1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኩባና የዩኤስ አሜሪካ ግንኙነት እየተሻሻለ መምጣቱ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 6 2001

በዩኤስ አሜሪካ በስደት የሚኖሩ የኩባ ተወላጆች ካለፉት ሶስት አሰርተ ዓመታት ወዲህ አሁን በትውልድ ሀገራቸው የሚገኙ ዘመዶቻቸውን ካላንዳች ገደብ ሊጎበኙ እንደሚችሉ ተገለጸ።

https://p.dw.com/p/HWj9
ምስል AP

የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ኩባውያኑ አሜሪካውያን ወደ ትውልድ ሀገራቸው እንዳይጓዙ አርፎባቸው የነበረውን ዕገዳ በጠቅላላ አንስተዋል፤ ወደ ትውልድ ሀገራቸውም የፈለጉትን ያህል ገንዘብ እና የስጦታ ፓኬቶች ጭምር እንዳይልኩ የሚከለክለውንም ደምብ ሽረዋል። በኩባ ላይ ካለፉት አርባ ሰባት ዓመታት ወዲህ የተጠለው ኤኮኖሚ ማዕቀብ ግን አሁንም እንደጸና ይገኛል። የቀድሞው የኩባ መሪ ፊደል ካስትሮ በሁለቱ ሀገሮች ግንኙነት ላይ የታየውን ለውጥ ቢያሞግሱም፡ ኩባ ርዳታ ሳይሆን ማዕቀቡ ቢነሳላት እንደሚሻል በግልጽ አስታውቀዋል።

የዩኤስ አሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ይህን ርምጃ የወሰዱት ገና በምርጫ ዘመቻ ወቅት ሀገራቸው በኩባ አኳያ የምትከተለውን ጥጥር ፖሊሲ ለማላላት በገቡት ቃል መሰረት ነው። የፕሬዚደንት ኦባማ ቃል አቀባይ ሮበርት ጊብስ እንዳስታወቁት፡ ይኸው ዩኤስ አሜሪካ በኩባ አኳያ ስትከተለው በቆየችው ፖሊሲ ላይ አሁን ያደረገችው ለውጥ በደሴቲቱ ዴሞክራሲያዊና ፖለቲካዊ መብቶችን የማስፋፋቱን ሂደት ለማበረታታት የታሰበ ነው። ፕሬዚደንት ኦባማ ኩባውያን ተጨማሪ ነጻነት እንዲያገኝ ምኞታቸው መሆኑን ጊብስ አክለው አስረድተዋል።

ዋነኞቹን ዴሞክራቲክ እሴቶችን አምነው የተቀበሉ ሁሉ የዜጎችዋን መሰረታዊ የሰብዓዊ፡ የፖለቲካና የኤኮኖሚ መብቶችን የምታከብር ኩባ እንድትመሰረት ይጓጓሉ። ፕሬዚደንት ኦባማ ዛሬ የወሰዱት ርምጃ ይኸው ዓላማ ገሀድ እንዲሆን ይረዳል ብለው ያምናሉ። »

የኩባ ህዝብ ሀቀኛውን ነጻነት ያገኝና የፕሬዚደንት ኦባማ ርምጃም ለብዙ ዓመታት ሻክሮ የቆየውን የሁለቱን ሀገሮች ግንኙነት ለማሻሻል ያስችል ዘንድ ግን በመዲናይቱ ሀቫና የሚገኘው የኩባ መንግስት በሚከተለው አመራር ላይ አንዳንድ ለውጥ ማድረግ ይጠበቅበታል።

በኩባውያን አሜሪካውያን ላይ ያረፈው ዕገዳ በተነሳበት ርምጃ በተደሰቱት ኩባውያን አንጻር ለብዙ ዓመታት የመሩትንና እአአ በ 2008 ዓም ስልጣኑናቸውን ለወንድማቸው ለራውል ካስትሮ ያስረከቡት የቀድሞው የኩባ መሪ ፊደል ካስትሮ መልካም መሆኑን ቢሉትም፡ ርምጃው ርቆ እንዳልሄደ ከማስታወቅ አልተቆጠቡም። በፕሬዚደንት ኦባማ ውሳኔ ላይ ካለፉት አርባ ሰባት ዓመታት ወዲህ በኩባ ላይ ስላረፈው ጠንካራው የኤኮኖሚ ማዕቀብ በአንድ ቃል እንኳን አለመወሳቱ ፊደል ካስትሮን ቅር አሰኝቶዋል። ፊዴል ካስትሮ ሀገራቸው ርዳታ ሳይሆን እርሳቸው በጣም ጨካኝ የሚሉት ያሜሪካውያኑ ኤኮኖሚያዊ ማዕቀብ እንዲነሳለት ነው ያሳሰቡት። የዩኤስ አሜሪካውያን ተቋማት በኩባ የሳተላይት ስነ ቴክኒክ እንዲያስተዋውቁ፡ ዘመናይ የስልክ መገናኛ ገመዶችን ወደ ኩባ እንዲዘረጉና የገመድ አልባ ስልኮች አቅራቢዎችም ከኩባ ተቋማት ጋር አገልግሎት የመስጠቱን ስምምነት እንዲደርሱ ይፈቅዳል።

የፕሬዚደንት ኦባማን ርምጃ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት « ሂውመን ራይትስ ዎች » ዩኤስ አሜሪካ እስካሁን ስትከተለው ከቆየችው ኢፍትሃዊና ያልተሳካ ፖሊሲ ለመላቀቅ የሚረዳ ወሳኝ ርምጃ ሲል አሞግሶታል። ማዕቀቡን በተመለከተ ግን የዩኤስ መስተዳድር ተጨማሪ ርምጃዎችን መውሰድ እንደሚጠበቅበት ድርጅቱ ከማሳሰብ አልቦዘነም። የዩኤስ አሜሪካ የንግድ ምክር ቤትም ወደ ሀምሳ ዓመት የተጠጋው ማዕቀብ እንዲላላ ጠይቆዋል። የዩኤስ አሜሪካ ዜጎች ወደ ኩባ እንዳይጓዙ የሚከለክለውን ዕገዳ እንዲያነሳ በርካታ ዴሞክራት እና ሬፑብሊካን ፖለቲከኞች ለህግ መመሰኛው ምክር ቤት ማመልከቻ አስገብተዋል።

ፕሬዚደንት ኦባማ ለአዲሱ የኩባ ፖሊሲያቸው በዚህ ሳምንት በትሪኒዳድና ቶቤጎ በሚደረገው የአሜሪካ ጉባዔ ላይ ድጋፍ እንደሚያገኙ ይጠበቃል። ይሁንና፡ በኩባ በርግጥ ለውጥ የማምጣቱን ሁኔታ ለማበረታታት ከተፈለገ፡ ዩኤስ አሜሪካ በኩባ አኳያ በተናጠል የምትከተለውን አሰራር በመተው፡ በላቲን አሜሪካ እና በአውሮጳ ካሉ ተጓዳኞችዋ ጋር ተባብራ መስራት እንደሚኖርባት የፕሬዚደንት ኦባማ አማካሪ ዳን ሬስትሬፖ አስገንዝበዋል።

DW/AFPE/DPA/

አርያም ተክሌ