1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

የኦሮሚያ እና የአማራ ክልሎች የ'ኤኮኖሚ አብዮት' እቅዶች

ረቡዕ፣ መጋቢት 20 2009

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በርካታ ፋብሪካዎች የሚያስተዳድር የአክሲዮን ማኅበር ማቋቋሙን ገልጧል።ፖለቲካዊ ተቃውሞ ገጥሞት የነበረው ክልል የሚያቋቁማቸው ፋብሪካዎች 'የኤኮኖሚ አብዮት' ለመቀስቀስና የሥራ አጥነት ለመፍታት ያለሙ ናቸው ተብሏል። የኤኮኖሚ ባለሙያዎች እና የተቃዋሚ ፖለቲከኞች ግን እቅዶቹ 'ግብታዊነት' ይስተዋልባቸዋል ሲሉ ይተቻሉ

https://p.dw.com/p/2aGDX
Mutter und Sohn Tannasee Baher Dahr Äthiopien
ምስል DW/Azeb Tadesse Hahn

የኦሮሚያና የአማራ ክልሎች የ'ኤኮኖሚ አብዮት' እቅዶች

ባለፈው ዓመት የከፋ ፖለቲካዊ ተቃውሞ የገጠመው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኦሮሚያ አቻውን መንገድ ተከትሏል። የክልሉ መንግሥት የብረታ ብረት እና ስሚንቶ ፋብሪካዎችን ጨምሮ 22 የማምረቻ ተቋማት የሚያስተዳድር ዓባይ ኢንዱስትሪ ልማት አክሲዮን ማኅበር የተሰኘ ኩባንያ ሊያቋቁም ማቀዱ ተሰምቷል። እቅዱ ከሰመረ ኩባንያው የብረታ ብረት ፣ የማዳበሪያ ፣ የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች የሰፋፊ እርሻዎች ባለቤትም ይሆናል ተብሏል። በእቅዱ መሠረትም እጅግ አነስተኛ የደን ሽፋን ባላቸው ደብረ ብርሐን እና የወልዲያ ከተሞች የእንጨት ፋብሪካዎች ይቋቋማሉ።

የአማራም ሆነ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልሎች አዲስ በሚመሰርቷቸው ኩባንያዎች «በሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች ሥራ ለመፍጠር» ማቀዳቸውን በተደጋጋሚ ገልጠዋል። የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ ክልሎቹን ለናጠው ፖለቲካዊ ተቃውሞ ምላሽ ለመስጠት የተጠነሰሱት እቅዶች በእርጋታ እና በጥናት መዘጋጀት ነበረባቸው የሚል እምነት አላቸው። የክልሎቹ እቅዶች «በቂ ጊዜ ተወስዶበት ተጠንተዋል ወይ?» ሲሉ የሚጠይቁት አቶ አብዱልመናን የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሊያቋቁም ያቀዳቸው 22 ድርጅቶች ብዙ ናቸው የሚል እምነት አላቸው። «ባለሐብቶቹ እነዚህ እቅዶች ላይ ገንዘባቸውን አፍስሱ ሲባሉ በቂ የሆነ መረጃ ተሰጥቷቸዋል ወይ?» የሚሉት አቶ አብዱልመናን እንዲህ አይነት ግዙፍ እቅዶች ለአክሲዮን ሽያጭ ሲቀርቡ አስፈላጊ ጥናቶች ሊደረጉ ይገባል ሲሉ ይሞግታሉ።

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በ25 በመቶ ባለቤትነት የሚያቋቁመው ኩባንያ አክሲዮን እየተሸጠ መሆኑን ሪፖርተር ጋዜጣ በዕለተ-እሁድ እትሙ አስነብቧል። ሁለቱም ክልሎች የሥራ ዘርፎቹ እና የሥራ ቦታዎቹ የተመረጡባቸውን ምክንያቶች፤ የኩባንያዎቹን የአመሰራረት እና የአስተዳደር ሁኔታ በጥልቀት የሚያትት ጥናትም ይሁን ዶሴ በይፋ ለሕዝብ ስለማቅረባቸው የሚታወቅ ነገር የለም። ባለፍ አገደምም ቢሆን ስለ 'ኤኮኖሚ አብዮት' የሚቋቋሙት ኩባንያዎች በመንግሥት እና የግሉ ዘርፍ ጥምረት (Public Private Partnership) የሚዋቀሩ ናቸው የሚሉ ድምፆች ይሰማሉ። የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፤ የመንግሥት ጉዳዮች ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ክልላቸው ስለሚያቋቁማቸው ኩባንያዎች በፌስቡክ ገፃቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ይኸንኑ ጠቁመዋል። የዓለም ባንክ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት መንግሥት እና የግሉ ዘርፍ በጥምረት የሚያከናውኗቸው ሥራዎች በአብዛኛው በመሠረተ-ልማት ላይ የሚያተኩሩ ናቸው።

Äthiopien Eröffnung Industriepark Industrial Park in Hawassa
ምስል DW/G. Tedla

ሁለቱም ክልላዊ መንግሥቶች ባለፈው ዓመት የከፋ ተቃውሞ እና ኹከት ከማስተናገዳቸውም ባሻገር ክልሎቹን በብቸኝነት ላለፉት 26 ዓመታት ያስተዳደሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥያቄ በዝቶባቸዋል። በተደጋጋሚ ውይይቶች እና ግምገማዎች ውስጥ የከረሙት የክልሎቹ የፓርቲ እና የመንግሥት ሹማምንት የገጠሟቸውን ፈተናዎች ለመወጣት የተከተሏቸው አካሔዶችም ሆኑ የመፍትሔ ሃሳቦች እጅጉን ተመሳሳይ ናቸው።

ሁለቱ ክልሎች የጀመሩትን የኩባንያ ምስረታ እና የአክሲዮን ሽያጭ የታዘቡት ተቃዋሚ ፖለቲከኛው አቶ ግርማ ሰይፉ መንግሥት «በምን ስርዓት ነው የእነዚህ አክሲዮኖች ሽያጭ የተካሔዱት?» ሲሉ ያጠይቃሉ። «በነበረው ሕዝባዊ መነሳሳት ችግሩ በኤኮኖሚ ተጠቃሚነት አለመኖር ነው የሚል የተሳሳተ ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።» ሲሉ የሚተቹት አቶ ግርማ አሁን በሚቋቋሙት ኩባንያዎች «የኦሮሚያንም ይሁን የአማራን ወጣቶች በአጠቃላይ ደግሞ ሕዝቡን» የሚጠቅም አይደለም ሲሉ አክለዋል።

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ካቀዳቸው 22 የሥራ ዘርፎች መካከል ፌዴራል መንግሥት ጀምሯቸው የተንገዳገዱ ይገኙበታል። የኢትዮጵያ መንግሥት በእድገት እና ለውጥ እቅዱ እገነባቸዋለሁ ያላቸው የስኳር እና የማዳበሪያ ፋብሪካዎች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ አልተጠናቀቁም። ኢትዮጵያ ውስጥ በአክሲዮን ግዙፍ የማምረቻ ፋብሪካዎች ለመገንባት የተደረጉ ሙከራዎች እምብዛም አልተሳኩም። አቶ አብዱልመናን የኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ያቋቋሟቸው ኩባንያዎች ከፊታቸው በርካታ ጋሬጣዎች ይጠብቋቸዋል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ። ባለፉት አስር አመታት ከ30 በላይ አክሲዮን የሚሸጡ ኩባንያዎች ተቋቁመው እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ አብዱልመናን «አምስት እና ስድስት ከሚሆኑት በቀር» ስኬታማ አለመሆናቸውን ያስታውሳሉ።  

Äthiopien Soldaten
ምስል picture-alliance/dpa/S. Morrison

ኢትዮጵያ የገጠማት ፖለቲካዊ ተቃውሞ እና ኹከት ገፊ ምክንያቶች ሥራ አጥነት እና ፍትኃዊ የኃብት ክፍፍል እጦት ናቸው ሲሉ ባለስልጣናቱ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣል። በተለይ ወጣቶች ላይ የሚበረታው ሥራ አጥነት አገሪቱ ከምትከተለው ኤኮኖሚያዊ ፖሊሲ ጋር ያለውን ግንኙነት ግን ለመናገር አልደፈሩም። አቶ ግርማ ሰይፉ የሁለቱ የክልል መንግሥታት ውሳኔ ኢትዮጵያ የምትከተለው ፖሊሲ ውድቀት ማሳያ ነው የሚል እምነት አላቸው። «የመሰረትንው የኤኮኖሚ ሥርዓት ሥራ ፈጥሮ የዜጎችን የኤኮኖሚ ተጠቃሚነት አላረጋገጠም የሚል አቋም ላይ የደረሱ ይመስለኛል።» የሚሉት አቶ ግርማ የኦሮሚያ እና የአማራ ብሔራዊ ክልሎችን የሚያስተዳድሩት የፖለቲካ ፓርቲዎች የትግራይ ሕዝቦች ነፃ አውጪ ግንባር (ሕውሓት)ን መንገድ መከተልን መርጠዋል ሲሉ ይነቅፋሉ።

በብሔራዊ ደረጃ በተለያዩ ጊዜያት ግዙፍ እና አማላይ የልማት እቅዶች ሲነደፉ እና ሲታቃዱ ታይተዋል። ባለፈዉ ዓመት በተለይ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ተቀስቅሶ ለበርካታ ወራት የዘለቀዉ ሕዝባዊ ተቃዉሞ፤ መንስኤዉ ሥራ አጥነትና ፍትኃዊ የሃብት ክፍፍል አለመኖር መሆኑን መንግሥት መግለፁ የእቅዶቹ ተግባራዊነት ጥያቄ ላይ የሚጥል ነዉ። አሁን በክልሎቹ በተናጠል የሚታየዉ «የኢኮኖኮሚ አብዮት» እንቅስቃሴስ ተገቢዉን መፍትሄ ማምጣት ይችል ይሆን? ይህም የሚጠየቅ ዋና ጥያቄ ይሆናል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ