1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦሮምያዉ ግድያ፤ ኤርትራ ትዉጣ መባሉ፤ ፖለቲካዊ አተካራ የበዛበት የዓለም ዋንጫ

ዓርብ፣ ኅዳር 16 2015

በኦሮምያ ስለቀጠለዉ ግጭት ጦርነት እና ግድያ ፤ የኤርትራ ጦር ከትግራይ እንዲወጣ ስለመጠየቁ፤ እንዲሁም ፖለቲካዊ አተካራ ስለበዛበት የኳታሩ የዓለም እግር ኳስ ግጥምያን በተመለከተ ሰሞኑን የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ላይ በርካታ አስተያየቶችን አስቀምጠዋል። እናም በዚህ ዝግጅት አስተያየቶቹን አሰባስበን ጨምቀን ይዘናል።

https://p.dw.com/p/4K1OE
Symbolbild I BigTech I Social Media
ምስል Mana Vatsyayana/AFP/Getty Images

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ሰሞኑን የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች በኦሮምያ ስለቀጠለዉ ግጭት ጦርነት እና ግድያ  ፤ የኤርትራ ጦር ከትግራይ እንዲወጣ ስለመጠየቁ፤ እንዲሁም ፖለቲካዊ አተካራ ስለበዛበት የኳታሩ የዓለም እግር ኳስ ግጥምያ ላይ በርካታ አስተያየቶችን አስቀምጠዋል። እናም በዚህ ዝግጅት አስተያየቶቹን አሰባስበን ጨምቀን ይዘናል።  

Social Media Apps | WhatsApp Facebook Twitter Instagram
ምስል Nasir Kachroo/ZUMA Press/imago images

በኦሮሚያ ክልል እየተስፋፋ ላለው ግጨት አስቸኳይ እልባት እንዲፈለግ ተጠይቋል። አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ (DW)የሰጡት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ (ኦፌኮ) አመራሮች በክልሉ ሰላምን ለማስፈን ዋነኛ ኃላፊነት ያለበት መንግስት የኅብረተሰቡን ደኅንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣም ጠይቀዋል። በድሉ ቤዛ የተባሉ የፌስ ቡክ ተከታታይ እንደሚሉት፤ ግለሰብን ከስልጣን ማውረድ ብቸኛ መፍትሄ ባይሆንም፤ይህ ሁሉ ህዝብ እያለቀ የኦቦ ሺመልስ በስልጣን መቀመጥ ይገርማል።

የሸዋ ጌጥ፤ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ ያስቀመጡት አስተያየት ደግሞ እንዲህ ይላል። በወለጋ ለሚታየዉ ጭፍጨፋ ሌላ ምክንያት እየተፈለገ ነው።  ላለፉት 4 ዓመታት ሴቶች ህጻናት አረጋዉያን ገበሬዎች ያለማንም ከልካይ በጅምላ ተጨፍጭፈዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ጭፍጨፋው ተጠያቂነት የሚያመጣበት ቀን እንደሚመጣ የገባቸው የጨፍጫፊው ወገኖች ለጭፍጨፋቸው ምክንያት በመፈለግና በሌላ ለማላከክ ላይ ታች ሲሉ እያየን ነው። ሆኖም በጭፍጨፋው እጃቸው ያለበት ሁሉ አንድ ቀን መጠየቃቸው አይቀርም። ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል።

ፋኖ በለው ኦነግ ወይም ኧሸባብ ሲሉ አስተያየታቸዉን የሚጀምሩት ራህሚት ያሴን የተባሉ ፋኖ በለው ኦነግ ወይም ኧሸባብ  የፈለገ ይሁን፤ መንግስት ባለበት ሀገር ይሄን ያህል ህዝብ ሲሞት ማየት ወላሂ በጣም ያሳዝናል። መቼ ይሆን ይህ ህዝብ ሰቆቃዉ አብቅቶ እፎይ ብሎ የሰላም አየር የሚተነፍሰው ፤ ሲሉ በጥያቄአስተያየታቸዉን ደምድመዋል።የወለጋው ጭፍጨፋ፤ የቴዲ አፍሮ ናዕትና «አረንጓዴ ዐሻራ»

መሪ አይውጣልሽ የተባለች ሀገር ሲሉ አስተያየታቸዉን የሚጀምሩት አህመድ ቱሃር አሚር ናቸዉ። እስኪ አሁን ምን ይባላል። እስኪ አሁን ለዚህ ምስኪን ህዝብ መቅደም ያለበት ቅንጡ ቤተ መንግሥት ወይስ ለመኖሩ ዋስትና የሚሰጠዉ መሪ፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል። አማረች ሙላት የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ ፤ ይህ ንፁኃን ደም ነገ ምን ያመጣብን ይሆን፤ ሲሉ ይጠይቃሉ። ይህ የንፁሐን ደም ምን ያመጣብን ይሆን? ለሁሉም ነገር ጊዜ አለዉ። የሀገር ሽማግሌዎች አባካችሁ ለሰላም ቁሙ። ለነገው ትውልድ እዳ አናሰረክብ ብለዋል።

Kenia Nairobi | Abkommen zwischen äthiopischer Regierung und Tigray Rebellen | Birhanu Jula und Tadesse Werede Tesfay
ምስል Thomas Mukoya/REUTERS

የኤርትራ መንግስት ጦር በተደረሰው የሰላም ስምምነት ላይ ዕንቅፋት እየፈጠረ መሆኑ የትግራይ ባለስልጣናት ገለፁ። ከሰላም ስምምነቱ ሳምንታት በኃላ ቢሆንም የኤርትራ ጦር በትግራይ ውስጥ እንዳለ፤ በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች ላይ በሚኖር ህዝብ የተለያዩ በደሎች እየፈፀመ ስለመሆኑ በህወሓት በኩል ተገልጿል። በሌላ በኩል በኢትዮጵያ መንግሥትና በህወሓት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት በተግባር በመተርጎም ላይ መሆኑን የትግራይ ኃይሎች ዋና አዛዥ ጀነራል ታደሰ ወረደ አስታዉቀዋል። ጀነራል ታደሰ በሰጡት ማብራሪያ በአሁኑ ጊዜ ተኩስ መቆሙን፤ ስለተደረሰው የሰላም ስምምነት ለትግራይ ኃይሎች ማስረዳትና ከውጊያ ቀጣናም የማራቅ ስራ መቀጠሉን በመቀጠል የውጊያ ግንባሮችን ማፍረስና ሰራዊቱንም ወደተቀመጠለት ስፍራ መውሰድ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

አያሌዉ ዳምጤ፤ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ እንደሚሉት፤ አታራግቡ እሳት ሲያራግቡት ይነዳል ይላሉ። መሐመድ አብዱ ይማም እንደሚሉት ደግሞ ቃል የተገባዉ ይከበራ መጀመርያ፤ ኤርትራ አታሳስብም፤ብትውድ በውድ ካልሆነ በግድ ህግ ታከብራለች ባይናቸዉ። መሻሊ አሰፋ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ በበኩላቸዉ፤ የኤርትራ ሰራዊት የትግራይን መሪት ለቆ ከወጣ ችግሩ በሰላም ይፈታል፤ ብለዋል።  

ብሩክ ያሲኖ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ ረሰም ያለ አስተያየት ነዉ ያስቀመጡት። የተለያዩ ተግዳሮቶች ከዚህም ከዚያም ሊገጥሙ እንደሚችሉ እሙን ነው። ነገር ግና ጦርነቱን ከማስቀጠል ከሚገጥሙት አንፃር ከታየ ቀላል ናቸው። ፅንፈኞች፤ በጦርነቱ አትራፊ ሚድያዎች፤ አክቲቪስቶች፤ፖለቲከኞችና ሌሎች፤ ተግዳሮት አይፈጥሩም ብሎ መጠበቅ እንዝህላልነት ነው። ለዚህ ስምምነት ያበቃው በመሬት ላይ ያለው ተጨባጭ ሚዛንና የህዝብ ስሜትን የሚለውጥ ታምራዊ አንዳች ነገር ካልተፈጠረ በስተቀር እያንዳንዷን አንቀፅ ወደተግባር ከማውረድ የተለየ አዋጭ ነገር ባለመኖሩ ባዘለም ባቀፈም ተፈፃሚነቱ ከሞላጎደል አይቀሬ ይመስለኛል፤ ሲሉ ጽፈዋል።ሃይማኖት ተቋማት የሰላም ጥሪ፤ በምዕራብ ኢትዮጵያ የዜጎች ጭፍጨፋ፤ በአማራ ከተሞች የሰዓት እላፊ

Symbolbild I BigTech I Social Media
ምስል Ozan Kose/AFP/Getty Images

አሸር ሳይድ፤ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ ፤ ሁሉም ጉዳይ በሠላም ይጠናቀቃል። የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያ ህዝብ፣ የኢትዮጲያ ህዝብ ከትግራይ ህዝብ አንዱ ሌላውን ከልቡ ይቅርታ ይጠይቃል። አንዱ ሌላውን ይከሳል፣ አንዱ ሌላውን ይረዳል እየደግፋል። የህዝባችን ቤተሰባዊ ትስስሩ ቀድሞ ከነበረበት እርከን ከፍ ብሎ በመከባበርና በመተባበር ያብባል። ይህ ምኞትና ተስፋ ብቻ አይደለም። ይህ ውሳኔ የማይሻርና የማይሸረሸር የዚህ ትውልድ የዘመን ቃልኪዳን ነው። ይህ ትውልድ አባቶቹ ያበላሹትን መንገድ ገንብቶ፣ ያፈረሱትን ቤት አበጅቶ እኩልነትን፣ ነፃነትና ሠላምን እያረጋገጠ ወደፊት ይገሰግሳል። ሀገሩን በልማት እየገነባ ህዝቡን ከችግር ያላቅቃል። ከአባቾቻችንና ከታላላቆቻችን የሚጠበቀው የታሪክ አደራ እነርሱ የመጡበት መንገድ ያስከተለውን ምስቅልቅልና ያስከፈለውን ዋጋ በመረዳት ይህን ዘመን ለዘመን ልጆች ማስረከብና መተው ነው። የነርሱን ዘመንና ልጆቻቸውን በልተው የነርሱን ቀጣዩን ትውልድ ሊበሉ ያሰፈሰፉ ወገኖች ቢበቃቸው እናመሰግናቸዋለን። ካልበቃቸው እንታገላቸዋለን። ሠላም ለኢትዮጵያና ለመላው የሰው ልጆች ሁሉ ይሁን ሲሉ አስተያየታቸዉን አብቅተዋል።

ባለፈዉ እሁድ የጀመረዉ ኳታር መዲና ዶሃ ላይ በድምቀት የጀመረዉ የዓለም እግር ኳስ ግጥምያ፤ ሳዑዲ አረቢያ ከፍተኛ ግምት የተሰጣት አርጀንቲናን 2 ለ 1 ፤ ማሸነፍዋ፤ ጃፓንም እንዲሁ ጀርመንን ሁለት ለአንድ መርታትዋ የኳስ ክብነቱ የተመሰከረበት ሆኖ ሰንብቷል ተብሎአል። ስፔን ኮስታሪካን 7 ለዜሮ መርታትዋ፤ ስፔን የግብ ጎተራ አገኘች ተብሎላታልም። ጀርመንን የፊታችን እሁድ የምትገጥማት ስፔን ኮስታሪካ ላይ ያሳየችዉን የግብ ቅርቻት የማድረግ ልማድ ጀርመን ላይ ስለመድገምዋ ቢያንስ የጀርመን ደጋፊዎች ጥርጣሬ አላቸዉ።  ከኳስ ባሻገር ፖለቲካዊ ጉዳዮች የተንፀባረቁበት የኳታሩ የዓለም የእግር ኳስ ግጥምያን አስመልክቶ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በርካታ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል።

ቃል ብቻ፤ የሚል መጠርያ ያላቸዉ አንድ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ አንድ አስተያየት አስቀምጠዋል። «የኢትዮጵያ ኑሮ እኛን 12 ለዜሮ እየመራን ነው።» ሲሉ።   ዛኪ ሃበሻ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ ፤ በዚህ ዓለም ዋንጫ ግጥምያ እስካሁን ፈረንሳይና ስፔን ያሳዩትን ብቃት የትኛዉም ብሔራዊ ቡድን ሲያሳይ አላየሁም ባይ ናቸዉ። ካሳሁን አማረ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ እንደሚሉት፤ ጃፓኖች ጀርመኖችን ድባቅ መተው እጃችንን በአፋችን አስጨነዋል ሲሉ በሳቅ የተሞላ ስዕል አያይዘዉ ለጥፈዋል።

Symbolbild I BigTech I Social Media
ምስል Nicolas Economou/NurPhoto/picture alliance

አቡኑ ዓለም ኧል አርቤል፤ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ «እውነት እየቆየች ትገናለች። የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን መደገፍ ትርፉ ሽንፈት ነዉ። ይህ ነዉ ጀርመንን የገጠማት።  ሁሉም የየሀገሩን ባህል እና እምነት ማክበር አለበት። ጀርመን ከማን በልጣ ነው ኳታርን ልትቃወም የቻለችው፡፡ እንደራሷ ልታይ ይገባት ነበር» ሲሉ አስተያየታቸዉን ደምድመዋል።

ኑረዲን ሰዒድ የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ ለጀርመን ሽንፈት ብቻ ሳይሆን ውርደትም ነው። የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ ጠበቃ ለመሆን እንጂ ኳስ ለመጫወት አልነበረም ወደ ሜዳ የገብት፤ ሲሉ አስተያየታቸዉን አብቅተዋል።  ኡም ፈራሀን የተባሉ የዓለም ዋንጫ ተከታታይ፤ የሚገርም ጨዋታ፤ የጃፓን በረኛ  ብዙ የጀርመን ግቦችን አምክኗል።  አይ የኳስ ነገር፤ ከጅምሩ በጃፓን ላይ የጎል ናዳ ሊወረድ መስሎኝ ነበር፣ ሲሉ አስተያየታቸዉን አስቀምጠዋል። ሊዲያ ሃበሻ በመጨረሻ እንዲህ አሉ፤ ተአምሩ እንደቀጠለ ነው የዘንድሮ የዓለም ዋንጫ፤ ትእግስቱን ይስጠን እንጂ ጉድ እናያለን፤ ብለዋል።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ