የኦዴፓ እና የኦሮሞ ፓርቲዎች ምክክር 

አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
05:00 ደቂቃ
06.12.2018

የኦሮሞ ፓርቲዎች ምክክር

በኦሮምያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የኦሮሞ ፓርቲዎች፣ ከግጭት እና አላስፈላጊ ፉክክር ርቀው ቢተባበሩ ለክልሉ መረጋጋት እንደሚበጅ አንድ DW ያነጋገራቸው የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ አሳሰቡ። ተንታኙ ጥቃቅን የፖለቲካ ልዩነቶች ላይ በማተኮር ከመጋጨት ይልቅ ተቀራርበው ችግሮችን በመፍታት የህዝቡን ጥቅም ማስጠበቅ ቅድሚያ ሊሰጡት የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል።

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ)በኦሮምያ ክልል ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ከ10 በላይ ከሚሆኑ የኦሮሞ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች ጋር ዛሬ ውይይት አካሂዷል። «በአንድነት ወደ ዴሞክራሲ ስርዓት ሽግግር» በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው በዚሁ ውይይት ላይ የአገር ሽምግሌዎች እና አክቲቪስቶችም ተሳትፈዋል። በዚህ ውይይት ላይ በኦሮምያ ክልል የሚንቀሳቀሱ የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኦሮሞ ህዝብ ጉዳይ ላይ አብረው መሥራት የሚችሉበት መንገድ ላይ ምክክር ተካሂዷል። በዚሁ ውይይት ላይ የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ እንዲቋቋም ተወስኗል። መድረኩ ተመሳሳይ ውይይቶችን ለማካሄድ እና ችግሮችንም በውይይት ለመፍታት የሚያስችል እንደሚሆን ተነግሯል። በስብሰባው ላይ የተካፈሉት የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ አቶ ገረሱ ቱፋ ለDW በሰጡት አስተያየት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ተቀራርበው ለመነጋገር መስማማታቸው በጎ ጅምር ነው ብለዋል። በአቶ ገረሱ እምነት በኦሮምያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጎላ ልዩነት አይታይባቸውም። ከዛሬው የውይይት መድረክ እንደተገነዘቡትም አንዳንድ ፓርቲዎች ከኦዴፓ ጋር ለመሥራት ይፈልጋሉ።  
እነዚህ ፓርቲዎች ልዩነቶቻቸው ለማጥበብም ሆነ በኦሮምያ የተከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት በተለመደው አካሄዳቸው መቀጠል የለባቸውም እንደ አቶ ገረሱ። ፓርቲዎቹ ወደ ግጭቶች ከሚወስዱ አላስፈላጊ ፉክክር መቆጠብም አለባቸው። ጥቃቅን ባሏቸው ልዩነቶች ላይ ከማተኮር ፣የጋራውን ወቅታዊ ችግር ለመፍታት በሚያስችሉ ጥረቶች ላይ መትጋት አለባቸው። እንቅስቃሴያቸውም ጥንቃቄ የተሞላበት ሊሆን ይገባል። ለዚህም ምክንያት የሚሉት «የተለየ» ሲሉ የገለጹት የወቅቱን የኢትዮጵያ ሁኔታ ነው። 
ዛሬ ኦዴፓ ከተቃዋሚ የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከአገር ሽማግሌዎች እና ከአክቲቪስቶች ጋር ባካሄደው ምክክር ላይ የፀጥታ ችግርም ተነስቶ ነበር። በተለይ የምዕራብ ኦሮምያ የፀጥታ ችግር፣ በቤንሻንጉል እና በኦሮምያ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ሰዎች ጉዳይ፣ እና በዚያ አካባቢ አለ ከሚባለው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የኦነግ ሠራዊት እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ተፈጥሯል የተባለ ችግር ተመክሮበታል። አቶ ገረሱ የቀጠለውን የፀጥታ ችግሩ መንስኤ እና በዛሬው ውይይት በመፍትሄነት የቀረቡትን ሃሳቦች አስረድተዋል።   

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ከማዕቀፉ ተጨማሪ ዘገባዎች

03:34 ደቂቃ
ኢትዮጵያ | 8ከ...ሰዓት በፊት

ለአማራ ተፈናቃዮች ርዳታ ተሰጠ

04:06 ደቂቃ
ኢትዮጵያ | 9ከ...ሰዓት በፊት

የብሔራዊ ፈተና ዝግጅት

ተከታተሉን