1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኬንያ ፕ/ምርጫና የሌሎች ሀገራት አስተያየት

ሰኞ፣ መጋቢት 2 2005

ኬንያውያን ባለፈው ሰኞ ምርጫ አከናውነው ኡሁሩ ኬንያታ አዲሱ ፕሬዚዳንታቸው እንዲሆኑ መርጠዋል። አዲሱ ፕሬዚዳንት የጦር ወንጀሎችን በሚከታተለው ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የሚጠየቁ መሆናቸውን ጨምሮ የኬንያውያን ምርጫ ውጤትን በተመለከተ የኢትዮጵያና የሌሎች ሀገራት አስተያየት ምን ይመስላል?

https://p.dw.com/p/17vAl
ምስል Reuters
Kenyatta Sieger der Präsidentenwahl in Kenia
ምስል REUTERS

ኬንያውያን አዲሱ ፕሬዚዳንታቸውን ባሳለፍነው ሰኞ መርጠዋል። የምርጫው ውጤት ከ5 ዓመት በፊት እንደነበረው በግጭት የተዋጠ ባይሆንም፤ ከውዝግብ ግን የፀዳ አልነበረም። ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ተፎካካሪያቸው ራይላ ኦዲንጋን ያሸነፉት በጠባብ ልዩነት ሲሆን፤ ኦዲንጋ የምርጫውን ውጤት እንደማይቀበሉት ተናግረዋል። የምርጫውን ሂደትና ውጤቱን አስመልክቶ የአፍሪቃ ኅብረት ዘገባው ስላልደረሰው መግለጫ ዛሬ መስጠት እንደማይችል ገልጿል። ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን በእንግሊዘኛ ምኅፃሩ ኢጋድ የወቅቱ መሪ ናት። በኬንያ ምርጫ ከመካሄዱ ጥቂት ቀደም ብሎም የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም የኢጋድ ሚንስትሮችን መርተው ወደ ኬንያ ማምራታቸው ይታወቃል። የመንግስት ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ኢትዮጵያ የኬንያ ወዳጅ መሆኗን በመጥቀስ ድጋፏን እንደምትገልፅ ዛሬ ለዶቼቨሌ ተናግረዋል።

የወንጀል ጉዳዮችን በሚመለከተው ዓለም አቀፉ ችሎት ክስ የቀረበባቸው የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ስልጣን ላይ ሆነው በሄጉ ፍርድ ቤት ከተከሰሱ ሰዎች መካከል ሁለተኛው መሆናቸው ነው። መቀመጫውን ሄግ ያደረገው ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት እስካሁን በስልጣን ላይ እያሉ ክስ የመሰረተባቸው የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር ነበሩ። የአሜሪካ ብሔራዊ ሬዲዮ ጣቢያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ የሚጠብቃቸው የምርጫ ውጤትን በመደለዝ የሚነሳ ክስ ብቻ አይደለም ሲል ዘግቧል።

«ኡሁሩ ኤንያታ በጦር ወንጀለኝነት በዓለም አቀፉ ሸንጎ ተከሰዋል»

አዲሱ የኬንያ ፕሬዚዳንት የወንጀል ጉዳዮችን በሚመለከተው ዓለም አቀፉ ችሎት የሚፈለጉ የመሆናቸው ጉዳይ ለኬንያና ለአካባቢው ሀገራት ምን መልዕክት ሊኖረው እንደሚችል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በዚህ መልኩ ይገልፃሉ።

የዛሬ አምስት ዓመት በኬንያ የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ የተቀሰቀሰውን የያኔው ሁከት በማስተባበር ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ተጠያቂ እንደሆኑ የሄጉ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ማስታወቁ ይታወቃል። በዚሁን ፍርድ ቤት የሚፈለጉት ኡሁሩ ኬንያታ የኬንያ ፕሬዚዳንት ሆነው የመመረጣቸው ሁኔታ ከኬንያ ጋ በፀጥታ እና በንግድ ትስስር ያላቸው ምዕራባውያንን ሳያሳስባቸው አልቀረም። ለዚያም ይመስላል የኬንያውያን የምርጫ ውጤት ተከትሎ አሜሪካንን ጨምሮ ምዕራባውያን ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ኡሁሩ ኬንያታን በስም ሳይጠቅሱ ኬንያውያንን እንኳን ደስ ያላችሁ ሲሉ ተደምጠዋል።


ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሂሩት መለሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ