1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

ዶ/ር ዛኪ በጉበት ካንሰር ላይ አተኩረዋል

ረቡዕ፣ ግንቦት 23 2009

በአዳጊነት ዕድሜያቸው ለትምህርት ወደ አሜሪካ ተጉዘው በዚያው የመምህርነት እና የምርምር ስራቸውን የቀጠሉት ኢትዮጵያዊው ዶ/ር ዛኪ ሸሪፍ በርካታ ሽልማቶችን እና ዕውቅናዎችን ከተለያዩ ተቋማት አግኝተዋል፡፡ በካንሰር በሽታ ላይ በሚያደርጉት ምርምር ይበልጥ የሚታወቁት ኢትዮጵያዊ ምሁር ባለፈው እሁድም ተጨማሪ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ 

https://p.dw.com/p/2dwJF
Zaki Sherif
ምስል Ethiotube

የካንሰር ተመራማሪው የ“ሲድ” ሽልማት አገኙ

መቀመጫውን በአሜሪካ ያደረገው እና ለትርፍ ያልተቋቋመው ማህበረ ግዩራን ዘረ ኢትዮጵያ (በምህጻሩ SEED) የተሰኘው ድርጅት ላለፉት 24 ዓመታት የማያስታጉለው ሁነት አለ፡፡ ዓመት እየቆጠረ በተለያዩ ዘርፍ ለተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ለህብረተሰቡ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ መዝኖ ሽልማት ይሰጣል፡፡ በዚህ ዓመትም ለስምንት ግለሰቦች ሽልማት አበርክቷል፡፡ አንጋፋው ድምጻዊ መሐሙድ አህመድ እና የጊዜው ኮከብ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ከተሸላሚዎቹ ዝርዝር መካተታቸው የእዚህ ዓመቱ ስነ ስርዓት ከሌላው ጊዜ በላቀ የብዙዎችን ትኩረት እንዲስብ አድርጓል፡፡ በሁለቱ የጥበብ ሰዎች ከተሸፈኑት ስድስት ተሸላሚዎች ውስጥ አንዱ የአካዳሚክ ሰው ናቸው፡፡ 

Spanien Krankenhaus Quironsalud in Torrevieja
ምስል Imago/Agencia EFE

ሙሉ ስማቸው ዶ/ር ዛኪ አብዱላሂ ሸሪፍ ነው፡፡ ዶ/ር ዛኪ በአሜሪካ ከፍ ያለ ቦታ ከሚሰጣቸው ዩኒቨርስቲዎች አንዱ በሆነው በዋሽንግተን ዲሲው የሀዋርድ ዩኒቨርስቲ ውስጥ መምህር ናቸው፡፡  ለዘንድሮው የ“ሲድ ሽልማት” የተመረጡበትን ምክንያት የእሁዱን የሽልማት ስነ-ስርዓት በአጋፋሪነት ስትመራ በነበረችው አርቲስት አለምጸሀይ ወዳጆ ቀርቦ ነበር፡፡ 

“ዶ/ር ዛኪ ገና በ14 ዓመቱ አላባማ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ገብቶ ከዚያም በተከታታይ ዕውቅ በሆኑ የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች በመመረቅ ውጤታማ የሆነ ሳይንቲስት እና ብርቅዬ ወገናችን ነው፡፡ በሙያው መስክ የተደነቀው እና የተከበረው ዶ/ር ዛኪ ሸሪፍ ለአቻቸዎቹ እና በመላው ዓለም ለሚገኙ ለብዙ የህክምና ባለሙያዎች መምህር፣ አርአያም የሆነም ሰው ነው፡፡ SEED ይህን የተከበረ ምሁር በባዳር እና ሂጅራ ተቋሙ ለሰጠው ሰፊ አግልግሎቱ እና ለብቁ መሪነቱ፣ ከኢትዮጵያ ማህበረሰብ ውስጥ የተለያዩ የእምነት ተከታዮች በሰላም እና በፍቅር ህብር እንዲኖሩ እና እንዲሰሩ ላደረገው ቀና አስተዋጽኦ ያለውን አድናቆት እየገለጸ ልዩ የሆነውን የእውቀት ውጤቱን በውጪ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ክብርና አድናቆት በመሆኑም ጭምር የዘንድሮ ተሸላሚ አድርጎ ሲመርጠው በደስታ ነው” ስትል አለምጸሀይ በንባብ አሰምታለች፡፡ 

በሀዋርድ ዩኒቨርስቲ በባዮኬሜስትሪ እና ሞሎኪዩላር ባዮሎጂ የትምህርት ክፍል የሚያስተምሩት ዶ/ር ዛኪ ይበልጥኑ የሚታወቁት በካንሰር በሽታ ዙሪያ እያደረጉ ባለው ዘርፈ ብዙ ምርምር ነው፡፡ ከጡት እስከ ጉበት እና የማህጻን ጫፍ ድረስ ያሉ የካንሰር አይነቶች ላይ ጥናቶች አካሄደዋል፡፡ ሆኖም በአንድ እና በሁለት የሰውነት አካል ላይ ከማተኮር ይልቅ “የካንሰር በሽታ እንዴት ነው የሚጀምረው?” የሚለው ላይ አጠቃላይ ጥናት ማድረግን ይመርጣሉ፡፡ ለመሆኑ የካንሰር በሽታ ምንድነው? 

“ካንሰር አንድ በሽታ አይደለም፡፡ ካንሰር ምናልባት በአማርኛ ቂንጤ ልንለው እንችላለን፡፡ ይሄ ጂን የሚባለው  እንደ ፍሬ ነው እንግዲህ ህዋሳት ውስጥ የሚገኝ ዲንኤ የሚባለውን ሁሉ የሰውነታችን ህዋሳት ጠቅላላ የሚይዝ ነው፡፡ እርሱ ሲበላሽ፣ አንዷ እንኳ ብትበላሽ ቀስ በቀስ ህዋሳትን ከመጠን በላይ ታባዛለች፡፡ ሲባዙ ነው እንግዲህ መጨረሻ ላይ ካንሰር (ቂንጤ) ይሁንና ከዚያ በኋላ ያው ያብጣል፡፡ ያበጠው ቦታ ላይ ነው እንግዲህ ያ ሁሉ የምንበላው ምግብ፣ ያ ሁሉ ለሰውነት የሚያስፈልገው ገንቢ እና አልሚ የሆኑ ንጥረነገሮች በሙሉ ለካንሰሩ የሚሄደው፡፡ ለሰውነቱ አይሄድም፡፡ ይሄ እብጠቱ ነው በመጨረሻ ሰውን የሚገለው ማለት ነው” ሲሉ ዶ/ር ዛኪ ስለበሽታው ምንነት አጠር ባለ መልኩ ይገልጻሉ ፡፡ 

እንደ ዶ/ር ዛኪ ማብራሪያ እንደዚህ የተፈጠረ እብጠት በተጀመረበት ቦታ አይቀርም፡፡ እብጠቱ እያደገ ሲመጣ ወደ ደም ዝውውር ስርዓት ውስጥ ገብቶ በደም ስር እንደሚተላለፍ ይናገራሉ፡፡ ካንሰር ብዙውን ጊዜ ከጡት ተነስቶ ወደ ሳንባ እንደሚሄድም ያስረዳሉ፡፡ “ፓቶሎጂስት” የሚባሉ የህክምና ባለሙያዎች ከዚህን መሰል እብጠት ህዋሳት ወስደው በመመርመር “በቅርጹ እና በአይነቱ” ካንሰሩ መጀመሪያ የተነሳው ከጡት ይሁን ከሌላ ቦታ መለየት እንደሚችሉም ያብራራሉ፡፡ ብዙ ሰዎች የጡት ካንሰር ሲባል የሴቶች ችግር ብቻ እንደሚመስላቸው የሚናገሩት ዶ/ር ዛኪ በወንዶች ላይም ሊከሰት እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ለስራ ጉዳይ ሲሄዱ ያጋጠማቸው ለአንድ ጥናታቸው መነሻ እንደሆናቸው ይገልጻሉ፡፡ 

Krebs Krebszelle Illustration Lungenkrebs
ምስል Imago/Science Photo Library

“ኢትዮጵያ በነበርኩ ጊዜ ያናገርኳቸው የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ኦንኮሎጂስት ዶክተር የወንድ የጡት ካንሰር ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም የላቀ ቦታ እየያዘ ነው ብለውኝ ነበር፡፡ ያዳበረ ባይሆንም ወንዶችም ጡት አለን፡፡ ጡታችን ውስጥ ያሉት ህዋሳቶች በካንሰር በኩል ሊበከሉ ይችላሉ፡፡ እና በዚያን ጊዜ በጣም አሳሳበኝ፡፡ እንዴት ኢትዮጵያ ውስጥ በወንዶች ላይ እየበዛ መጣ? ብዬ አንድ ማመልከቻ ለተባበሩት መንግስታት እና እዚህ አሜሪካ ላለው ብሔራዊ የጤና ተቋም አስገብቼ ነበር፡፡ ገንዘብ ለማግኘት፡፡ ኢትዮጵያም ሰው ልኬ ወይም ራሴም ሄጄ ህዋሳቶችን ከበሽተኞቹ ሰብስቤ ከዚያ በኋላ እዚህ መጥቼ ምርመራ ለማድረግ  እና በተቻለ መጠን እዚያ ያሉትም ዶክተሮች በዚህ ዓይነት ሁኔታ አስገብቼ እንደው በየጊዜው እየተላላክንም ቢሆን አንድ ቦታ ላይ ለመድረስ ነበር ያሰብኩት፡፡ የገንዘብ ድጋፉ እስከዚህም ተጨባጭ የሆነ መልስ አላገኘምና በዚያው ለጊዜው ትቼዋለሁ” ይላሉ ተመራማሪው፡፡ 

ዶ/ር ዛኪ በወንዶች የጡት ካንሰር ላይ የጀመሩትን ምርምር በመጽሀፍ መደርደሪያቸው ላይ አኑረው እጃቸው አጣጥፈው ቁጭ አላሉም፡፡ ይልቅስ ከዚህ ቀደም በስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ ስኩል ኦፍ ሜዲሲን በነበሩበት ወቅት ወደ ጀመሩት ጥናት ተመለሱ፡፡ የስታንፎርዱ ጥናታቸው አንድ ቤተሰብ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በዚህ ቤተሰብ ውስጥ የተወለዱ ስምንት ልጆች በሙሉ በካንሰር በሽታ ተጠቅተዋል፡፡ ዶ/ር ዛኪ የእዚህን ለየት ያለ ቤተሰብ የኋላ ታሪክ ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር ሆነው ሲፈተሹ እስከ አያት እና ቅድመ አያት ድረስ በተለያዩ ዓይነት የካንሰር በሽታዎች ተጠቅተው ያገኛሉ፡፡

የቤተሰቡ የህክምና ዶሴ የ“ካንሰር አመጣጥ እንዴት ነው?” ለሚለው የተማራማሪዎች የዘወትር ጥያቄ ፍንጭ ያቀብል እንደው በማለት ምርምሩ ቀጠለ፡፡ ከዚያ ቀደም እንዲህ አይነት ማሳያዎች ተለይተው ምርምር ይደረግ የነበረው በአይጦች ላይ ነበር፡፡ ዶ/ር ዛኪን ስለካንሰር መነሻ በሰዎች ላይ የጀመሩት ምርምር በጉበት ካንሰር ላይ ወዳተኮረው እና አሁን በማካሄድ ላይ ወደሚገኙት ምርምር መራቸው፡፡ ለምን ጉበትን መረጡ?

“የጉበቱን ለማጥናት የፈለግሁት ብዙ ጊዜ የጉበት ካንሰር ሲኖር ግዴታ ትልቅ መርፌ ከቆዳ በኩል ተጀምሮ ወደ ጉበቱ ተልኮ ትንሽ ህዋሳትን ያወጡና በዚያው ይለኩታል፤ በማይክሮስኮፕ ያዩታል፡፡ ፓቶሎጂስቶች ናቸው ካንሰር መሆኑን የሚለዩት፡፡ እና በዚያን ጊዜ ደግሞ ያንን ጉበት ለማዳን ረፍዷል ማለት ነው፡፡ የእኔ ስራ ምንድን ነበር ባዮ ማርከር የሚባሉ ምልክቶች በደም የሚገኙ ከሆነ ለመለየት ነበር፡፡ ይሄ ጉበት ወደ ካንሰር ሙሉ ለሙሉ ከመቀየሩ በፊት አስቀድመን እንኳን ትንሽ ምልክቶችን በደም ብናይ እና በደም ብቻ መለካት የሚቻል ከሆነ በዚያ ምክንያት ነው እንግዲህ ወደ ጉበት የሄድኩት” ሲሉ ምክንያታቸውን ያስረዳሉ፡፡

Krebs Krebszelle Illustration Darmkrebs
ምስል Imago/blickwinkel

እነዚህን ጥቃቅን የሆኑ ምልክቶችን (ባዮ ማርከር) ከሰውነት አውጥቶ ለመመልከት ታዲያ ዋጋቸው የማይቀመስ መመርመሪያ ማሽኖች ያስፈልጋሉ፡፡ ዶ/ር ዛኪ አሁን በቤተ-ሙከራቸው ውስጥ እየተጠቀሙባቸው ያሏቸው ሶስት ማሽኖች ድምር ዋጋ 740 ሺህ ዶላር ግድም እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ማሽኖቹን ለመግዛት እና ለምርምሩ የሚወጣው ከበድ ያለ ገንዘብ ደግሞ እንዲህ አይነት ምርምሮችን በገንዘብ በሚደግፉ ተቋማት አማካኝነት ካልተሸፈነ ልክ እንደ ጡት ካንሰር ምርምሩ በውጥን የሚቀር ይሆናል፡፡

ዶ/ር ዛኪ በጉበት ላይ ለሚያደርጉት ምርምር ለአሜሪካ ብሔራዊ የጤና ተቋም ያስገቡት ማመልከቻ ከበርካታ ተመራማሪዎች እቅድ ጋር ተወዳድሮ በመመረጡ የ1.5 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ አሸናፊ ሆኗል፡፡ አሁን በሚገኙበት ሀዋርድ እና በቀድሞው ዩኒቨርስቲያቸው ጆርጅታውን በትብብር የሚሰራ እርሳቸውን ጨምሮ በ15 ተመራማሪዎች እየተደረገ ያለ ሌላ የካንሰር ጥናት ደግሞ 28 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ አግኝቷል፡፡ የእዚህ ምርምር ትኩረት ምንድነው?፡፡

“በአሜሪካን በሚኖሩ ጥቁሮች እና በነጮች መካከል የጉበት ካንሰር እንዴት ሊለይ ይችላል? ምክንያቱም ብዙ ጥናቶች የሚያሳዩት የተበከለው ጂንም የተለየ ነው፡፡ እንደምናውቀው የአካባቢ፣ የመኖሪያ ሁኔታዎችም ትንሽ የተለያዩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የምግብ አበላሉም ያው ከአካባቢ ጋር የተካተተ ነው፡፡ በእነዚህ ሁለቱ [የካንሰር ምልክቶች] ባዮማርከር ማግኘት ይቻላል ወይ? በጆርጅ ታውን የጉበት ካንሰር ካለባቸው ነጮች ህዋሳቶች እና ደም እየሰበሰብን ሲሆን እዚህ ሀዋርድ ዩኒቨርስቲ ደግሞ የጥቁሮችን ደም እና ህዋሳቶች እየሰበሰብን ነው፡፡ እና በዚያ አንጻር ነው እንግዲህ ስራውን የምንሰራው፡፡ አንድ ሰው የሚሰራው አይደለም፡፡ ተማሪዎችም አሉኝ” ይላሉ ዶ/ር ዛኪ፡፡ 

ለአምስት ዓመት የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያገኝ ቃል የተገባለት ይሄ ምርምር ሁለተኛ ዓመቱን በማገባደድ ላይ ይገኛል፡፡ እነዶ/ር ዛኪ በሳይንስ ጆርናሎች ላይ አዲስ ግኝታቸውን ገና ባያሳትሙም አካሄዳቸው ግን ተስፋ ሰጪ አንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ሰውነታችን ፕሮቲን፣ ካርቦ ሃይድሬት፣ ኒውክሊክ አሲድ እና ስብ (ፋት) ከተሰኙ ግዙፍ የሆኑ ጠቃሚ ባዮሞሎኪዮሎች ውጭ መስራት እንደማይችል የሚናገሩት ዶ/ር ዛኪ የእነርሱ ጥናት አለቅጥ ሲከማች ካንሰር በሚያመጣው ስብ ላይ ያተኮረ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡   

“ይሄ ስብ (ፋት) ለሰውነታችን ለብዙ ነገር ይጠቅማል፡፡ ህዋሳቶች ራሳቸው ዙሪያቸው የተከበበው በስብ ነው፡፡ እና እነዚህ ሰውነትንም ይጠብቃሉ፡፡ በተመሳሳይ ጊዜም አንዳንድ ገንቢ የሆኑ ነገሮች በእነዚህ በሜንብሬን በተከበቡ ነገሮች ወደ ህዋሳት ውስጥ ለመግባት ያስችላቸዋል፡፡ ኮሌስትሮልም በዚያ ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡ ስብ ሲባል በጣም ብዙ ክፍፍሎች አሉት፡፡ ግን ይሄ የተከማቹ ስብ (ሳቹሬትድ ፋት) የሚባሉ በሃይድሮጅን አቶም የተከበቡ አሉ፡፡ እነዚህ ሳቹሬትድ ብዙ ጊዜ  ትርፍ ነው የሚሆኑት፡፡ ትርፍ ሲሆኑ ደግሞ ያው ይከማቻሉ፡፡ ሲከማቹ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ የተለመደ ሂደትን ያግዳሉ፡፡ የሚበክሏቸው ህዋሳት ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በመጨረሻ ግን ውስጣቸው ያለው ኬሚካሎች እነሱ ናቸው ጉዳት ሊያመጡ የሚችሉት፡፡ አሁን እኛ ለማሳተም የምንፈልገው ትክክለኛ ኬሚካሎችን በመለየት እና በመጥቀስ ነው” ሲሉ በጥናታቸው ሊደርሱበት ስለሚፈልጉት ግኝት ይገልጻሉ፡፡

Wellcome Image Awards MicroRNA scaffold cancer therapy (João Conde, Nuria Oliva und Natalie Artzi/Massachusetts Institute of Technology (MIT))
ምስል João Conde, Nuria Oliva und Natalie Artzi/Massachusetts Institute of Technology (MIT)

ዶ/ር ዛኪ ከዚህ በተጨማሪ መጠጥ በማይጠጡ ሰዎች ላይ ስለሚከሰት የጉበት ካንሰር ምርምር እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ቀደምት ጥናቶቻቸው በእውቅ የሳይንስ ጆርናሎች ላይ የታተሙላቸው ኢትዮጵያዊው ተመራማሪ ከተለያዩ የሙያ ተቋማት ዕውቅና እና ሽልማቶች ተሰጥቷቸዋል፡፡ ባለፈው እሁድ ከ SEED የተበረከተላቸው ሽልማት ግን ለየት ያለ ስሜት እንዳሳደረባቸው ይናገራሉ፡፡

“እንግዲህ ይሄ ሽልማቱ በተለይ ኢትዮጵያውያን በሙያቸው አስተዋጽኦ ያደረጉ በዚያ አንጻር ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያውያን ነው ይሄ ሽልማት የተሰጠው፡፡ እኔ ብዙ ጊዜ በሙያዬ በሳይንስ እና ህክምና በኩል፣ በጤና አካባቢ ሽልማት አግኝቻለሁ፡፡ ቢሮዬም በዚያ ነው ያጌጠው፡፡ ብዙ ነገር ነው ያለው ግን ስሜቱ አንድ አይደለም፡፡ ከኢትዮጵያውያን ዕውቅና ተገኝቶበት፣ ያደረግኸው፣ ያበረከትኸው ነገር ጥሩ ነው ለእኛም ያኮራናል ብሎ መናገሩ ትልቅ እና የተለየ ደረጃ ነው የሚሰጠው፡፡ እና በዚያ አንጻር ስሜቱም የተለየ ነው የሆነው” ይላሉ ዶ/ር ዛኪ፡፡
 

ተስፋለም ወልደየስ

ኂሩት መለሰ