1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኩፍኝ በሽታ ስርጭት መጨመሩ

ማክሰኞ፣ የካቲት 26 2011

የኩፍኝ ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ መጨመሩ የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት አስታውቋል። በሽታው ከሳምባ ነቀርሳና ኢቦላ በበለጠ ተላላፊ እንደሆነ ተቀምጧል። የኩፍኝ በሽታ በተለይም በሕጻናት ላይ ሞትና ህመም ያስከትላል።

https://p.dw.com/p/3EUso
Impfung gegen Masern
ምስል Imago/Xinhua

በኢትዮጵያ የኩፍኝ በሽታ ስርጭት

እንደጎርጎራዊ አቆጣጠር በያዝነው 2019 ዓመት የዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት የኩፍኝ በሽታ በአለም አቀፍ ደረጃ መጨመሩን በሪፖርቱ ገልጿል። 
የዓለም የጤና ድርጅት እንደገለጸው በ2018 በአለም አቀፍ ደረጃ 50 በመቶ የበሽታው ስርጭት ከፍ ብሏል። 136,000 ሰዎችንም በዚሁ በኩፍኝ ሕይወታቸው እንዳለፈ ጠቅሷል። 
ድርጅቱ ዩክሬይን ፣ ፍሊፒንስና ብራዚል ከዓመት ዓመት የወረርሽኙ ቁጥር ከጨመርባቸው ሃገራት መሆናቸውን ገልጿል። 
በኩፍኝ ወረርሽኝ ሳቢያ ሶስት አራተኛውን ድርሻ ከያዙ 10 ሀገራት ውስጥም ሶስቱ ሃገራት አሉበት። ከነዚህ ሀገራት በተጨማሪ የኢትዮጵያ ጎረቤት ሱዳን፣ የመን፣ ቤንዙዌላ፣ ሰርቢያ፣ ማዳጋስካር፣ ሱዳን፣ ታይላንድ እና አውሮፓዊቷ ፈረንሳይ በዝርዝሩ ውስጥ ተካተውዋል።
በኢትዮጵያ ላለፉት ሶስት ዓመታት የኩፍኝ በሽታ ስርጭት 80 በመቶ መቀነሱን በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የክትባት ፕሮግራም አስተባባሪና በእናቶችና ሕጻናት ዳይሬክቶሬት ምክትል ዳይሬክተር ወ/ሮ ሊያ ወንደወሰን ይናገራሉ። ከ1972 ዓ,ም ጀምሮ በኢትዮጵያ የኩፍኝ ክትባት እየተሰጠ እንደሚገኝ ጠቅሰው ስርጭቱንም ከዚህ በታች እንዲቀንስ እየተሰራ እንደሆነም ይገልጻሉ። 

«የኩፍኝ በሽታ በኢትዮጵያ እየቀነሰ መቷል። ላለፉት ሶስት ዓመታት እኤአ በ2015 እስከ 2018 በከፍተኛ ደረጃ በሽታውን መቀነስ ችለናል። ከዛ በፊት በነበሩት ዓመታት ከፍተኛ የኩፍኝ ወረርሽኝ የተከሰተበት ወቅት ነበር። በወቅቱ ተከስቶ በነበረው ድርቅ ጋር ተያይዞ ነው። ከዛ በኋላም የኩፍኝ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ቢከሰትም፤ ከኩፍኝ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ሞት እና ህመምን መቀነስ ችለናል። የበሽታውን ስርጭት ከ80 በመቶ በክትባት አማካኝነት ለመቀነስ ተችሏል። ስርጭቱ በ2018 እኤአ ከ1 ሚሊዮን ህዝብ 14 ነበር። ወደፊት ከአንድ ባነሰ ለማድረስ እቅድ አለን። የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሁለተኛ ዙር የክትባት አገልግሎት ለመስጠት አዲስ የክትባት ፕሮግራም ጀምሯል። በዘጠኝ ወር ይሰጥ የነበረውን የሕጻናት የኩፍኝ ክትባት በድጋሜ በ15 ወር በድጋሜ ይሰጣል። የሕጻናቱ የበሽታውን የመከላከል አቅም ይበልጥ ለማጎልበትም ይረዳል። በሁሉም የሀገራችን ክልሎች ክትባቱን እናሰራጫለን።»

Masern-Virus
ምስል Imago/Science Photo Library

የክትባት ሽፋናችን ለማረጋገጥ ይረጃ ዘንድ መረጃዎችን ኅብረተሰቡ በተገቢው መንገድ መያዝ እንዳለበት የሚያሳስቡት ወ/ሮ ሊያ ማህበረሰቡም ይሄን እንዲገነዘብ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።  
በሕጻናት ህመምና ሞትን ከሚያስከትሉ ተላላፊ በሽታዎች አንዱ እንደሆነ የሚገልጹት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህክምና ክፍል የሕጻናት ህክምና ረዳት ፕሮፌሰር እና የህጻናት ተላላፊ በሽታዎች ከፍተኛ ባለሙያ ዶ/ር ትንሣኤ አለማየሁ ናቸው። በሽታው ከፍተኛ ተጓዳኝ የጤና ችግርም እንደሚያስከትል ይገልጻሉ።

«በሕጻናቱ ላይ ከፍተኛ ህመምና ሞት ከሚያስከትሉ ተላላፊ በሽታዎች አንዱ ነው። ከእራስ ጀምሮ ወደ ሆድ ከዛ ወደ እግር ደረጃ በደረጃ የሚወርድ ሽፍታ፣ የዓይን መቅላት፣ ንፍጥና አልፎ አልፎ የሚከሰት ሳል የበሽታው የመጀመሪያዎቹ ምልክቶች ናቸው። ህመምተኛው ህክምና ካላገኘ በሽታው ከጀመረ ቀን አንስቶ እስከ ጥቂት ቀናት የሚያስከትላቸው ጉዳቶች ሲኖሩ ዓመታትን ቆይቶ የሚያስከትለውም ጉዳቶች አሉ። በተወሰኑ ሳምንታት ውስጥ የማጅራት ገትር፣ የመተንፈሻ አካላት ኢንፌክሽኖች፣ የበሽታ መከላከል አቅም መቀነስ፣ ተቅማጥን ያስከትላል። ሊታከም የማይችል የቅንጭላት ጉዳትን ጨምሮ ሊከሰት ይችላል።
የመተላለፊያ መንገዱ ዋናው በትንፋሽ እንዲሁም በንኪኪ ፤ በሽታው ከታየ የመጀመሪያዎቹ 5 ቀናት በንኪኪ እንዳይተላለፍ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል። በአየር መተላለፊያ መንገዶቹን መቀነስ ማስክ ማድረግ ያስፈልጋል። ሆኖም በዋናነት የበሽታው መከላከያ መንገዱ ክትባት ነው።»

የበሽታው ብቸኛ መከላከያ መንገድ ክትባት እንደመሆኑ፤ ወላጆች ልጆቻቸውን በተገቢው ዕድሜ የመከላከያ ክትባት ተከታትለው ማስከተብ እንዳለባቸው ዶ/ር ትንሣኤ ያስገነዝባሉ።

ነጃት ኢብራሂም 

ተስፋለም ወልደየስ