1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኪሊማንጃሮ ተራራ በሰደድ እሳት መያያዝ እና የአካባቢው ስነምህዳር

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 7 2013

ባለፈው እሁድ ምሽት የታንዛንያ ብሔራዊ ፓርክን የሚያስተዳድረው ባለ ሥልጣን በዓለማችን በትልቅነቱ አንዱ ስለሆነው የኪሊማንጃሮ ተራራ አስደንጋጭ ምስል በትዊተር ገጹ ላይ አወጣ። በእርግጥ ነው በትዊተር ገጹ ላይ የሰፈረው ምስል ዝርዝር ጉዳይ አልያዘም ።

https://p.dw.com/p/3k4rv
Satellitenbild Feuer auf Kilimandscharo, Tansania
ምስል Planet Labs Inc.

የኪሊማንጃሮ ተራራ በሰደድ እሳት መያያዝ እና የአካባቢው ስነምህዳር

ባለፈው እሁድ ምሽት የታንዛንያ ብሔራዊ ፓርክን የሚያስተዳድረው ባለ ሥልጣን በዓለማችን በትልቅነቱ አንዱ ስለሆነው የኪሊማንጃሮ ተራራ አስደንጋጭ ምስል በትዊተር ገጹ ላይ አወጣ። በእርግጥ ነው በትዊተር ገጹ ላይ የሰፈረው ምስል ዝርዝር ጉዳይ አልያዘም ። በዚያ በምሥራቅ አፍሪካ የሣር ምድር ከፍ ብሎ የሚታየው እና ባለ ግርማ ሞገሡ ተራራ ምን እንደገጠመው በወቅቱ ማንም መገመት አልቻለም ነበር። ነገር ግን ቆይቶ እንደተረጋገጠው ከኪሊማንጃሮ ተራራ አጋማሽ አካባቢ ሽቅብ የሚወናጨፍ የእሳት ነበልባል ታይቷል። በኪሊማንጃሮ ተራራ እና በአካባቢው የሰደድ እሳት ሲከሰት የመጀመርያው አልነበረም። ቀደም ሲል በተራራው ግርጌ እና በአቅራቢያው የነበረውን ደን ያቃጠለ ነገር ግን በቁጥጥር ስር የዋለ የሰደድ እሳት ተከስቶ ነበር። ነገር ግን የአካባቢው ባለ ሥልጣናት እንደሚሉት አሁን ከተራራው አጋማሽ ክፍል የተነሳው ቃጠሎ በቁጥጥር ስር ሳይውል ሦስተኛ ቀኑ ላይ ደርሶ፤ እስከ ዛሬ ከታዩት ብርቱ የእሳት አደጋዎች አንደኛው ሆኗል። ስለሁኔታው ናኦሚ ፌምባ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ ለDW ሲገልጹ

Tansania Feuer auf dem Kilimandscharo
ምስል DW/Veronica Natalis

«በኪሊማንጃሮ ተራራ ላይ የነበረ የተፈጥሮ ሃብት ተቃጠለ» ብለው ነው። «በአካባቢው የነበሩ የድንገተኛ የሰደድ እሳት ተከላካይ ሠራተኞች እሳቱን ለማጥፋት ብርቱ ጥረት እያደረጉ ቢሆንም ተጨማሪ ድጋፍ ካላገኙ እሳቱን በቁጥጥር ስር ማዋል አይቻላቸውም » በማለትም ሃሳባቸውን አክለዋል።

Tansania Kilimandscharo Brand
ምስል Tanzania National Parks/Reuters

የታንዛንያ ባለስልጣናት እንደሚሉት አንዳንዴ በአካባቢው በሚከሰት የመብረቅ አደጋ እና አልፎ አልፎ ሀገር ጎብኚዎች በሚፈጥሩት የጥንቃቄ ጉድለት የሰደድ እሳት ሊከሰት ይችላል። ነገር ግን በዚህ ዓመት የኮሮና ወረርሽኝ በፈጠረው ስጋት የሀገር ጎብኚዎች እንቅስቃሴ እጅጉን በመዳከሙ ለዚህኛው አደጋ በምክንያትነት ለማንሳት ሚዛን ላይደፋ ይችላል ይላሉ የታንዛንያ የአካባቢ ጥበቃ ኤጄንሲ ኃላፊ ፍራንክ ሉቬንዳ ።

« በኪሊማንጃሮ ተራራ ላይ የተነሳው የሰደድ እሳት መንስኤው አሁንም ድረስ በእርግጥ አልታወቀም። ነገር ግን በተደጋጋሚ በአካባቢው የሚከሰተው የሰደድ እሳት አንዳች መልዕክት መተው አልቀረም።»

Tansania Kilimandscharo Brand
ምስል Tanzania National Parks/Reuters

የኪሊማንጃሮ  ተራራ በስፍራው ብቻ የሚገኙ የበርካታ ብርቅዬ እንስሳት እና ዕጽዋት መኖርያ ነው። በየዓመቱም ከመላው ዓለም በሺዎች የሚቆጠሩ ሀገር ጎቢኚዎች እጅግ ቀዝቃዛ እና አዳጋች ወደሆነው የተራራውን ጫፍ በመውጣት አልያም በዙርያው የሚገኙትን የተፈጥሮ ገጸ በረከቶች ይጎበኛሉ። ይህ የብርቅዬ እንስሳት እና ዕጽዋት መገኛ ተራራ ላይ የቃጠሎ አደጋ መድረሱ በተራራው ብዝኃ ሕይወት እና ስነ ምህዳር  ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተጽዕኖ ምን ይሆን ስትል የዶይቸ ቬለዋ ኤሊዮት ዳግላስ ትጠይቃለች።

በተራራው ላይ ለስድስት ዓመታት የስነምህዳር የምርምር ፕሮጀክት የመሩት በጀርመን ዩኒቨርሲቲ ቩርዝበርግ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ስነምህዳር እና የትሮፒካል ባዮሎጂ (የሞቃታማ አካባቢዎች ስነ ፍጥረት ) መምሕር የሆኑት ዶ/ር ማርሴል ፒተርስ እንደሚሉት

« በሞቃታማ አካባቢዎች በሚገኙ ተራሮች ላይ ከፍ እያሉ በሔዱ ቁጥር አስደማሚ እና በሌሎች አካባቢዎች የማይገኙ የእንስሳት ዝርያዎችን ማየት ይቻላል»። ነገር ግን በኪሊማንጃሮ ተራራ ላይ እምብዛም ነው ይላሉ ፕሮፌሰሩ ። በዚህም «በተራራው ላይ የተከሰተው ቃጠሎ በሌሎች አካባቢዎች የማይገኙ እንስሳትን የማግኘት ዕድሉ አነስተኛ ነው » ይላሉ። ወጣቱ ተራራ ተብሎ በሚታወቀው የኪሊማንጃሮ ተራራ ላይ የተከሰተው የሰደድ እሳት በብዝኃ ሕይወት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ እንዳለ ሆኖ ዝርያን ከገጸ ምድር ያጠፋል የሚል እምነት ግን እንደሌላቸው ዶ/ር ማርሴል ተናግረዋል። ምክንያታቸውን ሲገልጹም « ከባሕር ጠለል በላይ ከ3,000 ሜትር ከፍታ በላይ ባሉ ተራሮች ላይ ያለው የዕጽዋት ስነ ምህዳር ዘርዘር ያለ በመሆኑ እሳቱ ገፍቶ ከባሕር ጠለል በላይ 5,895 ሜትር ከፍታ ወዳለው የተራራው ጫፍ ድረስ የመሄድ ዕድል አያገኝም»። የሆነ ሆኖ በተራራው ላይ የተነሳው የሰደድ እሳት ፈጣን እና ውጤታማ የድንገተኛ የሰደድ እሳት መቆጣጠር እና መከላከል የሚያስችል አቅም በአካባቢው ማደራጀት እንዳለበት አመላክቷል።

Tansania Berg Kilimanjaro
ምስል Finbarr O'Reilly/Reuters
Tansania Feuer auf dem Kilimandscharo
ምስል DW/Veronica Natalis

ታምራት ዲንሳ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ