1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኬንያ ፕሬዝደንት እና «አይ ሲ ሲ»

ሰኞ፣ መስከረም 26 2007

የኬንያው ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ነው። የዛሬ ሰባት ዓመት ገደማ የኬንያ ምርጫን ተከትሎ በሃገሪቱ በተፈጠረው ፖለቲካዊ ቀውስና የብሄር ግጭት እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩት ፕሬዝደንቱ ወደ ዘሄግ ሲያቀኑ መንበረ ስልጣናቸውን በጊዜያዊነት ለምክትላቸው ዊሊያም ሩቶ ያስረክባሉ።

https://p.dw.com/p/1DRDS
Kenia Uhuru Kenyatta
ምስል picture-alliance/dpa

ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት (ICC) ተገኝተው ክሳቸውን እንደሚያደምጡ ለኬንያ ፓርላማ አስታውቀዋል። ፕሬዝደንቱ ዘሄግ በሚገኘው ፍርድ ቤት በተከሳሽነት ሲቆሙ ግን መንበረ ስልጣናቸውን በጊዜያዊነት ለምክትላቸው ዊሊያም ሩቶ አደራ አስቀምጠው ይሆናል።

ፕሬዝደንቱ በኬንያ ብሄራዊ ቴሌቭዥን በቀጥታ በተላለፈው የፓርላማ ንግግራቸው ካሁን ቀደም ግልጋሎት ላይ ያልዋለ የሕገ-መንግስት አንቀጽ በመጠቀም መንበረ ስልጣናቸውን ወደ ምክትላቸው ዊሊያም ሩቶ በጊያዜያዊነት እንደሚያስተላልፉ አስታውቀዋል። «በችሎቱ የምገኘው በኬንያ ፕሬዝዳንትነቴ አይደለም» ያሉት ኬንያታ በዚህ ፍርድ ቤት በተከሳሽነት መቆማቸው ከስልጣናቸውና ፕሬዝዳንታዊ ሥራቸው ጋር በፍጹም የሚገናኝ አይደለም ሲሉም ተደምጠዋል።

Kenia Präsident Kenyatta und Vizepräsident Ruto
ፕሬዝደንት ኬንያታና ምክትላቸዉ ሩቶምስል picture alliance/dpa

በስልጣን ላይ እያሉ ከዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት የቆሙ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት የሚሆኑት ኡሁሩ ኬንያታ ጉዳይ በኬንያውያን ዘንድ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኗል።

«ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ ወደ ሄግ መሄድ የለባቸውም ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም መጀመሪያ ክብራቸውን ዝቅ ማድረግ ይሆናል። ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ችሎቱን በቴሌ-ቪዲዮ እንዲከታተሉ ለምን እንደማይፈቅድላቸው አይገባኝም። ይህ ለአፍሪቃውያን መሪዎች ንቀት ነው ብዬ አስባለሁ። አፍሪቃዊ ፕሬዝዳንት ፍርድ ቤት መቅረቡም ተገቢ ነው ብዬ አላምንም።'»

«ይህ አሳፋሪ ነገር ነው። ለመላው አፍሪቃውያን ስድብ ነው። በጣም ሳዝኖኛል።»

«ወደ ፍርድ ቤቱ በመሄድ ዓለም አቀsፍ ገጽታቸውን ቢገነቡ ይሻላል። ጥፋተኛ መሆናቸዉ እስካልተረጋገጠ ድረስም ነጻ ናቸዉ።»

«ጉዳዩ ኬንያ ከቀረው አለም ጋር በሚኖራት ግንኙነት ላይ የረጅም ጊዜ ተጽዕኖ ይኖረዋል። እናም በእኔ እምነት ቢሄዱ ጠቃሚ ይሆናል።»

Niederlande Kenia Anhörung zu Gewalt nach Präsidentenwahl in den Haag William Samoei Ruto
ዊልያም ሳሙኤል ሩቶ በዴንሃግ ችሎትምስል AP

«'የተከሰሱባቸው ጉዳዮች ፕሬዝዳንት ከመሆናቸዉ በፊት የተፈጸሙ ናቸው። ፕሬዝዳንቱም ይሁን የሃገራችንን ሉዓላዊነት ሊከበር ይገባል ብዬ አምናለሁ። እርሳቸዉም ሕጉን ማክበር ይኖርባቸዋል። ይህ ለመላው ኬንያውያንና የዓለም ሰዎች ማንም ከሕግ በላይ አለመሆኑን ያሳያል።»

የኬንያው ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ የኬንያ ምርጫ ተከትሎ በ2007 እና 2008 የተፈጠረው ደም አፋሳሽ ግጭት አቀናብረዋል በሚል አምስት ክሶች ቀርበውባቸዋል። የ52 ዓመቱ ፕሬዝደንት በዚሁ የክስ ሂደት ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት ከችሎቱ ፊት ቀርበው ነበር።

ዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለል ተመልካች ፍርድ ቤት በዚህ የክስ ሂደት ተከሳሹ በአካል እንዲገኙ ችሎቱ በአብላጫ ድምጽ መወሰኑን መቀመጫውን በሄግ ያደረገው ፍርድ ቤት አስታውቋል። ፍርድ ቤቱ የኡሁሩ ኬንያታ ጠበቆች ጉዳያችንን ያስረዳልናል ያሉትን ማስረጃ እንድናቀርብ ጊዜ ይሰጠን ባሉት መሠረት ለጥቅምት ሰባት ተቀጥሮ የነበረውን ችሎት ወደ ጥቅምት ስምንት በመቀየር ተከሳሹ በአካል ተገኝተው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ጥሪ ማድረጉ አይዘነጋም።

ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታና ምክትላቸው ዊሊያም ሩቶ አቀናብረውታል በተባለው ግጭት 1,200 ኬንያውያን ለሞት ሲዳረጉ 600,000 ያህሉ ደግሞ መሰደዳቸው አይዘነጋም።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ