1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ጥር 17 2011

የብዙ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ አስተያየት ሰጪዎችን ትኩረት የሳቡ ሰወስት ጉዳዮችን  ይቃኛል።የኦሮሚያ አስተዳደርና ኦነግ ሥለ መስማማታቸዉ ቀዳሚዉ ነዉ።የእነ አቶ በረከት ስምዖን መታሰር ቀጥሎ፣  የኢትዮጵያ ሶማሊያ መስተዳድር አዲስ ፖለቲካዊ ቀዉስ ያሰልሳል።

https://p.dw.com/p/3CCA6
Äthiopien Treffen Volksgruppe der Oromo
ምስል DW/S. Muchie

xxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxxx - MP3-Stereo

ጤና ይስጥልኝ እንደምን አመሻችሁ።የዛሬዉ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት የብዙ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴ አስተያየት ሰጪዎችን ትኩረት የሳቡ ሰወስት ጉዳዮችን  ይቃኛል።የኦሮሚያ አስተዳደርና ኦነግ ሥለ መስማማታቸዉ ቀዳሚዉ ነዉ።የእነ አቶ በረከት ስምዖን መታሰር ቀጥሎ፣  የኢትዮጵያ ሶማሊያ መስተዳድር አዲስ ፖለቲካዊ ቀዉስ ያሰልሳል።

                                  
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ በምሕፃሩ) ወራት ያስቆጠረ ደም አፋሳሽ፣ ግጭት፣ ዉዝግባቸዉን ለማስወገድ «የመጀመሪያ ደረጃ» የተባለ ስምምነት ትናንት አምቦ-ምዕራብ ሸዋ ላይ ተፈራርመዋል።ለኢትዮጵያ መንግስት ቅርበት ያላቸዉ መገናኛ ዘዴዎች እንደዘገቡት የሁለቱ ወገኖች ተወካዮች ተኩስ ለማቆም ተስማምተዋል።በአብዛኛዉ ምዕራብ ኦሮሚያ ዉስጥ ሸምቋል የሚባለዉ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ሠራዊት አለበት ከተባለዉ «ጫካ» ወጥቶ ማቆያ ሠፈር እንዲሠፍር ወስነዋልም።
የአምቦዉን ሥምምነት ያፈራረመዉ ባለፈዉ ሳምንት ማብቂያ የተመሠረተዉ «የቴክኒክ» ኮሚቴ ነዉ። «የቴክኒክ» የተባለዉ አስታራቂ ኮሚቴ ከምሁራን፣ ከአባገዳዎች፣ የኦሮሚያ ገዢ ፓርቲ (ኦዴፓ)ና ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የተወከሉ 71 አባላት ያሉት ስብስብ ነዉ።ኮሚቴዉ ባለፈዉ ሳምንት ማብቂያ አዲስ አበባ ዉስጥ ሲመሠረት የሁለቱ ጠበኛ ድርጅቶች ወይም የፖለቲካ ማሕበራት ተወካዮች ለመነጋገር-መስማማታቸዉ ለብዙ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አስተያየት ሰጪዎች «ብሥራት»፣ለጥቂቶቹ የትችት፣ለበጣም ጥቂቶቹ ደግሞ የጥያቄ ምክንያት ነዉ የሆነዉ።
ጉደታ ዓለሙ ፈይሳ፣ በፌስ ቡክ «ደስ ይላል» ይላሉ።«ለማ (መገርሳ)ና ዳዉድ (ኢብሳ) ወድማማች ናቸዉ።» ቀጠሉ ዓለሙ «2ቱም የኦሮሞን ህዝብ ይመራሉ። የኦሮሞ ወጣት 45 አመት ሲሞት፣ ሲገረፍ ኑሮ አሁን እከሌ ጠላት ነዉ እየተባለ የገበሬ የድሃ ልጅ ሞት ይብቃ።» 
ጉደታ  እንደሚሉት ሁለቱ ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች ደም አፋሳሹን ግጭትና ጠብ ለማቆም መስማማታቸዉ ለሌሎችም አርአያ ሊሆን ይችላል።«ተጣልቶ መታረቅ የእግዚአብሄር ትእዛዝ ነዉ ያዋጣል። ሃቀኛ አገራዊ የሽምግልና እርቅ ይቀጥል። በራያና ወልቃይት ይደገም።»
የላስታ ሰቆጣ፤ (ስሙ የፌስ ቡክ ብቻ ሳይሆን አይቀርም) አስተያየትም ከጉደታ ጋር የተመካከሩ ይመስላል።«በጣም ደስ ይላል፤ እርቁ ይስመር። ሃቀኛ አገራዊ ሽማግሌ ይስፋፋ።» ይሉና « የወልቃይት እራያ ጉዳይም በአገራዊ ሽማግሌ ይፈታ።» እያሉ ይቀጥላሉ።
ዴራ ማን፣ ግን የብዙዎችን ሥጋትና ጥርጣሬ ምናልባትም ከልምድ የመነጨ ቀቢፀ ተስፋን ባጭር ዓረፍተ ነገር የገለጡ ይመስላል።«በቃል ደረጃ የመስማማት ችግር የለባቸውም። ተግባር ላይ ግን አሁንም ጥርጣሬ አለን።»
በርግጥም የፌደራዊዉም ሆኑ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥታት፣የኦነግ ሆኑ የሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ባለስልጣናት፣ በሠላም አብሮ ለመስራት መስማማታቸዉን ያልተናገሩበት ወቅት የለም።አምስት ወር።ከአስመራ እስከ አዲስ አበባ መነጋገር፣መግባባት መስማማታቸዉን እየተናገሩ ከአዲስ አበባ እስከ ወለጋ መጋጨት፣ሰላማዊ ሕዝብን መግደል፣ማፈናቀል፣ ሐብት ንብረቱን መዝረፋቸዉ  ነዉ አሳዛኙ ሐቅ።
ባለፈዉ ሳምንት  አዲስ አበባ፣ ትናንት አምቦ ላይ ተስማሙ የተባሉትን የኦሮሚያ ክልልል መንግስትና የኦነግ ባለሥልጣናት ወይም መሪዎች ናቸዉ።የፌደራሉ መንግሥት በስምነቱ ያልተካፈለበት ምክንያት ያነጋግራል። የኦነግ ታጣቂዎች ከፌደራሉ መንግሥት የመከላከያ ሠራዊት ጋር መጋጨታቸዉ እየተዘገበ፣ ሥምምነቱ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ወይም የክልሉ ገዢ ፓርቲና የኦነግ ብቻ መሆኑ ወይም ብቻ ነዉ ተብሎ ለፌደራሉ መንግሥት ቅርበት ባለቸዉ መገናኛ ዘዴዎች መዘገቡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቅጥ ማጣቱን ጠቋሚ ነዉ።
ዴራ ማን «ተግባር ላይ ግን አሁንም ጥርጣሬ አለኝ» ማለታቸዉን የብዙዎች የሚያደርገዉም ይኸዉ ነቁ። 
እምይ ማን ስፖርት፣ ኦነግን ክፉኛ ነዉ የሚተቹት። በፌስ ቡክ ባሰፈሩት አስተያየታቸዉ እንዳሉት አያምኑትም።ሌሎችም እንደሳቸዉ እንዲሆኑ ይጠይቃሉም። «ምን እንደሚፈልግ አይታወቅም።ኢትዮጵያን ለማስተዳደር አቅምም፣ በህዝብም ተቀባይነት የለውም። ይኸ ድርጅት ተደምሬያለሁ እያለ ስንት ህዝብ ስንት ሀብት ጠፋ እናም አብሮ ለመስራት ተስማማሁ የሚለውን ነገር አትመኑት።»
የጌታቸዉ ሉሉ ጌቾ አስተያየት ደግሞ ኦነግ ላይ ከእምይ ማን ስፖርትም ጨከን ይላል።«የነቀዘዉ የኦነግ ክፍል ካልተቆረጠ።» ይላሉ ጌታቸዉ ሉሉ ጌቾ በፌስ ቡክ  «ጤነኛዉን የኦነግ ግንድ ማበስበሱ አይቀርም ...በህግ አግባብ መጠየቅ ያለባቸው ለፍርድ መቅረብ አለባቸዉ።» 
ሳኚ ኬናሳ፤- ግን ኦነግን ሳይሆን ኦዴፓን በቀድሞ ስሙ እየጠሩ ነዉ የወቀሱት።«እስኪ እናያለን።መቼስ OPDO አሁን ደግሞ ምን ሰበብ አምጥታ ብቅ ትል ይሆን?» ይጠይቃሉ ሳኚ ኬኔሳ በፌስ ቡክ አስተያየታቸዉ።
ሥለ ኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ወይም ስለ ክልሉ ገዢ ፓርቲ ሥለ ኦነግ ንግግርና ስምምነት የተሰጠና የሚሰጠዉ አስተያየት ብዙ ነዉ።ወደ ሁለተኛዉ ጉዳይ እንለፍ።የእነ አቶ በረከት መታሰር።
ሁለቱም መጀመሪያ የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዴን) ፣ስልጣን ሲይዝ ከኢትዮጵያነት ወደ አማራነት ጠበብ ብሎ የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን)፣በቅርቡ ደግሞ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) የሆነዉ ፓርቲ ከፍተኛ ባለስልጣናት ነበሩ።
አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) በተለይ አቶ በረከት የኢሕድንም የኢሕአዴግም መስራች፤ ከ1983 ጀምሮ ሁለቴ የማስታወቂያ ሚንስትር፤ ኃላ ደገሞ የመንግሥት የኮሙኒኬሽን ጉዳይ ሚንስትር፣ ከሁሉም በላይ የቀድሞዉ ፕሬዝደንትና ጠቅላይ ሚንስር መለስ ዜናዊ ቀኝ እጅ ነበሩ።
ሁለቱም፣ ባለፈዉ ዓመት መጨረሻ ከመጨረሻዉ ሥልጣኛቸዉ ከብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ታገዱ።ሮብ ታሰሩ።ምክንያት ብአዴን የሚቆጣጠረዉን ጥረት የተባለዉን የኩባንዮች ስብስብ በሚመሩበት ዘመን ደረሰ በተባለ ሙስና መጠርጠራቸዉ ነዉ።ሁለቱም ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ።መታሰራቸዉ ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ርዕሥ እንደሆኑ ሳምንቱ ሊያበቃ ነዉ።ጥቂቶቹን  እንጠቃቅስ። 
አቶ በረከት ባለፈዉ ነሐሴ ከብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት እንደተባረሩ ከDW ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ «ቤት እንኳን የለኝም» ብለዉ ነበር-በሙስና እንደሚጠረጠሩ ሲጠየቁ።ይሕቺ አባባላቸዉ ዛሬ ሲታሰሩ ለሰዉ አገኝ ፍቅሩ አታላይ ምፀታዊ  አስታየት ምክንያት ሳትሆን አልቀረችም።
«ቤት አልባ የቀድሞ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጊዚያዊ መጠለያ ተሰጣቸው።» አሉ ሰዉ አገኝ በፌስ ቡክ ስላቃቸዉ።
እግዚአብሔር ፍቅር ነው ደግሞ  አቶ ባረከት በቅርቡ መቀሌ ዩኒቨርስቲ የተናገሩትን ይጠቅሳሉ።«የኢ.ፌ .ዴ.ሪ. መንግሥት ጥርስ እንደለሌው በመቐለ ዩኒቨርስቲ የውይይት መድረክ ሲያወሩ ነበር፣» አከሉ አስተያየት ሰጪዉ።ቀጥሎም «በሌሎች ይደረግ የነበረው የህግ የበላይነትን የማስከበር ሥራ በረከት ላይም የጊዜ ጉዳይ እንጂ ከህግ እንደማያመልጡ እርግጠኞች ነበርን !!! ያልሞተ ሰው ገና ብዙ እናያለን። እድሜ ዳኛው» 
አበራ ሮክ ግን ተቃራኒዉን ነዉ ያሉት።«የዶክተር አቢይ መንግስት ሀሳብ ምንድነው?» ይጠይቃሉ፣ መልስ የመሰላቸዉን አስከትለዉ፣ «እኔ ሳስበው የአቢይ መንግሥት እንደ ሳውድ መንግስት ተቀናቃኝ እያሰረ አምባገነን ይሆናል የሚል ሀሳብ አለኝ» አበራ ሮክ በፌስ ቡክ።
ጌታሁን ተጠምቀ « በቀል» ይላሉ በፌስ ቡክ ፅሁፋቸዉ «የበቀል ፖለቲካ አሁንም ቀጥሏል። ለውጥ ነውና እኒህ ነበሩ የለውጡ አደናቃፊ? አህዴግ የሚለውና የሚተገብረው ለየቅል ሆነብኝ።»
አሰፋ ሲሳይ፣ ግን አቶ በረከት ስምዖንን በስም ጠቅሰዉ «ኢትዮጵያችንን የበደሉ፣ የታሪክ አተላ፣ ሀገር  የገነጠሉ፣ የዘረፉ ያስዘረፉ-----» እያሉ ዉግዘቱን አዝጎደጎዱት-ያዉ በፌስ ቡክ።
ቢያንከ አረጋዊ በቲዉተር ገፃቸዉ አጭር ግን ምናልባት አነጋጋሪ መልዕክት አስፍረዋል።እነሆ፣- «ብሔር አልባው ነፍሰበላ በሙስና ተጠርጥሮ በፊት በር ታሰረ። ብሔር ያለው ሌባ በጓሮ ተመልሶ ዐይኑን በጨው አጥቦ ለለውጥ ሀይሉ ያጋፍራል። በዛሬይቷ ኢትዮጵያ ልጅህን ወንጀል አትስራ ሳይሆን በተለይ ንፁህ ብሄር ሳይኖርህ ወንጀል አትስራ ብለህ አሳድግ!» ከቻላችሁ እንዴት ለምን በሉ።
የሶማሌ መስተዳድር  ፖለቲከኞች የገጠሙት እሰጥ አገባ እንዳዲስ አገርሽቷል።ከአራት ወር ግድም በፊት የቀድሞዉን የክልሉን ርዕሠ-መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ዑመርን (አብዲ ኢሌ በቅፅል ስማቸዉ) ከስልጣን ለማዉረድ ምናልባትም በሕግ ለማስጠየቅ ባንድ ያበሩ የመሰሉት ፖለቲከኞች አሁን እየተዘጋቡ ነዉ።
አዲሱን የክልሉን ርዕሠ መስተዳድር ሙስጠፋ መሐመድ ዑመርን ከስልጣን ለማዉረድ የክልሉ ገዢ ፓርቲ የኢትዮጵያ ሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ኢሶሕዴፓ ሊቀመበርና በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙ የተባሉ ኢሕአዴግ አባላት እያሴሩ ነዉ መባሉ ዕንቆቅልሽ ሆኗል።በሻን ኤዲ-«ምን አይነት ነገር ነዉ?» ጠየቁ በፌስ ቡክ።«የሶሕዴፓ ሊቀመንበር ማለት አብዲ ሺዴ ናቸዉ።በፊትም የአብዲ ኢሌ ተላላኪ ነበሩ።መንግስት ሊገለብዙ ነዉ?» እንደገና ጠየቁ።
ሳምሶን ክብረት በፋንታቸዉ «አሳፋሪ ተግባር ነው።»ይሉታል።«ጠቅላይ ሚንስትር  ዐቢይ ለጉዳዩ ከባድ ትኩረት ሊሠጡትና ፈጣን ርምጃ ሊወስዱ ይገባል። የሶማሌ ክልል አለመረጋጋት ለመላው ኢትዮጵያ አደጋ ነው።»
ሔኖክ MH፣ ከሳምሶንም ጠንከር ያደርጉታል።«በጣም አሳፋሪ ነዉ።ዐብያችን ለጉዳዩ አስቸኳይ መፍትሔ ይፈልጉለት።»
እስካሁን መፍትሔዉ አልተነገረንም።ምናልባት ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በሰብአዊ መብት ጥሰትና በሌሎች ወንጀሎች በሚጠረጠሩ የሶማሌ ክልል የቀድሞ ባለሥልጣናት ላይ ያደረገዉን ማጣራት ዛሬ ይፋ አድርጓል።ይሕ መፍትሔ ይሆን? ነጋሽ መሐመድ ነኝ መልካም የሳምንት መጨረሻ።

Jemal Deere Kelif
ምስል privat
Äthiopien Konferenz in Mekelle Bereket Simon
ምስል DW/M. Haileselassie
Äthiopien Treffen Volksgruppe der Oromo Dawud Ibssa
ምስል DW/S. Muchie

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ