1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእስራኤል ምርጫ ውጤት እና አስተያየት

ረቡዕ፣ መጋቢት 9 2007

የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የሚመሩት የሊኩድ ፓርቲ በትናንቱ ዕለት የተካሄደው ምክር ቤታዊ ምርጫ አሸናፊ ሆነ። ከ120 የምክር ቤት፣ ክኔሴት መንበሮች ሊኩድ 30 ዎቹን ፣ ዋነኛው ተፎካካሪያቸው ይትዝሀቅ ሄርሶግ የመሩት የተቃውሞ የመሀል ግራው የጽዮናውያኑ አንድነት ትብብር 24 ፣ የዐረባውያኑ ፓርቲዎች የመሠረቱት

https://p.dw.com/p/1EspU
Israel Wahlen 2015 Netanjahu Jubel
ቤንያሚን ኔታንያሁምስል Reuters/N. Elias

ጥምረት 14 መንበሮችን ፣ የሞሼ ካህሎን የኩላኑ ፓርቲ ደግሞ 10 መንበሮችን አግኝተዋል።አንዱም ፓርቲ አብላጫውን ድምፅ ባለማግኘቱ ኔታንያሁ በቀጣዮቹ ሳምንታት አንድ ጥምር መንግሥት እንደሚመሠርቱ አስታውቀዋል።  

የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከጠንካራ ፉክክር በኋላ ለድል የተጓዙበት ጎዳና ቀላል እንዳልነበረ የፖለቲካ ተንታኞች አመልክተዋል። የሊኩድ ፓርቲያቸው ከ120 የእስራኤል ምክር ቤት፣ ክኔሴት መንበሮች 30 አግኝቶዋል። ይትዝሀቅ ሄርሶግ የሚመሩት የተቃውሞው የሰራተኛ ፓርቲ እና የቀድሞዋ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሲፒ ሊቭኒ የሚመሩት የሀትንዋ ፓርቲ ባንድነት የፈጠሩት የጽዮናውያኑ አንድነት ትብብር ጥምረት በምርጫው 24 መንበሮችን በማግኘት ሁለተኛው ጠንካራ ኃይል ሆኖዋል። ይህን ውጤት ተከትሎ የሊኩድ ፓርቲ መሪ ኔታንያሁም በቀጣዮቹ ሁለት ወይም ሶስት ሳምንታት አንድ የቀኝ ክንፍ ጥምር መንግሥት ለማቋቋም ጥረት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል። ሄርሶግም ሆኑ በምርጫው ሶስተኛ ጠንካራ ኃይል መሆን 14 መንበሮችን ያገኘው የዐረባውያኑ ፓርቲዎች ጥምረት ከሊኩድ ጋ ተጣምረው የመስራት ፍላጎት እንደሌላቸው ከወዲሁ ግልጽ አድርገዋል። ሀገሪቱን ለአራተኛ ጊዜ በጠቅላይ ሚንስትርነት ይመራሉ የሚባሉት ኔታንያሁ፣ ሞሼ ካህሎን የሚመሩት እና 10 መንበሮችን ያገኘው የኩላኑ ፓርቲ በጥምሩ መንግሥት እንዲጠቃለል ለማግባባት እንደሚሞክሩ ተሰምቶዋል።

Wahlen in Israel Herzog und Livni
ሲፒ ሊቭኒ እና ይትዝሀቅ ሄርሶግምስል Reuters//Ratner

የሊኩድ ፓርቲ የጽዮናውያን አንድነት ትብብር ጥምረት ጠንካራው ፉክክር ከገጠመው በኋላ፣ ኔታንያሁ በምርጫው ዕለትም ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ከእስራኤል ሕዝብ መካከል 20%ን የሚሸፍኑት ዐረብ እስራኤላውያን የሳቸውን መመረጥ ለማከላከል በብዛት ድምፅ ሊሰጡ ወጥተዋል ሲሉ ያሰሙት ማስጠንቀቂያ መጨረሻ ሰዓት ላይ ብዙ መራጭ እንዳስገኘላቸው ተሰምቷል። ምክንያቱም ለብዙ አይሁዳውያን የዐረብ እስራኤላውያን በሀገሪቱ ፖለቲካ ላይ የመወሰን መብትን መቀበል አሁንም አዳጋች ነውና።

Israel Wahlen Arabische Liste
የዐረባውያኑ ፓርቲዎች ጥምረትምስል Reuters/A. Awad

በመጨረሻዎቹ የምርጫ ዘመቻ ቀናት የሊኩድ እና የሌሎች ቀኝ አክራሪ ፓርቲዎች ደጋፊ መራጮችን ለመቀስቀስ በማሰብ ኔታንያሁ ቀደም ሲል ከፍልሥጤማውያን ጋ በሚደረግ የሰላም ድርድር ላይ ይዘውት የነበረውን አቋም በመቀየር በሳቸው አመራር አንድ ነፃ የፍልሥጤም መንግሥት እንደማይመሠረት አስታውቀዋል።

ይሁንና፣ ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸው የጀርመን አረንጓዴ ፓርቲ አባል ፎልከር ቤክ እንደሚሉት፣ የእስራኤል ፀጥታ ሊጠበቅ የሚችለው የሁለት መንግሥቱ ምሥረታ ገሀድ ሲሆን ነው።

« የእስራኤል ፀጥታ ዋስት ለዘለቄታው ሊረጋገጥ የሚችለው ወደ ፍልሥጤማውያን መንግሥት ምሥረት የሚያመራ አንድ የሰላም ሂደት ሲኖር ብቻ ነው ብዬ አምናለሁ። ይኸው የሰላም ሂደት፣ ማለትም፣ ወደፊት የሚደረጉ የሰላም ድርድሮች ግን ለእስራኤል የፀጥታ ዋስትና ተጨባጭ ዘዴዎችን ማካተት ይኖርባቸዋል። »

ኢራን የኔታንያሁን በምክር ቤታዊ ምርጫ ማሸነፍ በፍልሥጤማውያን ወይም በዐረቡ ዓለም ዘንድ የሚያስገኘው ፋይዳ የለም ስትል አጣጥላዋለች።

የፍልሥጤማውያኑ ፕሬዚደንት ማህሙድ አባስ የሁለት መንግሥት ምሥረታን ሀሳብ ከሚቀበል ማንኛውም የእስራኤል መንግሥት ጋ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን የአባስ ቃል አቀባይ ከምርጫው ውጤት በኋላ አስታውቀዋል።

በዩኤስ አሜሪካ ምክር ቤት በሬፓብሊካውያን ግብዣ ካለ ፕሬዚደንቱ ስምምነት ከጥቂት ሳምንታት በፊት ንግግር ላሰሙት ለኔታንያሁ በዛሬው ዕለት የደስታ መግለጫ የላኩ የመጀመሪያዎቹ ፖለቲከኞች ሬፓብሊካውያን መሆናቸው ተሰምቷል።

Washington Barack Obama Benjamin Netanjahu
ምስል picture-alliance/AP Photo/C. Dharapak

ኔታንያሁ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው የሚቀጥሉበትን ጉዳይ አስመልክተው በዋሽንግተን የሚገኘው የብሩኪንግስ የፖለቲካ ጥናት ተቋም ተንታኝ ማይክል ኮፕሎቭ እንደሚገምቱት፣ ውጥረት የሚታይበትን የኔታንያሁን እና የዩኤስ አሜሪካ መንግሥት ግንኙነትን ማሻሻሉ አዳጋች ይሆናል።

« ኔታንያሁ ከዋይት ሀውስ ጋ ያለውን ግንኙነት ሁሉ አበላሽተዋል። ኋይት ሀውስ የኔታንያሁ አድናቂ አይደለም። ኔታንያሁም የፕሬዚደንት ኦባማ አድናቂ አይደሉም። እና ከኋይት ሀውስ ጋ ያለው ግንኙነት እንደራደ ይቀጥላል። እና ኔታንያሁ እና አሜሪካዊው ፕሬዚደንት በቀሪው የኦባማ የሥልጣን ዘመናቸው በቀጥታ የሚነጋገሩ አይመስለኝም።

አርያም ተክሌ

ተክሌ የኋላ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ