1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የከብት አርቢዎች ግጭት በምስራቅ አፍሪካ

ዓርብ፣ መጋቢት 30 1997

በድርቅ በተደጋጋሚ በሚመታዉ በሰሜናዊ ኬንያ አካባቢ በዉሃ እጥረትና በግጦሽ መሬት ሳቢያ በከብት አርቢዎች መካከል የሚፈጠረዉ ግጭት እየተባባሰ ሄዷል። ከዚህ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች አባባሽነት በጎሳ መካከል በቆየዉ ግጭትም ከአንድ መቶ በላይ ሰዎች ከያዝነዉ የአዉሮፓዉያኑ ዓመት መጀመሪያ አንስቶ ተገድለዋል

https://p.dw.com/p/E0k5
በሰሜን ዑጋንዳ Lord’s Resistance Army በደቡብ ሱዳን ሚሊሻዎች፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ኦነግና በምሥራቅ አፍሪካ ያለዉን በረሃማ ቦታ ሁሉ እንደራሱ ግዛት የሚቆጥረዉ የሶማሊያዉ War Lord የሚያቀርቡት የጦር መሳሪያ በኬንያ ላለዉ የጎሳ ብጥብጥ ተደራራቢ ችግር መፍጠሩን OXFAM አስታዉቋል።
የብሪታንያዉ ግብረ ሰናይ ድርጅት OXFAM እንደሚለዉ ሰሜናዊ ኬንያ በጦር መሳሪያ ተጥለቅልቃለች።
ከሶማሊያ ጋር በሚዋሰነዉ የማንዲራ ክፍለ ሃገር ጋሬ እና ሙሩሉ የተሰኙት ጎሳዎች ግጭት የዘወትር ተግባራቸዉ ሆኗል። በቅርቡም በተቀሰቀሰ ግጭት 23 የጋሬ ጎሳ የገጠር ኗሪዎች አብዛኛዋቹ ሴቶችና ህፃናት ናቸዉ በAK 47 ጠብመንጃ ተገድለዋል።
ተመሳሳይ ግጭት በሌሎች ጎሳዎች መካከልም ተነስቶ በመርሳ ቤትና በቱርካና ክፍለ ሃገራት የበርካቶች ህይወት ጠፍቷል።
በአካባቢዉ የሚንቀሳቀሱ መንግስታዊ ያልሆኑና የእርዳታ ድርጅቶች እንደሚሉት ከሰሜን ኬንያ ከደቡብ ኢትዮጵያና ከሶማሊያ በሺ የሚቆጠሩ አርብቶ አደሮች ወደ 250,000 የሚቆጠሩ ከብቶች ከሺ በላይ በጎችና ፍየሎች እንዲሆም ግመሎቻቸዉን ይዘዉ ዉሃ ፍለጋ ወደ ደቡባዊ የኬንያ አካባቢ ተሰደዋል።
ከቦረና፤ ከሶማሊያ፤ ከቱርካና፤ ከሳምቡሩና ከሚሩ ጎሳዎች የተሰደዱት እነዚህ አርብቶ አደሮች በኬንያ ኪሲቱ ክፍለ ሃገር በምትገኘዉ ኢሲሎ ያለዉን ዉስን የግጦሽ መሬትና ዉሃ በጋራ ለመጠቀም አስበዉ ነዉ ወደዚያ የሄዱት።
እነዚህ ስደተኞች ያላቸዉ ዋነኛ ሃብት ከብቶቻቸዉ ናቸዉ። የህልዉናቸዉ መሠረት የሆኑት ዉድ እንስሶቻቸዉ በረሃብና ዉሃ እጦት ሲሞቱ ሲያዩ ያኔ በመካከላቸዉ ግጭት ይቀሰቀሳል።
በዚያን ሰዓት የሚያስቡት አንድ ነገር ብቻ ነዉ ከብቶቻቸዉን ማዳን ለዚያ ሲሉም ለመሞትም ሆነ ለመግደል ዝግጁ ናቸዉ።
እዚህ የመጣሁት በአገሬ በማንዳር ያሉት የዉሃ ጉድጓዶች ስለደረቁ ነዉ በማለት የገለፀዉ ሶማሊያዊዉ አርብቶ አደር አብዲከር ሞሃመድ ነዉ።
በመኖሪያ አካባቢዉ በዉሃ እጦት በርካታ ግመሎች ማለቃቸዉን የገለፀዉ ይህ ሰዉ በዚያ ሰበብ ሰዎች መጋጨት እንደጀመሩ ነዉ የሚናገረዉ።
ሞሃመድ ኢሲሎ ለመድረስ ከብቶቹን እየነዳ 550 ኪሎ ሜትር በመጓዝ ከሁለት ቀናት በላይ ፈጅቶበታል።
በመንገዱም በዉሃና ግጦሽ መሬት ሳቢያ ከሌሎች ጎሳዎች ጋር ይፋለሙ የነበሩ የእርሱ ቢጤ አርብቶ አደሮችን አይቷል።
እዚህ እንደደረሰም ከሳምቡሩ፤ ከቦረና እንዲሁም ከአገሩ ከመጡ ሌሎች ቢጤዎቹ ጋር በመተባበር ዉሃ ለማግኘት ጉድጓድ የቆፈሩት በጋራ ነዉ።
ሞሃመድ እንደገለፀዉ ይሄ የመጀመሪያ ጊዜዉ መሆኑ ነዉ ቋንቋዉን ከማይናገሩ ሰዎች ጋር በጋራ ሲኖርና ሲሰራ።
ሁኔታዉ ለመተባበር እንዳስገደዳቸዉ ሁሉ ተረዳድተዉ ለመኖር ቢጥሩም አሁንም ከብቶቻቸዉን ከሞት አላዳኑም።
ዉሃ ባለመኖሩ ፀሃይም እጅግ እየበረታች ስትመጣ ከደቡብ ኢትዮጵያ ከሜጋ አካባቢ ጉዞ የጀመርኩት የዛሬ ሶስት ወር ገደማ ነበር። በበረሃ ዉስጥ መጓዙ በጣም አዳጋች ቢሆንም ፈጣሪ እንዲጠብቀኝ እየፀለይኩ እዚህ ደረስኩ ያለዉ ደግሞ ኢትዮጵያዊዉ አብዱል ጃፈር ነዉ።
በደቡብ ኢትዮጵያ ይላል አብዱል ገበያ የለም ሰዎቹም ከድህነታቸዉ የተነሳ ከብት አይገዙም። የመንግስት ወታደሮችም ችግር ይፈጥሩብናል። ስጋ ሲፈልጉ በቃ ዝም ብለዉ ከብቶቻችንን ተኩሰዉ ይመቷቸዋል በማለት ወደ ሌላ ቦታ ለመሰደድ ያበቃዉን ምክንያት ገልጿል።
በሌላ ወገን ኬንያ ዉስጥ የሚገኙት ጎሳዎች ምንም እንኳን እርስ በርሳቸዉ የሚጋጩ ቢሆኑም ኢስሎ የሚገኙት ስደተኞች ግን አንፃራዊ ሰላም አላቸዉ።
እዚህ የሚጋጭ የለም ይላል አብዱልም። ምክንያቱም ሲያስረዳ እዚህ ያሉት ሁሉም ከብት ሸጠዉ ገንዘብ ማግኘት የሚፈልጉ መሆናቸዉ ነዉ ይላል። እንደሱ አስተያየት ደግሞ በግጭት ጊዜ መሸጥና መግዛት አይኖርም።
በዚያ ላይ በመካከላቸዉ የሚፈጠረዉን ግጭት ለመሸምገል በዚህ አካባቢ የሰላምና የድርድር ኮሚቴ ተቋቁሟል።
የግጭታቸዉ መነሻ የግጦሽ መሬትና የዉሃ እጥረ ብቻ አይደለም የሚሉት በአካባቢዉ የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተጠያቂ የሚያደርጉት የፓለቲካ አካላት ነዉ።
ከዚያም አልፎ ከባህልና ወግ አንፃር ሲታይ በግጭት ወቅት የሌላዉን ጎሳ እየገደሉ ከብት መዝረፍ ወንድነት የሚፈተንበት የቆየ የአባቢዉ ልማድ መሆኑንም ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።
አንዳንድ የየጎሳዎቹ አባላት አሁን እየተረዱት የመጡት ነገር አለ። ለወግና ልማዳቸዉ ብለዉ መጋጨት ከቀጥሉ የግጦሽ መሬትና ዉሃ በማግኘት ፋንታ ትዉልድ አጥተዉ አካባቢዉ ሰዉ አልባ እንደሚሆን።