅንፈኛ ሸማቂ ቡድን ይመሩ፣ ከነፃነት በሕዋላ አረቦችን ለማጥፋት ይፎክሩ፤ ይታገሉ፣ የነበሩት ቤገን የኋላ ኋላ አረቡን ሳዳትን ለመሳም፤ የሰላም ዉል ለመፈረም የወሰኑት ፅንፈኛ መርሕ፤ ምግባርቸዉ፥ ንቀት-ጥላቻቸዉ ለሐገር-ሕዝባቸዉ እንደማይበጅ በመረዳታቸዉ እንደነበር-የትዉልድ ሐገር፥ምናልባት አፍ መፍቻ ቋንቋ ከሚጋሯቸዉ ሊበርማን እኩል የሚያዉቀዉ ያሁን ፖለቲከኛ ጥቂት ነዉ።

ከሊበርማን የፀረሰዉ-የቤገን የኋላ በጎ-አስተምሕሮት አሳይሆን ለዉጤት ያልበቃዉ ፅንፈኝነት መሆኑ ነዉ ዚቁ።ሊበርማን በቀደም እንዳሉት ከፍልስጤሞች ጋር የሚደራደር መንግሥትን አይቀየጡም። ሙሳን የመሳሰሉ አረብ-እስራኤሎችና ፅዮናዊነትን የማይቀበሉ አይሁዶችን ደግሞ ሕገ ወጥ ማለቱ ብቻ በቂ አይደለም አሉ።
ድምፅ

«ሕገ ወጥነት ነዉ ብሎ ማዉገዝ ብቻዉን በቂ ነዉ ብዬ አላምንም።ከዚሕ በተጨማሪ የዜግነት መብታቸዉም ሊገፈፍ ይገባዋል የሚል ተስፋ አለኝ።ታማኝነት ከሌለ ዜግነት ሊኖር አይገባም።ይሕ በሕግ መደንገግ አለበት።»

አንዋር አሳዳት የካፕዴቪዱን ስምምነት ከመፈረማቸዉ ከዘጠኝ ወራት በፊት ለእስራኤል ፓርላማ ባደረጉት ንግግር ከእንግዲሕ ጦርነት የለም።ደም መፋሰስ የለም ብለዉ ነበር።ሳዳት ያሉትን ሲሉ ስምምነቱንም ሲፈርሙ ከድፍን አረብ የሚገጥማቸዉን ቁጣ ተቃዉሞ አጥተዉት አልነበረም።እንደ ወታደር የተዋጉ-ያዋጉት እንደ ምክትል ፕሬዝዳት እንደ ፕሬዝዳትም ያዘዙት ተደጋጋሚ ጦርነት ፋይዳ እንደሌለዉ በማወቃቸዉ-እሳቸዉ ያወቁትን ሌሎቹ አረቦች ሲያዉቁት ቁጣዉ እንደሚበርድ በማሰባቸዉ ነበር-እንጂ።

ሳዳት ሕወታቸዉን የገበሩለትን የሰላም ዉል ያጫረዉን ቁጣ የማብረዱ፤ ድርድሩ ከሌሎቹ ጋርም እንዲደረግ አረቦችን የመገፋፋቱ፤ እስራኤል-አሜሪካኖችን የማግባባቱ አቅም፤ ሐላፊነት፣ የናስር-ሳዳት መንበር ወራሾች ፋንታ በሆነ ነበር።ሆስኒ ሙባረክ ሌላዉን አረብ ከፋፍለዉ፤ ሕዝባቸዉን እየረገጡ እስራኤል፣ ፍልስጤም፣ አሜሪካ፣ አዉሮጶችን ሻርም አልሼክ እየተቀበሉ ሲሸኙ እድሜያቸዉን አገባደዱ።

ጠቅላይ ሚንስትር ይትሳቅ ራቢን እና ሊቀመንበር ያሲር አረፋት በፕሬዝዳት ቢል ክሊንተን ሸምጋይነት በ1993 የሰላም ዉል መፈራረማቸዉ፣ከካፕ ዴቪዱ ስምምነት በሕዋላ እነ ሬጋን የገፉት ሽምግልና እነ ሙባረክ ያቀጨጩት የሰላም ድርድር የማንሰራራቱ ተስፋ ነበር።አረፋት «የጀግኖች ሰላም» የተሰኘዉን ዉል ፈርመዉ ፍልስጤም ሲገቡ የሐማስና የሌሎች አክራሪ ድርጅቶችን መሪዎችን አቅፈዉ እየሰሙ ነበር ድጋፋቸዉን የሸመቱት።

ማሕሙድ አባስ አንድ ፍልስጤምን አንድ ሳያደርጉ-ሐምሳ-ሰባት መንግሥታት አንድ ይሆናሉ እያሉ ባዶ ተስፋ ይዘምራሉ።ድርድሩን አንድ እርምጃ ፈቅ ሳያደርጉ ሥለ ነፃ መንግሥት ያወራሉ።እንደ ደፈጣ ተዋጊ፤ እንደ ወታደር ሲዋጉ፤ እንደ ጄኔራል ሲያዋጉ የጦርነትን ዘግናኝ ዉጤት የሚያዉቁት ይሳቅ ራቢን እንደ ፖለቲከኛ የሰላም ዉል ሲፈርሙ «በቂ ደም ፈሷል» ብለዉ ነበር።«ከእንግዲሕ «በቃ።»

በአስከፊዉ ጦርነት ወቅት እስራኤል አሜሪካ ይሉ የነበሩት ቤንያሚን ኒትንያሁ የጦርነትን መጥፎ ገፅታ በርግጥ እንደ ራቢን ኖረዉበት አያዉቁትም።ራቢንን የሚተካ የእስራኤል ፖለቲከኛ ራቢን የተሰዉለትን ጅምር-የሰላም እቅድ ያመክናል ብሎ መገመት ግን ከባድ ነበር።ከእንደ እስራኤል ይልቅ እንደ አሜሪካ የሚናገሩት ኒትንያሁ በ1996 የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ሥልጣን ሲይዙ ጅምሩን እቅድ አሽቀንጥረዉ ጣሉት።አሁን ደግሞ የጠቅላይ ሚንስትርነቱ ሥልጣን የኔ ነዉ-ይላሉ።
ድምፅ

«በፈጣሪ ድጋፍ የሚቀጥለዉ የእስራኤል መንግሥት መሪ እሆናለሁ።ጥሩ፥ ሠፊ መሰረት ያለዉ የተረጋጋ መንግሥት ማዋቀር እንደምችል እርግጠኛ ነኝ።ቃል እንደገባሁት በመጀመሪያ ከኛ የብሔረተኛ ቡድን አባላት ጋር እነጋገራለሁ።ከዚያ ቀጥሎ በቅርቡ ቃል እንደገባሁት በሕዝቡ ዉስጥ ያሉ ሐይላትን በሙሉ ለማስተባበር ከቀኞቹ ፅዮናዉያን ጋር እነጋገራለሁ።

በማክሰኞዉ ምርጫ የኒትንያሁን ሊኩድ ፓርቲን ባንድ መቀመጫ በልጦ የመጀመሪያዉን ሥፍራ የያዘዉ የካዲማ ፓርቲ መሪ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዚፒ ሊቭኒ የወደፊት መሪዋ እኔነኝ ባይ ናቸዉ።
ድምፅ
«አሁን ያለዉ ተገቢዉን ማድረግ ነዉ።የእስራኤል ሕዝብን ምርጫ ማክበር ነዉ።ባሁኑ ወቅት ለእስራኤል የሚገባዉን ማድረግ ነዉ።በተለተይ ደግሞ ፀጥታን በማስከበሩ መስክ፥ ከዉጪም ከዉስጥም የሚገጥሙ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሐብታዊ ፈተናዎችን ለመወጣት መጣር እና በኛ መሪነት ትልቅ ጥምር መንግሥት መመስረት ነዉ።»

Abbas im Straßburger Europaparlament
አባስምስል AP

ራቢን ይመሩት ከነበረዉ ከለዘብተኛዉ ሌበር ፓርቲ ከረር፣ ኒትንያሁ ከሚመሩት ሊኩድ ለስለስ የሚል መርሕ የሚከተለዉን የፖለቲካ ማሕበር የሚመሩት ሊቪኒ የተመኙት ከሆነላቸዉ እንደ አርያል ሻሮን በሐይልም በድርድርም ብለዉ ከፍልስጤሞች ጋር የተጀመረዉን ድርድር ለመቀጠል ቃል ገብተዋል።ቃል መርሐቸዉ ከፕሬዝዳት ኦባማ መስተዳድር የሚያግባባቸዉ አይነት ነዉ።

ግን እንዴት? ሊቪኒ ትልቅ-ያሉት-ጥምረት ከኒትንያሁ ፓርቲ ጋር ለማድረግ ያቀዱትን ነዉ። ኒትንያሁ መደራደርን አይደለም የእስራኤል ደሕንነት አሳልፎ የሚሰጥ ንቅናቄ ካሉት ሐይል ጋር አብሮ መስራቱንም አይፈቅዱም። የእስራኤል መንግሥት «አንጋሽ» የሚባሉት የሊበርማን ፅንፈኛ አቋም ከሊቪኒ ይልቅ ለኒትንያሁ የሚቀርብ ነዉ።ኒትንያሁ ዳግም የጠቅላይ ሚንስትር ከሆኑ ደግሞ-አቋማቸዉ ግልፅ ነዉ።
ድምፅ ፭
«የእስራኤልን ፀጥታ ለድርድር ያቀርባል፥ሕዝቡን ይሰነጥቃል፥ ብዬ የማስበዉ ንቅናቄ አካል መሆን አልችልም።ከዚሕም በተጨማሪ ከ1967ቱ (ጦርነት በሕዋላ) ካሉት ወሳኝ መስመሮች የመዉጣት መርሕን ይቀበላል፥እናም ለወደፊቱ የእየሩሳሌምን አንድነት ላደጋ ያጋልጣል ብዬ ከማስበዉ ንቅናቄ ጋር ልሻረክ አልችልም።»

ሳዳትና ቤገንን የሰላም ዉል ያፈራረሙት ጂሚ ካርተር «በመጨረሻ አሸነፍን» አሉ።ለሰላም የመጀመሪያዉን እርምጃ።-ለረጅሙና ላስቸጋሪዉ ጉዞ የመጀመሪያዉ እርምጃ።»እርምጃዉ ሳይደገም ዛሬም በሰላሳ አመቱ የሐማስ-እስራኤል ተኩስ አቁም፤ የፍልስጤም እስራኤል ድርድር፤ የእስራኤል ሶሪያ ንግግር፣ የአባስ ተስፋ፥ የሚቼል እምነት ተልኮ ሙሳ እንዳሉት የሌላ አመት፥ ሌላ ወሬ-መሆኑ ነዉ ቀቢፀ-ተስፋዉ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ZPR, Chronicle of the Century

NM, AA