1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምደባ እና ስጋቱ

Eshete Bekele ዓርብ፣ መስከረም 13 2009

የኢትዮጵያ አገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ድርጅት በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተደለደሉ ተማሪዎችን በትናንትናው ዕለት ይፋ አድርጓል። የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ግን ከተማሩበት ቀዬ ራቅ ብለው ለሚጓዙ ተማሪዎች እና ለቤተሰቦቻቸው ሥጋት መፍጠሩ አልቀረም።

https://p.dw.com/p/1K7PO
ምስል DW

[No title]

አስራ ሁለተኛ ክፍልን አጠናቀው ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለመግባት የተዘጋጁ ተማሪዎች እና ወላጆቻቸው በጉጉት የሚጠባበቁት ምደባ ይፋ ሆኗል። አገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ድርጅት በመደበኛ እና በማታ ተምረው በተፈጥሮ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ከ315 እና ከዚያ በላይ ያመጡ ወንዶች እና ከ300 እና በላይ ያመጡ እንስት ተማሪዎች በመላ አገሪቱ በሚገኙ አዳዲስ እና ነባር ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መድቧል። በማሕበራዊ ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ከ280 እና ከዚያ በላይ ያመጡ ወንዶች እንዲሁም 270 እና ከዚያ ያመጡ ሴቶች ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመድበዋል።
በኢትዮጵያ የኦሮሚያ እና የአማራ ክልሎች የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ግን ለተማሪዎቹም ሆነ ለቤተሰቦቻቸው ሐሳብ ሆኗል። ወንድማቸው ከተማረበት ቀዬ ለትምህርት እንደሚጓዝ የተረዱት አቶ አብርሐም (የአባታቸውን ሥም አልተናገሩም) ይህ ስጋት ከገባቸው መካከል አንዱ ናቸው።
በዶይቼ ቬለ የፌስ ቡክ ማህበራዊ ድረ-ገጽ ውይይት ላይ የተሳተፉት አቶ አያናው ወርቁ « አንዴ ፈተናው በመሰረቁ ሌላ ጊዜ ደግሞ በአካባቢው ብጥብጥ በነበረበት ሁኔታ ላይ የነበሩ ተማሪዎች ከፍተኛ የስነ ልቦና ጫና ፈጥሮ አልፏል። የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት በመጣልኝ እያለ ሲጨነቅ የከረመ ተማሪ (መቸም በትምህርት መንገድ ያለፈ ጭንቀቱን ያውቀዋል) አሁን ደግሞ ባልፈለጉት ዩኒቨርስቲ መመደባቸው የበለጠ ያሳዝናል። » ሲል አስተያየታቸውን አስፍረዋል።
ክንድአለም ንጉሴ በበኩላቸው « ከአሁኑ መፍትሄ ካልተቀመጠ ተማሪዎች እርሥ በእርሥ ይተነካኮሣሉ» ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጠዋል። ፍቅሪ'ዩ ህይወተይ ደግሞ «ሰላም ከሌለ ምንም ነገር የለም። ተቃውሞው በመማር ማስተማሩ ዙሪያ ተፅዕኖ ይኖረዋል። እናም መንግስትና ህዝብ ተወያይተው መፍታት አለባቸው!!!» ብለዋል።
ወንድማቸውን ወደ ተመደበበት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም በመላክ እና ባለመላክ መካከል የሚዋልሉት አቶ አብርሐም የኢትዮጵያ መንግስት ፣ ተቃውሞዎች ሲቀሰቀሱ የኃይል እርምጃ ከመውሰድ ቢቆጠብ የሚል አስተያየት አላቸው።
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ የጎላ ተሳትፎ አላቸው። በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በመላ አገሪቱ ከሚገኙ መምህራን ጋር በጀመረው ስልጠና ላይ በተሳታፊዎች ከተነሱ አበይት ጉዳዮች መካከል የአገሪቱ ነባራዊ ቀውስ ይገኝበታል። ውይይቶቹ የአዲስ ተመዳቢ ተማሪዎችን ስጋት ለመፍታታቸው ግን ማረጋገጫ የለም።
በዋትስ አፕ ገፃችን ከደረሱን መልዕክቶች መካከል «በክልላቸው እንዲማሩ ይፈቀድላቸው ዘንድ የሚመለከተውን ክፍል አነጋግሩ እና መፍትሄ ይሰጠው።» የሚል ይገኝበታል። ስማቸውን ያልነገሩን ሌላ ተሳታፊያችን ደግሞ «ዮኒቨርስቲ መቀየር ይቻላል በተመሳሳይ ፊልድ እና በተለያየ ፆታ ይቺን ጥያቄ እንድትመልሱልኝ በአክብሮት እጠይቃለሁ።» ሲሉ ፅፈዋል። መሰል የቅያሬ ማመልከቻዎች ስለመኖራቸው ለመጠየቅ አገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ድርጅትን ለማነጋገር ብንሞክርም አልሰመረም።
እሸቴ በቀለ
ሒሩት መለሰ