1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦባማ ድንገተኛ የአፍጋኒስታን ጉብኝት

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 24 2004

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ትናንት ምሽት በአፍጋኒስታ የሚገኘዉን የአሜሪካንን ጦር በድንገት ጎበኙ። ፕሬዝደንት ኦባማ በወቅቱ ለጦሩ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን ከአፍጋኒስታን መንግስት ጋርም ታሪካዊ ያሉትን ስልታዊ ስምምነት ተፈራርመዋል።

https://p.dw.com/p/14o8X
ባራክ ኦባማና ሃሚድ ካርዛይምስል AP

ስምምነቱ ሁለቱ ሐገሮች ከ2014ዓ,ም በኋላም ወታደራዊ ግንኙነታቸዉን ለመቀጠል እንደሚያስችላቸዉ ታዉቋል።

የዩናይትድ እስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፤ የዓለም አቀፉ የአሸባሪዎች መረብ ፣የአል ቃኢዳ መሪ ፣ ኦሳማ ቢን ላደን በተገደሉበት አንደኛ ዓመት አፍጋኒስታን ውስጥ ጉብኝት አካሄዱ። ኦባማ በአፍጋኒስታን መዲና በካቡል፤ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሃሚድ ካርሳይ ጋር፤ እ ጎ አ በ 2014 ፣ በዚያ የሚገኘው ዓለም አቀፍ ሰላም አስከባሪ ኃይል ከወጣ በኋላ፣ የዩናይትድ እስቴትስ ወታደሮች ድርሻ ምን ሊሆን እንደሚችል ውል ተፈራርመዋል። የአሜሪካ ወታደሮች ከ 2014 በኋላ፤ የአፍጋኒስታንን ወታደሮች ማሠልጠናቸውን እንደሚገፉበትና የአል ቃኢዳ ደጋፊዎችንም መውጋታቸውን ይቀጥላሉ ተብሏል። 

Obama Ansprache Bagram Air Field Afghanistan
ምስል AP

በያመቱ ፤ አፍጋኒስታን ምን ያህል አዲስ እርዳታ እንደሚያስፈልጋት የሚወስነው የአሜሪካ  ምክር ቤት ይሆናል። የአየር ኃይል ምሽግ በሚገኝበት ባግራም ላይ  ኦባማ፤ በቀጥታ ወደ ዩናይትድ  እስቴትስ በተሠራጨ ዝግጅት ላይ ባሰሙት ንግግር፣ ዩናይትድ እስቴትስ አል ቃኢዳን ለመደምሰስ ምንጊዜም ቆርጣ እንደተነሳች ናት ብለዋል። ኦባማ ትንንት ማታ፣ ከአፍጋኒስታን ወደ ሀገራቸው ባስተላለፉት መልእክት፣ እንዲህ ነበረ ያሉት--
«ከባግራም የአየር ኃይል ምሽግ፤ እንደምን አመሻችሁ እላለሁ! ይህ ጣቢያ ከትውልድ ሀገራችን፣  ከ 7, 000 ማይል(1,120 ኪሎሜትር) በላይ ይርቃል። ነገር ግን፣ ከ 10 ዓመት በላይ ልባችን ምንጊዜም ያረፈበት ቦታ ነው። ምክንያት ቢሉ፣ እዚህ አፍጋኒስታን ውስጥ፣ ከግምሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን፣ የሃገራችንን ደኅንነት ለማስጠበቅ ሲሉ መስዋዕትነት በመክፈል ላይ ናቸውና!በዛሬው ዕለት፣ በዩናይትድ እስቴትስና በአፍጋኒስታን መካከል የተደረገ አዲስ ታሪካዊ ውል ፈርሜአለሁ።
ወደፊት በሚኖረን  ግንኙነት፣ አፍጋኒስታናውያን  ለአገራቸው ፀጥታ ኀላፊነትን ይሸከማሉ።  በሁለቱም ነጻ መንግሥታት መካከል በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ትብብር ይኖራል። የወደፊቱ መጻዔ ዕድል፤ ጦርነት እንዲያከትም አዲሱ ምዕራፍ እንዲከፈት የሚያደርግ ነው። »

 

የኦባማ ጉብኝት ባበቃ በአጭር ጊዜ ውስጥ፤ የታሊባን ደጋፊዎች፣ የአውሮፓው ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት ሠራተኞች በሚጠቀሙበት አንድ የእንግዶች ማረፊያ ቤት  በጣሉት አደጋ፣ 6 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።   

አበበ ፈለቀ/ ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ