1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የፖለቲካ ተሿሚዎች

ሐሙስ፣ መስከረም 19 2009

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መምህራን ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት በተሳታፊዎች ከተተቹ ጉዳዮች መካከል የትምህርት ተቋማትን ቦርድ የሚመሩ የፖለቲከኛ ሹመኞች ጉዳይ አንዱ መሆኑ ተሰምቷል። ምሁራኑ በፖለቲካ ሹመኞች የተሞሉ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቦርዶች እንዴት የትምህርት ጥራትን ማሳደግ ይችላሉ ሲሉ ሞግተዋል። 

https://p.dw.com/p/2QkBL
Deutschland Universität Bonn Doktorhut
ምስል picture-alliance/dpa/J. Stratenschulte

The impact of political appointment on the Educational system - MP3-Stereo

በዶይቼ ቬለ የፌስቡክ ማሕበራዊ ድረ-ገፅ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ በተደረገ ውይይት የተሳተፉት ሰለሞን በላቸው «የመንግስት አካላት የዩኒቨርሲቲዎች የቦርድ ሰብሳቢ መሆናቸው ለትምህርት ጥራት ጥሩ አስተዋጽኦ አለው፤» ይላሉ። አቶ ሰለሞን «የትምህርትን ጥራትን ሊያውኩ የሚችሉ መጥፎ አቅጣጫዎች ካሉ መንግሥት ጣልቃ በመግባት ማስተካከያ መፍትሄዎችን ይሰጣል ልቅ የሆነ የመምህራን ኢ-ዲሞክራቲክ አስተሳሰብን ይሰብራል» ብለዋል። 

ፍሬዘር ብርሃኑ ግን የፖለቲካ ሹመቱ «የስርዓቱን ህልውና ከማረጋገጥ በዘለለ ከትምህርት ጥራት ጋር አንዳችም ግኑኝነት የለውም።» ባይ ናቸው። ጸሐፊው  «የስርዓቱን ጠቅላይነት ማሳያ ሊሆኑ ከሚችሉ ገጽታዎች መካከል ያሉትን ተቋማት ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ፖለቲካዊ ቅኝት እንዲኖራቸው አድርጎ ማዋቀር ነው። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱም ከፍተኛ ስልጣናት አወቃቀርም ይህንኑ ከግብ ለማድረስ የተተለመ እንጂ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተቀመረ አይደለም።» ሲሉ ኃሳባቸውን አስፍረዋል።

ለረጅም ጊዜ በዩኒቨርሲቲ  ሲያስተምሩ እንደቆዩ የሚናገሩት አቶ ወንድይራድ አስማማው የከፍተኛ ተቋማት አመራርሮች በፖለቲካ አቋማቸው የተሾሙ እንደሆኑ ይናገራሉ። 

በዶይቼ ቬለ የፌስቡክ ማሕበራዊ ድረ-ገፅ አስተያየታቸውን ያሰፈሩት አሰፋ ወ «እንኳን በከፍተኛ የትምርት ተቋማት በአንደኛ ደረጃ ት/ት ቤቶች እንኳን መሪዎቹ የድርጅት አባላት ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ከትምህርት ጥራት ይልቅ ቁጥርን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ትርፍ ማስፋፊያ በመሆኑ የትምህርት ጥራት አለ ለማለት ይከብዳል።» ብለዋል። አቶ ወንድይራድ አስማማው በኢትዮጵያ ለሚስተዋለው የትምህርት ጥራት ጉድለት የመምህራን ነፃነት እጦት አንዱ ነዉ ባይ ናቸዉ። በፖለቲካዊ ጫናው ምክንያት መምህራኑ በአንድ ተቋም ለመርጋት እንደማይሹ ለሙያው ያላቸው ክብርም ማሽቆልቆሉንም ታዝበዋል። በእሳቸው ገለጣ ትምህርትና ፖለቲካ ተደበላልቀዋል።


የማነ ገብረኪዳን ግን «ፓለቲከኛው ክፍል ገብቶ አያስተምር፤ ምርምር አይሰጥ፤ ምን አገናኘው ከትምህርት ጥራት ጋር?  ወዴት ጠጋ ጠጋ? መምህሩ ነው ተጠያቂ፤ ክፍል ገብቶ ፖለቲከኛው አልረበሸውም። ለመምህሩ ጥናት ሲሰራም ርእስ አልመረጠለት። ምንም ተያያዥነት የለውም።» ሲሉ አስተያየታቸውን ገልጠዋል። ይባቤ ወርቁ በበኩላቸው «ቀበሌን በትክክል መምራት ባለመቻሉ ህዝብ እያስለቀሰ የሚገኝ ካድሬ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን መርቶ እንዴት አገር ተረካቢ ትውልድ ማፍራት ይችላል ?» ሲሉ ጠይቀዋል።

እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ

The impact of political appointment on the Educational system - MP3-Stereo