1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርት

የክረምት ትምህርት አሰጣጥ እና የተማሪዎች ተሞክሮ

ዓርብ፣ ነሐሴ 24 2011

በዚህ ትምህርት ቤት በተዘጋበት የክረምት ወቅት ተማሪዎች ፊልም ማየት፣ መፅሀፍ ማንበብ ፣ከጓደኞች ጋር እንደልብ መገናኘት፣ ሌላም ሌላም እቅድ ይይዛሉ። ነገር ግን በርግጥ ተማሪዎች በዓመት ውስጥ ያላቸውን የዕረፍት ጊዜ እንደፈለጉ ያሳልፋሉ ወይስ በክረምት ወቅትም ለትምህርት ቤት ይዘጋጃሉ?

https://p.dw.com/p/3OlAc
kleine Mädchen in einer Schule in Tigray
ምስል DW

የክረምት ትምህርት አሰጣጥ እና የተማሪዎች ተሞክሮ

ኢትዮጵያ ውስጥ እንደየአካባቢው ከሁለት ወር እስከ ሁለት ወር ተኩል ድረስ በክረምት ወቅት ትምህርት ቤቶች ይዘጋሉ። ይህ ወቅት ተማሪዎች እና መምህራን በይፋ የሚያርፉበት ጊዜ ነው። ግን በርግጥ እንደዛ ነው? ሀፊዝ አደብ ዛሬ በአዳማ ዮንቨርስቲ የሁለተኛ ዓመት የኢንጂነሪንግ ተማሪ ነው።  በአንድ ወቅት ይኖርበት በነበረው የደሴ ከተማ ክረምቱን በትምህርት አሳልፏል። « ከስምንተኛ ወደ ዘጠነኛ ክፍል ሳልፍ ለማጠናከሪያ እንሆነኝ የክረምት ትምህርት ተምሬያለሁ» ይላል። ትምህርቱን  የተከታተለው  በፍላጎት ሳይሆን ቤተሰቦቹ እንዲማር ጫና ስላሳረፉበት ነው። ይሁንና ሀፊዝ ጊዜውን በክረምት ትምህርት ማሳለፉ ጠቅሞኛል እንጂ አልጎዳኝም ይላል። ያለ ማጠናከሪያው ትምህርትም ዮንቨርስቲውን ይቀላቀል እንደነበር የማይጠራጠረው ወጣት ዋናው ነገር« እንደ ግዴታ » አለማየት እንደሆነ ይናገራል።

ሰይድ ሲጀመር አንስቶ በክረምት ሰዓት በፍላጎት ነው የተማረው።  ዛሬ ለመምህራን የሚሰጠውን የክረምት ትምህርት በከፍተኛ ተቋም ይከታተላል። የመጨረሻ አመት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተማሪም ነው።  « በ2007 ዓም ክረምት ላይ ነው የጀመርኩት እና አምስት ክረምቶችን ተምሬያለሁ» ።ሰይድ በበጋ ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን የሳይንስ እና ባዮሎጂ ትምህርት ያስተምራል። ሰይድ መንግሥት ወጪያቸውን እየሸፈነ በክረምት ከሚያስተምራቸው መምህራን ውስጥ ለመካተት እድል ያላገኘው ለመማር በወሰነው ትምህርት ምክንያት ነው።

Äthiopien Addis Abeba Beschwerden über Abiturprüfung
ምስል DW/Solomon Muchie

የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴታ ወይዘሮ ፂዎን ተክሉ በክረምት ወቅት መምህራን የማስተርስ እና የዲግሪ ትምህርት እንዲሁም ዩንቨርስቲ ውስጥ የተለያዩ መርኃ ግብሮችን እንደሚወስዱ ለ DW ገልጸዋል። ከዚህም ሌላ ክልሎች የማጠናከሪያ ትምህርት እንደሚሰጡ ይናገራሉ።

ምንም እንኳን መምህራን እንደፈለጉት የአመት እረፍታቸውን መውሰድ ባይችሉም ቢያንስ በዚህ በጀርመን ሀገር መምህራን ረዥም የዕረፍት ጊዜ ካላቸው ሰራተኞች ውስጥ ይመደባሉ። በዚህ በአውሮፓውያኑ የበጋ ወቅት ብቻ ትምህርት ቤት ለስድስት ሳምንት ያህል ይዘጋል። ወደ ኢትዮጵያ ስንመለስ የ 27 ዓመቱ ይበይን ገብረኪዳን ይህንን የዕረፍት ጊዜውን ተጠቅሞ የትምህርት ደረጃውን ከሚያሻሽሉት መምህራን ሌላኛው ነው። በመደበኛ ጊዜው ወይም በበጋ የኬሚስትሪ መምህር ሲሆን  በክረምት ደግሞ በአክሱም ዮንቨርስቲ የኢኮኖሚክስ ተማሪ ነው። « ከዋጋው መወደድ በስተቀር የትምህርት አሰጣጡ ጥሩ ነው። መምህራኖቹ ኮርሱን በሚገባ ይሰጣሉ»  ይላል።ይበይንም በዚህ ዓመት ከሚመረቁት ተማሪዎች አንዱ ነው። የከፍተኛ ተቋም ትምህርት በክረምት መሰጠቱ ስራ እና ትምህርቱን ጎን ለጎን አድርጎ ለማካሄድ እንደረዳው ይናገራል። ወጪውን በግሉ ሸፍኖ እንደሱ ትምህርቱን ለአምስት ዓመታት በወሎ ዮንቨርስቲ የተከታተለው ሰይድ በመማሩ በርግጥ ትርፋማ ይሁን አይሁን የሚያውቀው በተማርኩት ትምህርት ስራም ሳገኝ ነው ይላል።

Äthiopien Universität Adis Ababa
ምስል picture alliance/chromorange/G. Fischer

እንደ ሰይድ በግላቸው ከሚማሩ መምህራን ይልቅ ለምን መንግሥት የመደባቸው መምህራን በቅድሚያ ስራ እንደሚያገኙ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴታዋ ወይዘሮ ፂዎን ሲያብራሩ « መምህሩ ያለበት ቦታ፣ የትምህርት ቤቱ ፍላጎት፣ የስራ ክፍት ቦታ» ወሳኝ  ናቸው ይላሉ። በሀገር አቀፍ ደረጃስ? ለመምህራን እና ለተማሪዎች የክረምት ትምህርት መሠጠቱ ምን ያህል ጠቅሟል? « ጥሩ ውጤት አስመዝግቧል ግን ከዚህ የበለጠ ማሻሻልም ይጠበቅብናል ይላሉ ወይዘሮ ፂዎን።

በተለይ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከወላጆች በኩል ልጆቻቸው ላይ የሚደረገው የትምህርት ጫና ተጠናክሯል። ልጆች ትምህርት በተዘጋበትም ወቅት እንዲያጠኑ እና ለሚቀጥለው  የትምህርት ዘመን እንዲዘጋጁ ይገፋፋሉ። የዕረፍት ጊዜ ተብሎ በሚዘጋው የትምህርት ወቅት ተማሪዎችም ይሁኑ መምህራን ያለማቋረጥ ጊዜያቸውን በትምህርት እና በጥናት ማሳለፋቸው ምን ያህል ይመከራል? ወይዘሮ ፂዎን ተማሪዎች ጨርሶ አያርፉም ማለት አይደለም ይላሉ።« ትምህርቱ የሚሰጡት በተወሰኑ ትምህርቶች ላይ ነው። ሌላው ደግሞ አስፈላጊነቱ ሲታወቅ የሚሰጥ ነው። እንደ መደበኛው ትምህርት ቀኑን ሙሉ የሚሰጥም አይደለም። » ይላሉ።

የክረምት ተማሪዎችን ተሞክሮ እና የክረምት ትምህርት አሰጣጥን  የቃኘው ዝግጅትን በድምፅ መከታተል ይችላሉ።

ልደት አበበ