1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የካጋሜ መሪነትና የሩዋንዳ ሥጋት

ሐሙስ፣ ነሐሴ 22 2006

የሩዋንዳ ከፍተኛ ባለስልጣናት በያዝነዉ ሳምንት መጀመርያ ለእስር ተዳርገዋል፤ በርካታ ሰዎችም ያሉበት ቦታ አይታወቅም። የደረሱበት እስካሁን ያልታወቁት ዜጎች ከመንግሥት ተቃዋሚ ወገን ብቻ ሳይሆን፤ ከደጋፊዎችም በኩል መሆኑ ተመልክቶአል። በዚህም ምክንያት የፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ የአገዛዛዊ መንግሥት ሃገሪቱን ሥጋት ላይ መጣሉ እየተነገረ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1D399
Paul Kagame
ምስል Reuters

የዛሬ ወር ግድም የሩዋንዳዉ ፕሬዚዳንት ፓዉል ካጋሜ የሃገሪቱን ካቢኔ መበተናቸዉ ይታወቃል። ፕሬዚዳንት ካጋሜ በአዲስ ያደራጁት ካቢኔ ለሃገሪቱ እድገትና ብልፅ እንደሚያስገኝ ተናግረዉ ነበር። በአዲስ የተቋቋመዉ የሃገሪቱ ካቢኔ ግን፤ ብዙ አዲስ ነገሮችን ይዞ ብቅ ብሏል ሲሉ ነዉ፤ በሃገሪቱ የሚገኙ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ቅሪታቸዉን እያሰሙ የሚገኙት። በያዝነዉ ሳምንት መጀመርያ ሰኞ፤ የሩዋንዳ መንግሥት ወታደር ሶስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ለእስር ተዳርገዋል። ከታሰሩት የሃገሪቱ ባለስልጣናት መካከል፤ «በሩዋንዳ ደህንነት ላይ ከፍተኛ ጥቃት ጥለዋል» በሚል ክስ የተመሰረተባቸዉ፤ የሃገሪቱ የደህንነት ባለስልጣን ቶም ባይባጋምባ ይገኙበታል።

ካጋሜ በሃገሪቱ አዲስ ካቢኔን ካቋቋሙ ወዲህ፤ በሃገሪቱ በፀጥታ ጥበቃ ፖሊሶች መነፅር ዉስጥ የገቡት የተቃዋሚ ፓርቲ ደጋፊዎች ብቻ ሳይሆኑ፤ በመንግስት የተወነጀሉ ፕሬዚዳንት ካጋሜ የቀድሞ አገልጋዮችም ናቸዉ። በሃንቡርግ ዩንቨርስቲ የማኅበረሰብ ዓለማቀፍ ህግ ጥናት ተቋም ባልደረባ ጌርድ ሃንክል እንደሚሉት በካጋሜ ደጋፊዎች መካከል የሚታየዉ መደጋገፍ እጅግ አቆልቁሎአል፤

Symbolbild Ruanda Polizei
ምስል Getty Images/Afp/Jose Cendon

« በራሳቸዉ ደጋፊዎች መካከል የሚታየዉ መተማመን እና ደጋገፍ እጅግ አቆልቁሎአል። የካጋሚ ስልጣን እና የአመራር ሂደት እጅግ አጠያያቂ እና አጨቃጫቂ ሆንዋአል። በሩዋንዳ እና በመንግሥት ቅርብ ተጠሪዎች አካባቢ የሚነገረዉ ነገር ሁሉ ተግባራዊ አይሆንም። ነዋሪዉ የሆነ የሚታይ የወደፊት እርምጃን ይጠብቃል»

እንደ ሃንክል በሃገሪቱ ከፍተኛ እርምጃ እና መሻሻል ይጠበቅ ነበር። ለምሳሌ እንደ ስልጣን ማጋራት አልያም፤ በሃገሪቱ ዲሞክራሲን ማስፈን የመሳሰሉ ነገሮች ። እንዳለመታደል ሆኖ ግን ከ14 ዓመት በላይ የመንግሥት ተጠሪ ሆነዉ የሚያገለግሉት ፓዉል ካጋሜና ሃገራቸዉ ሩዋንዳ ለዚህ ጉዳይ ገና የቀረቡ አይመስልም።

በመካከለኛዉ አፍሪቃ የክርስትያን ህብረት ተቋም አስተባባሪ ጊዚንደ አምስ እንደሚሉት በሩዋንዳ የሚታየዉ የሰብዓዊ መብት ይዞታ አሳሳቢ ነዉ « በሩዋንዳ በሚገኙ የብዙሃን መገናኛዎች እና የመንግሥት ተቃዋሚዎች ላይ የሚታየዉ የሰብዓዊ መብት ይዞታ አሳሳቢ መሆኑን ለዓመታት ታዝበናል»

እንደ ጊዚንደ በሩዋንዳ ነፃ ሚኒዲያ የለም። በሃገሪቱ ለመንግሥት ልሳን ሆኖ የሚያገለግል፤ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለ ብዙሃን መገናኛ ብቻ ነዉ የሚደመጠዉ። በመንግሥት ተቃዋሚዎች ላይ የሚደረገዉ ርምጃም ቢሆን ተመሳሳይ ነዉ። ፕሬዚዳንት ካጋሜን ለመቃወም ሲሞክሩ፤ የተቃዋሚዉ ፓርቲ ተጠሪ ታስረዉ፤ እድሜ ይፍታህ ተበይኖባቸዋል፤ ሲሉ በመካከለኛዉ አፍሪቃ የክርስትያን ኅብረት ተቋም አስተባባሪ ጊዚንደ አምስ ለ ዶቼ ቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ ገልፀዋል።

በሩዋንዳ እየሰፋ የመጣዉ የዴሞክራሲ ንቅናቄን የሚያራምደዉ የመንግሥት ተቀናቃኙ የአረንጓዴዉ ፓርቲ፤ ከመንግሥት በኩል በሚጣልበት ብትር እየጠበበና፤ አደባባይ መዉጣቱን እየገታ መጥቶአል። ካሳለፍነዉ ሐምሌ ወር ጀምሮ የፓርቲዉ ዋና ተጠሪ ዳማሴነ ሙንያሻካ፤ የገቡበት ቦታ አይታወቅም። ካጋሜ የሚያስተዳድሩት የሩዋንዳ መንግሥት በበኩሉ በግለሰቡ መጥፋት እጁ እንደሌለበት አስታዉቋል። የሩዋንዳ ደህንነት ሚኒስትር ፤ ፋዳህሊ ሃሪማናም ይህንኑ ነዉ የሚያረጋግጡት፤

« ይህ አይነቱ አካሄድ የመንግሥትን ስም ለማጉደፍ የሚደረግ እርምጃ ብቻ ነዉ። ከኛ ጋር ሰዎች ዝም ብለዉ አይጠፉም። ግን በአንዳንድ ወንጀሎች ያሰርናቸዉ ሰዎችም አሉ። ሰዎች በጥርጣሪ ተይዘዉ ለምርመራ ታስረዉ በሚገኙበት ግዜ፤ አንዳንዶች ዘመዶቻቸዉ ጠፍተዋል ብለዉ ያወራሉ»

ይህን ሁኔታ መቀመጫዉን በዩኤስ አሜሪካ ያደረገዉ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅት Human Rights Watch በሌላ ሁኔታ ነዉ የሚመለከተዉ። ድርጅቱ በቅርቡ ባወጣዉ መዘርዝር መሰረት፤ « ካለፈዉ መጋቢት ወር ጀምሮ ከአስር የሚበልጡ የሩዋንዳ ዜጎች፤ የደረሱበት ቦታ አይታወቅም። ድርጅቱ ለነዚህ ዜጎች መሰወር የሃገሪቱን የፖሊስና የጦር ኃይል ይወነጅላል።

Symbolbild Ruanda Zeitung
ምስል Getty Images/Afp/Marco Longari

በሩዋንዳ መንግሥት ተቃዋሚዎች እና ሂስ አቅራቢዎች ላይ ለዓመታት የዘለቀ የማፈን እና ሃሳባቸዉን እንዳይገልፁ እና እንዳይንቀሳቀሱ የሚደረግ ሙከራ እንዳለ የፖለቲካ ታዛቢዎች ይገልፃሉ። ጀርመናዊዉ ዓለማቀፍ ህግ ጥናት ተቋም ባልደረባ ጌርድ ሃንክል እንደሚሉት፤ የካጋሚ ተቃዋሚዎች የሚገኙት በዉጭ ሃገራት ብቻ ሳይሆን በቅርቡ እንደታየዉ በቅራቢያቸዉ አብረዉ ከሚሰሩት ሰዎች ጭምርም ነዉ፤

«በካጋሜ ፖለቲካ ዉስጥ ብዙ አብረዋቸዉ የሚሰሩ ሰዎች በሳቸዉ የፖለቲካ መርህ አልተስማሙም። ሰዎች ይህን ለማሳየት ወይም ለመግለፅ ግን ምንም አይነት ገጠመኝን አላገኙም። ስለዚህ ዝም ብሎ አብሮ ለመስራት ተገደዋል»

በዓለም አቀፉ ዲፕሎማሲ መርህ ሩዋንዳን በሚመለከት ያለዉ አመለካከት ሃገሪቱ ባሳየችዉ የኤኮኖሚ እድገት፤ ሙስናን ለመዋጋት ባደረገችዉ ትግል አኳያ፤ ማበረታት ነዉ። ጀርመናዊዉ ዓለማቀፍ ህግ ጥናት ተቋም ባልደረባ ጌርድ ሃንክል፤ የሩዋንዳን ህዝብ ኑሮዉ እንዳልተመቻቸለት እና ሃብቱ በጥቂቶች ህግ ተሰብስቦ ነዉ የሚገኘዉ። በመካከለኛዉ አፍሪቃ የክርስትያን ህብረት ተቋም አስተባባሪ፤ ጌዚና አመስ እንዲሚሉት ከሆነ ሩዋንዳን በተመለከተ ከአዉሮጳዉያኑ እና ከጀርመን በኩል አንድ ግልፅ የሆነ አቋም ያስፈልጋል። ሩዋንዳ በሰብዓዊ መብት ይዞታ አኳያ፤ ትኩረት እንድታደርግ፤ በሩዋንዳ እና በለጋሽ ሃገሮች መካከል ዉይይት ማድረግ ያስፈልጋል።

ሽቴፈኒ ዲክሽታይን / አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ