1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእነጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ክስ ተቋረጠ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 25 2010

የፌደራል አቃቤ ህግ በጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ እና ሰዓሊ አምሳሉ ገብረኪዳን ላይ ከፍቶት የነበረው ክስ መቋረጡ ታወቀ፡፡ ጋዜጠኛ ኤልያስ እና አምሳሉ ተከስሰው የነበረው አሁን በህትመት ላይ በማይገኘው “እንቁ” መጽሔት ላይ ታትሞ በነበረ ጽሁፍ ምክንያት “ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ተግባር ፈጽመዋል” በሚል ነበር፡፡

https://p.dw.com/p/2vQWT
Symbolbild Justiz Richter Gericht Richterhammer
ምስል picture-alliance/dpa/U. Deck

የክሱ ሂደት ከሁለት ዓመት በላይ ወስዷል

ከሁለት ዓመት በላይ ያስቆጠረው የጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ እና ሰዓሊ አምሳሉ ገብረኪዳን ክስ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ሲታይ የቆየ ሲሆን ተከሳሾቹ የመከላከያ ምስክር ለማቅረብ ለዛሬ ቀጠሮ ነበራቸው፡፡ ሆኖም ከሳሽ አቃቤ ህግ ባለፈው የካቲት ወር ክሱን በማቋረጡ ዛሬ ከክሱ ነጻ መሆናቸው ተነግሯቸዋል፡፡

ለክሱ መነሻ የሆነው ጽሁፍ “የተገነቡ እና እየተገነቡ ያሉ ሀውልቶች የማን እና ለማን ናቸው?” በሚል በ“እንቁ” መጽሔት በመጋቢት 2006 ዓ.ም በአምሳሉ ገብረኪዳን አማካኝነት የታተመ አስተያየት ነበር፡፡ በወቅቱ የመጽሔቱ ዋና አዘጋጅ የነበሩት አቶ ኤልያስ ለጽሑፍ መታተም ተጠያቂ ናቸው በሚል ከጸሀፊው ጋር አብሮ ተከስሷል፡፡ መጽሄቱን ያነበቡ የጅማ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ብጥብጥ አስነስተው 40 ሺህ ብር የሚገመት ንብረት እንዲያወድሙ ጽሁፉ ምክንያት እንደሆነ በክሱ ላይ ተጠቅሷል፡፡   

የአዲስ አበባው ዘጋቢያችን ዮሃንስ ገብረእግዚያብሔር ውሳኔውን አስመልክቶ ጋዜጠኛ ኤልያስን አነጋግሯል፡፡ ሙሉ ጥንቅሩን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ።  

ዮሃንስ ገብረእግዚያብሔር

ተስፋለም ወልደየስ

አርያም ተክሌ