1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእስራኤል ታሳቢ ጠቅላይ ሚንስትር መርሕና ሰብዕና

ሰኞ፣ የካቲት 16 2001

አክራሪ-ፅንፈኝነቱ ለዉጤት እንዳልበቃ የተረዱት አርያል ሻሮንን የመሳሰሉ አንጋፋ ፖለቲከኛ የቀድሞ ጄኔራሎችም የመሰረቱትን የፖለቲካ ፓርቲ ጥለዉ ሌላ እስከማዋቀር መድረሳቸዉ አይተዋል።አይተናልም።

https://p.dw.com/p/Gzjw
ኔትናያሁምስል AP

23 02 09

በ1996 (ዘመኑ በሙሉ እንደ አዉሮጳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ለጠቅላይ ሚንስትርነት እንደተመረጡ ጥቅል መርሐቸዉ በሰወስት አይሆኖችም ላይ እንደሚያጠነጥን-ግልፅ አደረጉ።የጎላን ኮረብታዎች ለቅቀን መዉጣት-አይሆንም።በየሩሳሌም ባለቤትነት መደራደር አይሆንም።በየትኛዉም ቅድመ ሁኔታ ድርድር-አይሆንም።ቤንያሚን-ቢቢ እንደ ደጋፊዎቻቸዉ ኔታንያሁ።ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋላችሁ። ዳግም ለጠቅላይ ሚንስትርነት የታጩት የእስራኤል ቀኝ አክራሪ ፖለቲከኛ መርሕ እንዴትነት የሥብዕናቸዉ ማንነት ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ አብራችሁኝ ቆዩ።
ድምፅ

ከ1948 ጀምሮ ከአረቦች ጋር በተደጋጋሚ የተደረገዉን ዉጊያ በግንባር ቀደምትነት የመሩ-ያስተባበሩ፥ የእስራኤል ፖለቲከኞች የጦርነቱን አማራጭ ለሕዝብ-ሐገራቸዉ ሰላም ደሕንነት እንዳልበጀ የተረዱበት ዘመን ነበር-1990ዎቹ።የሶቬት ሕብረት ኮሚንስታዊ ጎራ የፈረሰበት፥ በእስራኤል የቅርብ ወዳጅ-ደጋፊ በአሜሪካ የሚመራዉ የምዕራቡ ካፒታሊስት የበላይነቱን ያረጋገጠበት ዘመን።

ቀኝ ፅንፈኛዉ የነፃነት አርበኛ ሜናሕን ቤገን ከአንዋር አሳዳት ጋር የሰላም ዉል በተፈራረሙ በአስራ-ሰወስተኛዉ አመት፥ግራ ዘመሙ የቀድሞ እዉቅ ጄኔራል ይትሳቅ ራቢን ከያሲር አረፋት ጋር ሌላ የሰላም ዉል ሲፈራረሙ ደም-እንባ መፈሳሱ በቃ ብለዉ ነበር።
ድምፅ
«የብዙ ጦርነቶች እዉቅ አርበኞች ነን።ዛሬ ደግሞ እኛ ከእንግዲሕ ደም እና እንባ ማፈሰሱ መቆም አለበት እንላለን።አሁን እኛ የምንመኘዉ ዘላቂና ትርጉም ያለዉ ሠላም ነዉ።ለሠላም ሥንል ችግሮችን ለመጋፈጥ ዝግጁ ነን።»

ችግሩ በጦር ሜዳ እንደሚያዉቁት የሚጋፈጡት አይነት ግን አልነበረም።ራቢን የሳዳት እጣ ደረሳቸዉ።ከብዙ ጦርነት የዳኑ የተረፉት ጀግና ሰላም ባሉ፥ በዉጊያ አዉድ፥ በሰላም መድረክም ነፃነት ደሕንነቱን ባስከበሩለት ወገናቸዉ ባደባባይ በጥይት ተደበደቡ።የራቢን ሞት፥ የተከታዮቻቸዉን ጥረት አጉልብቶ ዳር እንዲዘልቅ የሚመኙትን ሠላም ለማፅናት ይረዳ-ይጠቅማል ነበር የብዙዎች ግምት ተስፋ።

በርግጥም ከዋሽንግተን ክሊተን፥ ከረመላሕ አረፋት፥ ከእየሩሳሌም ፔሬስ የሚገፉት የሰላም ጥረት ከዉጤት አፋፍ በደረሰበት በዚያ ዘመን እስራኤልን የሚመራዉ ፖለቲከኛ የራቢንን መርሕ-አለማ የሚጋራ እንጂ የገዳያቸዉን እምነት የሚደግፍ ይሆናል ብሎ መገመት ከባር ነበር።መጋቢት-1996 ግን ያልተገመተዉ ሆነ።በዚያ አመት በተደረገዉ ምርጫ የአራባ-ሰባት አመቱ ቀኝ አክራሪ ፖለቲከኛ አሸነፉ።ቢንያሚን ኔታንያሁ።

እስራኤል ከተመሠረተች ወዲሕ የተወለደ፥ የሥደት-እንግልት፥ የጦር ሜዳ ዉጊያ፥ መከራዉን ኖሮበት የማያዉቅ ፖለቲከኛ የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ስልጣን ሲያዝ ኔታንያሁ የመጀመሪያዉ ሆኑ።በአርባ-ሰባት አመታቸዉ የመሪነቱን ሥልጣን በመያዛቸዉም የመጀመሪያ ወጣት ጠቅላይ ሚንስትር ናቸዉ።እዚያዉ እስራኤልና አሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች ተምረዋል።እንግሊዘኛን እንደ እስራኤሎች ሳይሆን እንዳሜሪካኖቹ መናገሩን ይወዳሉ።የምርጫ ዘመቻቸዉም የእስራኤሎች ሳይሆን የአሜሪካኖች አይነት ነበር።
ድምፅ (ሙዚቃ)


ሐምሌ-4 1976።ሳዬሬት መትካል የተሰኘዉ የእስራኤል ልዩ ኮማንዶ ጦር ሁለት መቶ ሥልሳ መንገደኞችን ያሰፈረዉን የእስራኤል አዉሮፕላን ጠልፈዉ ኢንተቤ-ዩጋጋንዳ አዉሮፕላን ማረፊያ ያሳረፉት ፍልስጤማዉን አጋቾች በሙሉ ደምስሶ-ታጋቾቹን አስለቅቋል።ለረጅም ጊዜ ሲጠና፥ ሲሰላ ቆይቶ ዉድቅት ላይ የተጀመረዉ ዘመቻ ለድል ሲበቃ ግን-የልዩ ጦሩ አዛዥ ሌትናንት ኮሎኔል ዮናታን (ዮኒ) ኔታንያሁ ተገድለዉ ነበር።

የኢንተቤዉ ዘመቻ ሥልት አርቃቂና የሳዬሬት መትካል አዛዥ የነበሩት ጄኔራል ኤሁድ ባራክ ፖለቲካዉን ሲቀየጡ የቀድሞ አዛዥ-አለቃቸዉን የራቢንን ሕልም፥ ምኞት ጅምር ዳር ለማዝለቅ ነበር።እንደ ብዙዎቹ ጦርነቶች ሁሉ ሥለ ኢንተቤዉ ዘመቻም ከወድማቸዉ መገደል ሌላ ያልተሳተፉበት ቤንያሚን ኔታንያሁ ግን ፖለቲካዉን የተቀየጡት በታላቅ ወድማቸዉ መገደል እንደ በገኑ ነበር።

የወድማቸዉ ሃያኛ ሙት አመት ሲዘከር የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ሲይዙም ከፖለቲካዉ መርሕ ይልቅ የበቀል-ጥማት እንደተጫጫናቸዉ ነበር።ለጠቅላይ ሚንስትርነት በተደረገዉ ዉድድር ዋና ተፎካካሪያቸዉ ሼሞን ፔሬስን ለማሸነፍ የቻሉት የፔሬስ መንግሥት የፍልስጤም አጥፍቶ ጠፊዎችን ጥቃት መቆጣጠር አልቻለም።እስራኤል በአሸባሪዎች እየተጠቃች ከአረፋት ጋር ይደራደራል በሚል ዋና ዋና ምክንያቶች ነበር።

ፔሬስ በሰዉጅ የተገደሉትን የራቢንን ሥልጣን ወርሰዉ አንድ አመት ያክል በቆዩበት ዘመነ-ሥልጣናቸዉ በርግጥም ተደጋጋሚ ያሸባሪ ጥቃቶች በእስራኤል ላይ ደርሰዉ ከሰላሳ የሚበልጡ አይሁዶችም ተገድለዉ ነበር።ኔታንያሁ ሥልጣን በያዙ በሰባተኛዉ ወር በሰወስት አይሆንሞች የተቀመረ-መርሐቸዉን ገቢር ለማድረግ እየሩሳሌም የሚገኘዉን ምዕራባዊ ዋሻ መክፈታቸዉ ያስቆጣዉ ፍልስጤም ከአስራኤል ጦር ጋር ተጋጭቶ-ሰባ ፍልስጤም ሲገደል፥ አስር የእስራኤል ወታደሮች ሞቱ።

ኔታንያሁ ከፍልስጤሞች ጋር የተጀመረዉን ድርድር ለማስቆም ሆን በለዉ የጀመሩት እርምጃ ይዞላቸዉ ድርድሩ በነበረበት ቀረ።ቃል-እንደገቡት የእስራኤልን ደሕንነት፥ የሕዝቧን ሰላም ማስከር ግን አልቻሉም።በዚያዘመን የዋይት ሐዉስ ቃል አቀባይ የነበሩት ጆ ሎክ ሐርት «አደገኛ ግራ አጋቢ ሰዉ ናቸዉ» ይላሉ ኔታንያሁን።«ዉሸታምና ወሬኛ ናቸዉ።ይናገራሉ፥ ሲናገሩ ግን ከአፋቸዉ የሚወጣዉ እዉነት መሆኑን ለማመን ይከብዳል።»

ኔታንያሁ በ1999ኙ ምርጫ በኤሁድ ባራክ ተሸንፈዉ ሥልጣን መልቀቅ ግድ ነበረባቸዉ።ማን-ምንም አለ ምን ግን በአስረኛ አመቱ ዘንድሮ እንደገና መጡ።የቀድሞ ተፎካካሪያቸዉ ፕሬዝዳት ሺሞን ፔሬዝ።አርብ።
ድምፅ
«ከተመረጡት የክኔሴት (የምክር ቤት) አባላት መካካል 65ቱ፥ አብላጫዉን የክኔሴት መቀመጫ የያዙት ማለት ነዉ፥ ባልደረባቸዉ የምክር ቤት አባል ቤኒያሚን ኔታንያሁ መንግሥት መመስረታቸዉን እንደሚደግፉት ገልፀዉልኛል።ሥለዚሕ በተሰጠኝ ሥልጣንና ሐላፊነት፥ እና በሐገሪቱ ሕግ መሠረት የምክር ቤት አባል ቢንያሚን ኔታንያሁ መንግሥት እንዲመሠርቱ ሐላፊነቱን ሰጥቻቸዋለሁ።»

ኔትናያሁ የአረብ-እስራኤሎች፥ ፅዩናዉያንን የሚቃወሙ አይሁዶች የዜግነት መብት መገፈፍ-አለበት የሚሉትን፥ ኦቪጋር ሊበርማንን የመሳሰሉ ፅንፈኛ ፖለቲከኞችን ከጎናቸዉ አሰልፈዋል።ለመጀመሪያ ጊዜ ጠቅላይ ሚንስትር ከነበሩበት እስካሁን በተቆጠረዉ ጊዜ በእድሜያቸዉ ላይ አስራ-ሁለት አመት ጨምረዉ-ስልሳ ደጃፍ ደርሰዋል።አክራሪ-ፅንፈኝነቱ ለዉጤት እንዳልበቃ የተረዱት አርያል ሻሮንን የመሳሰሉ አንጋፋ ፖለቲከኛ የቀድሞ ጄኔራሎችም የመሰረቱትን የፖለቲካ ፓርቲ ጥለዉ ሌላ እስከማዋቀር መድረሳቸዉ አይተዋል።አይተናልም።

በእስራኤል ፖለቲካዊ ሒደት ከፍተኛ ተፅኖ የምታሳርፈዉ የዩናይትድ ስቴትስ አዲስ መስተዳድርም የመካከለኛዉ ምሥራቅ ችግርን በድርድር ለማስወገድ መቁረጡን ጠንቅቀዉ ያዉቁታል።ባንፃራዊ መመዘኛ ለዘብተኛ የሚባሉት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ዚፒ ሊቪንን የመንግሥታቸዉ አካል ለማድረግ መመኮራቸዉ በእድሜም፥ በፖለቲካዉም የመብሰል፥ የአለምን ተጨባጭ እዉነት የመቀበላቸዉም ምልክት ሊሆን ይችላል።መርሐቸዉ ግን በቀደም እንዳሉት ያዉ ነዉ።
ድምፅ

አለማ-መርሐቸዉ መያዝ-መሳቱን በርግጥ ጊዜ ነዉ-በያኙ።ለካካለኛዉ ምሥራቅ ሕዝብ ግን ትናንት ዛሬ-ዛሬም ትናንት ነዉ።ሠላም-ይዘመራል።ጦር ይሰበቃል።በጎ-ይወራል አስከሬን ይታጨዳል።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ZPR,Wikipedia

Negash Mohammed