1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኦዲግና የግንቦት 7 ጥምረት ላይ የሕዝብ አስተያየት

Merga Yonas Bulaሐሙስ፣ ነሐሴ 12 2008

የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዲግ)ና አርበኞች ግንቦት 7 ሰሞኑን ኢትዮጵያን እያስተዳደረ የሚገኘዉን ፓርቲ በጋራ ለመታገል የመግባብያ ሰነድ ተፈራርመዋል።

https://p.dw.com/p/1Jl8a
Karte Äthiopien Amhara, Tigray, Oromia Deutsch

[No title]

ሰሞኑን በአገሪቱ የሚታየዉን የተቃዉሞ እንቅስቃሴ ሁለቱም እንደሚደግፉትና አገሪቱን እየመራ ያለዉ ፓርቲም በጉልበት ስልጣን ላይ መቆየት እንደሚፈልግ፤ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋርም በጋራ መሥራት እንደማይፈልግ የተፈራረሙት ሰነድ ያመለክታል። ለዚህም ኦዲግም ሆነ አርበኞች ግንቦት 7 በሚፈጥሩት ጥምረት የዴሞክራሲ እና የነፃነት ኃይሎችን በመጠቀም ገዥዉን ፓርቲ ከስልጣኑ ለማስወገድ እንደሚታገሉ በሰነዱ ተጠቅሷል።


ሁለቱ ድርጅቶች የሚያራምዱት የፖለቲካ ርዕዮት የተለያየ መሆኑ ይታወቃል፤ ከዚህ በመነሳትም ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ጥምረቱ አሁን ለምን አስፈለገ ሲሉ ይጠይቃሉ። አስተያየታቸዉን ከሰጡን መካከል የሃዋሳ ከተማ ነዋሪ መሆናቸዉን የገለጹልን ስማቸዉ እንዳይጠቅስ የጠየቁ አድማጫችን ጥምራቱ እንዳስደሰታቸዉ ይናገራሉ።

አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ካላቸዉ ልምድ በመነሳት በፊት ብዙ ፓርቲዎች ጥምረት ከፈጠሩ በኋላ የዉኃ ሽታ ሆነው ስለሚቀሩ የኦዲግና አርበኞች ግንቦት 7 ጥምረትም ተመሳሳይ እድል ሊገጥመዉ እንደሚል ከወዲሁ ይገምታሉ። የሃዋሳዉ ነዋሪ ግን የበፊቶቹ ለመፍረሳቸዉ ምክንያት ገዥዉ ፓርት ነዉ ይላሉ።

አቶ ጥበቡ ዓለማዬሁ፣ የአዲስ አበባ ነዋሪ ናቸዉ። አገሪቱ ዉስጥ ያሉትን ፓርቲዎች ገዥዉ ፓርቲ አቅማቸዉን እንዳደከመዉና በአገሪቱ ዉስጥ መደራጀትም ሆነ ለምርጫ መቅረብ እንደሚከብድ ይጠቅሳሉ። ለዚህም የሁለቱ ድርጅቶች ጥምረት አስፈላጊነትና ከሌሎች ፓርቲዎችም እንደሚጠበቅ።

አቶ ጥበቡ የትጥቅ ትግል አስፈላጊ ነዉ ቢሉም፣ ሌላዉ የአዲስ አበባ ነዋሪ ናሽድ ናስረዲን ግን በጦር መሳርያ መንግሥት የመገልበጡን ሃሳብ አይቀበሉትም።


አቶ ጥበቡ ይህን ይበሉ እንጂ በዶቼ ቬለ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ ከተሰጡን አስተያየቶች አብዛኛዉ ሁለቱም «አሸባሪዎች» ናቸዉ፣ «የማፍያ ቡድኖች እንጂ ለሕዝብ የቆሙ አይደሉም»፣ እናም «የተፈጠረውን ግርግር አጋጣሚ ለመጠቀም የተደረገ ስምምነት እንጅ ልዩነታቸውማ ነጭና ጥቁር ነው» የሚሉ አስተያየታቸዉን ሰንዝረዋል።

መርጋ ዮናስ

ሸዋዬ ለገሰ