1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኬንያ ዘመቻ እርዳታ ወይስ ወረራ!?

ዓርብ፣ ኅዳር 1 2004

በተለያዩ ጊዜያት ፤ በተለይ ደግሞ ከሶማልያ አክራሪ ቡድኖች በኩል ይቃጣባት የነበረውን ትንኮሳ ለረጅም ጊዜ ታግሣ የቆየችው ኬንያ፤ ከ 3 ሳምንት ገደማ በፊት፤ ብርቱ እርምጃ በመውሰድ፤ በአየር ኃይል የታገዘ መደበኛ ጦር ኃይል በማዝመት 100 ኪሎ ሜትር ዘልቃ መግባቷ የታወቀ ሆኗል።

https://p.dw.com/p/Rw50
ምስል dapd

መግባት ብቻ ሳይሆን በመሃልና ደቡብ ሶማልያ 3 ጠ/ግዛቶችን ያሥተሣሰረ ቀጣና ወይም ገሚስ ነጻ ግዛት በመመደብ ድንበሯን ከአደጋ የፀዳ ለማድረግ ማሳላሰሏም አልቀረም። ተክሌ የኋላ አንድ በአካባቢው የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ባለሙያ በማነጋገር የሚከተለውን ዘገባ አጠናቅሯል።

ኬንያ ፤ በጦር ኃይሏ የተቆጣጠረችው ቀጣና ፤ «ጁባላንድ» ወይም አዛንያ የሚል ስያሜም ሳያገኝ አልቀረም። የኬንያ እርምጃ፤ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ፤ በአፍሪቃም ኅብረት እንዴት ይታያል? ይህ የኬንያ እርምጃ ለሶማልያ ህዝብ እርዳታ ወይስ ወረራ ነው?

በናይሮቢ፤ ፤ የዓለም አቀፉ የፀጥታ ይዞታ ተማራማሪ ድርጅት (ISS)፤ የአፍሪቃው ቀንድ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑትን Andy Asamoah ን ጠይቄአቸው ነበር--

«እርግጥ ነው፤ ኬንያ ወደ ሶማልያ ለመግባት ተንቀሳቅሳለች። ዋና ዓላማዋ በወሰን አካባቢ ፤ ከሶማልያ በኩል፤ በታጠቁ ቡድኖች ሳቢያ የተፈጠረው ውጥረት እንዲረግብና ከአንግዲህ ወዲያ የኬንያ ግዛት እንዳይደፈር ለማድረግም ነው። ይህ እርምጃዋ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብእንዴት ይታይላ?! ለሚለው፤ በዛ ያሉ አገሮች፣ በተለይ የአካባቢው አገሮች ድጋፋቸውን ነው የገለጡት። ይህም በአፍሪቃ ኅብረት ጭምር ድጋፍ መሰጠቱን ልብ ይሏል፤ ኢ ጋ ድ ና የአካባቢው መንግሥታትም እንዲሁ! ከዚህ ድጋፍም ሆነ ስምምነት ሌላ፤ ኬንያ በእርግጥ ፤ ሉዓላዊ ግዛቷን የማስከብር መብት አላት። ወደ ሶማልያ ጦር በማዝመት በተጨማሪ የዜጎቿ ሰላምና ፀጥታ ዋስታና እንዲኖረው ለማብቃትም ተነሳስታለች።»

ኬንያ ሌላ አገር ውስጥ በመግባት ፤ ጦሯ በዚያ ለተወሰነ ጊዜ እንዲቆይ የወሰነች ይመስላል? ግን ምን ያህል የምትቆይ ይመስሎታል? ለምንስ ዓላማ ነው በዚያ የምትቆየው?

«ኬንያ አሁን ከታጣቂዎች ቁጥጥር ነጻ ያደረገቻቸውን ቦታዎች አስተማማኝ ፀጥታ እስኪያገኙ ድረስ ፣ በዚያ ለጥቂት ጊዜም ቢሆን መቆየት ግድ ሳይሆንባት አይቀርም። ቦታዎቹ ተመልሰው ከታጣቂዎች እጅ እንዳይወድቁ ! ስለዚህ ኬንያውያኑ በዚያ የሚቆዩበት ጊዜ የሚወሰነው፤ የዓላማቸውን መሳካት ቀላል ሆኖ ካገኙት ነው። ግን ቀላል አይሆንም። ምክንያቱም፤ ዓላማቸው ለውጥ ታይቶበታል። 100 ኪሎሜትር የመከላከያ ቀጣና ከመፍጠር ባሻገር፤ አሸባባን ፈጽሞ ከአገሪቱ ማጥፋት የሚል አቅድ ይዘዋልና!ይህ ፈተና የበዛበት ተግባር ነው የሚሆነው። እናም በዚያ ለመቆየት፤ ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል። ይህን የማድረጉ ችሎታ የሚመዘነው፣ በሥፍራው በሚያጋጥማቸው የተቃውሞ መጠንና ፣ የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ኃይሎች፣ ኬንያ ከአማጽያን የማታስለቅቀውን ቦታ ለመቆጣጠር በሚኖራቸው የብቃት ደረጃ የሚወሰን ይሆናል። እነዚህን ሁሉ በማሰላሰል፤ ማለት የምችለው፤ የኬንያ ጢጦር ኃይሎች፤ በቅርብ ጊዜ ወደአገራቸው እንደማይመለሱ ነው። በተለይ ነጻ ያወጡትን ፣ አሸባብ መልሶ እንዲቆጣጠረው ላለማድረግ እስከተነሱ ድረስ! ገና ብዙ ሥራ ነው የሚጠብቃቸው!»

ግን ይህ እርምጃ ወረራ ነው አያሰኝም ወይ? ከዓለም አቀፍ ህግ አኳያስ እንዴት ነው የሚታየው?

«ይህ እንደወረራ አይቆጠርም ወይ ለሚለው፣ እኔ እንደማየው፤ እስካሁን በሶማልያ ማኅበረሰብ በኩል፣ በሶማልያም፤ በኬንያም፤ በየትኛውም ሌላ ቦታ ድጋፍ ነው እየተሰጠ ያለው። ስለዚህም ብዙኀኑ ሶማሌዎች፤ ድርጊቱን እንደወረራ አይደለም የሚቆጥሩት ። ሌላው ቁም ነገር፤ የአሸባብ ወገኖች ደጋፊዎች ናቸው እስካሁን የኬንያን እርምጃ፣ ወረራ ነው የሚሉት፣ ይህ ደግሞ በየጊዜው እንደሚታየው፣ አሸባብ ለራሱ የሚዋጉለትን ደጋፊዎች ለመመልመል፣ ብሔራዊ ስሜትን በመቀስቀስ ነው የሚጠቀመው።»

ተክሌ የኋላ

ሒሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ