1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦባማ የአፍሪቃ ጉብኝት ፍፃሜ

ረቡዕ፣ ሰኔ 26 2005

የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ትናንት በሴኔጋል፣ በደቡብ አፍሪቃ እና በታንዛንያ ያካሄዱትን የአንድ ሣምንት ጉብኝታቸውን አጠናቀቁ። ኦባማ በጉብኝታቸው ወቅት በአህጉሩ ያለውን ግዙፍ የኤኮኖሚ ዕድል በማመልከት፣ ሀገራቸው በዚሁ ዘርፍ ከአፍሪቃ ጋ ግንኙነትዋን እንደምታስፋፋ አስታውቀዋል።

https://p.dw.com/p/191fz
ምስል Reuters

የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ በጉብኝታቸው ወቅት ለማጉላት የሞከሩት ሀገራቸው ከአፍሪቃ ጋ አዲስ የትብብር ዘመን እንደምትጀምር ነው። ኦባማ እንዳስረዱት፣ አዲሱ የትብብር ሞዴልም እንደ እስካሁኑ በልማት ርዳታ እና በድጋፍ ላይ ሳይሆን፣ በንግዱ እና በሽርክናው ላይ የተመሠረተ ይሆናል። አፍሪቃ « ለአፍሪቃውያን የምትመች አፍሪቃን መገንባት አለባት። በዚሁ ሂደት ላይ የኛ ስራ ሸሪኮች መሆን ነው ነበር ያሉት።  

«አሜሪካ በአፍሪቃ ጉዳይ ለብዙ አስርታት ተሳትፋለች። አሁን ግን ድጋፍ፥ የዉጪ ርዳታ ከመስጠት ወደ አዲስ ትብብር እየተሸጋገርን ነዉ።የአሜሪካና የአፍሪቃ አዲስ ወዳጅነት። ችግሮቻችሁን የማስወገድ እና የማደግ አቅማችሁን በማዳባር ላይ ያተኮረ የእኩያሞች ወዳጅነት። ጥረታችን ኑሯችንን በሚቀርፁ በሰወስት መስኮች ላይ ያተኩራል።(በሥራ) ዕድል፥ በዲሞክራሲ እና በሰላም።»

Afrika Textilindustrie Ghana
ምስል picture-alliance/dpa

እርግጥ፣ ዩኤስ አሜሪካ ከአፍሪቃ ጋ ያካሄደችው ንግድ ባለፈው አሠርተ ዓመት በእጥፍ ጨምሮዋል፣ ይሁንና፣ ቻይና በዚሁ ጊዜ ውስጥ ከአፍሪቃ ጋ ያካሄደችው የንግድ ልውውጥ በህያ እጥፍ አድጎ ነው የተገኘው። ቻይና ዋነኛዋ የአፍሪቃ የንግድ አጋር በመሆን ዩኤስ አሜሪካን በንግድ ሽርክና አልፋ ከሄደች ብዙ ጊዜ አልፎዋል።  ይህ በተለይ ኦባማ በመጨረሻ በጎበኙዋት ታንዛንያ ውስጥ ጎልቶ ይታያል። በዩኤስ አሜሪካ እና በታንዛንያ መካከል በ 2012 ዓም የተካሄደው የንግድ ልውውጥ 360 ሚልዮን ዩኤስ ዶላር ነበር፤  የቻይና እና የታንዛንያ ያደረጉት የንግድ ልውውጥ 2,5 ሚልያርድ ዩኤስ ዶላር ነበር። ቻይናውያኑ መሪዎች በሁለተኛው የሥልጣን ዘመናቸው ሰሞኑን ወደ አፍሪቃ ከሄዱት ኦባማ በፊት ነበር ወደ አአህጉሩ የተመላለሱት። ባለፈው መጋቢት  የቻይናው ፕሬዚደንት ዢ ጂን ፒንግ ታንዛንያን ጎብኝተዋል። ይህ ሲታሰብ ታድያ አሁን ከአፍሪቃ ጋ የንግዱ ግንኙነት መጠናከርን በቅርብ የሚከታተሉት አዲሷ የአሜሪካ ሚንስትር ፔኒ ፕሪትስከር የኦባማን ራዕይ በተግባር የመተርጎሙ ስራቸው ቀላል እንደማይሆን ነው ያሳየው።

ፕሬዚደንት ኦባማ በአፍሪቃ የኤሌክትሪኩን አቅርቦት ወደፊት በእጥፍ ለማሳደግ ይረዳል በሚል ለአህጉሩ በአምስት ዓመት ውስጥ የሚሰጥ ሰባት ቢልዮን ዶላር  ዝግጁ የሚያደርግ መርሀግብር አንደሚያነቃቁ ገልጸዋል።

« የኤሌክትሪክ አቅርቦት በአሁኑ ጊዜ የተሳካ ውጤት ለማስገኘት ወሳኝ ነው። መብራት ተማሪዎች የሚያጠኑበት ፣ አንድን ሀሳብ ወደ ተቋምነት መቀየር የሚያስችል እና ቤተሰቦችም መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ማሟላት የሚችሉበት ኃይል ነው። አፍሪቃን ከዓለም አቀፉ ኤኮኖሚ ጋ ለማስተሳሰር የሚያስፈልገው ማገናኛም ነው። »

Überland-Stromleitungen
ምስል picture-alliance/dpa

ይህን የኦባማ ቃል ገሀድ ማድረጉ ቀላል እንደማይሆን መገመቱ አያዳግትም፤ ምክንያቱም፣ ከሰሀራ በስተደቡብ ከሚገኙት ሀገራት መካከል ሁለት ሦስተኛው ኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭ የላቸውም። ለመጀመሪያ ጊዜ በመርሀግብሩ የተጠቃለሉት ስድስት ሀገራት፣ ማለትም በኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ታንዛንያ፣ ዩጋንዳ፣ ላይቤርያ፣ ናይጀሪያ እና በሞዛምቢክ ለሀያ ሚልዮን ቤተሰቦችን ኤሌክትሪክ የማቅረብ ዓላማ አለው። እርግጥ፣ ይህ ዕቅድ እስከ መቼ ተግባራዊ ይሆናል የሚለው ጥያቄ አልተመለሰም።

እርግጥ፣ ይኸው የኦባማ መርሀግብር የቀድሞዉ የዩኤስ አሜሪካ  ፕሬዝዳት ቢል ክሊንተን እንዳስተዋወቁት አጎአ (AGOA) በሚል እንግሊዝኛ ምሕፃረ ቃል እንደሚጠራዉ የዩኤስ እና የአፍሪቃ የንግድና ትብብር ወይም ፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ ብዙ ቢልዮን ገንዘብ እንደመደቡለት የኤች አይ ቪ ኤድስ ሥርጭትን መከላከያ መርሀግብር በአህጉሩ ታሪክ ትልቅ ቦታ ባይሰጠውም፣ እንደታሰበው ተግባራዊ ከተደረገ የታለመ ውጤት መገኘቱ አይቀርም።  

የኦባማ ጉብኝት ከአፍሪቃ ጋ የኤኖሚው ግንኙነት እንደሚጠናከር  ቢጎላም፣ አፍሪቃ አሁንም ትልቅ ትኩረት እንደማታገኝ  በታንዛንያ የጀርመናውያኑ ኮንራድ አድናወር ተቋም መኃላፊ ሽቴፈን ራይት ገልጸዋል።

« አፍሪቃ ምንም እንኳን አስፈላጊ ብትሆንም፣  በዩኤስ አሜሪካ የውጭ ፖሊሲ ላይ ከቀዳሚዎቹ መካከል አይደለችም። »

ኦባማ ከኤኮኖሚው  ሌላም ካነሱዋቸው ነጥቦች አንዱ ሙስና  ሲሆን፣ አፍሪቃውያን መንግሥታት በዚሁ አንፃር እንዲሰሩና ለዴሞክራሲ መስፋፋት እንዲሰሩ ጥሪ አሰምተዋል።

አድሪያን ኪርሽ / አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ