1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የክሪምያ ቀዉስና የዓለም ኤኮኖሚ

ረቡዕ፣ መጋቢት 10 2006

የዩክሬይን ግዛት የሆነችው ክሪምያ ባለፈው እሁድ ከሩስያ ፌዴሬሽን ጋ ዳግም ለመዋሃድ የሚያስችላትን አወዛጋቢውን ህዝበ ውሳኔ ካካሄደች በኋላ የአዉሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት በሩስያ ላይ የመጀመርያዉን ማዕቀብ ጥለዋል። በተጣለዉ ማዕቀብ መሠረት፣ 21 ሩሲያውያን እና የክሪሚያ ባለሥልጣናት በምዕራቡ ዓለም፤

https://p.dw.com/p/1BSVz
Frankfurter Börse DAX
ምስል Reuters

ያላቸዉ የባንክ ሂሳብ እንዳይንቀሳቀስ እና ወደ አዉሮጳም እንዳይገቡ ተከልክለዋል። እንዲም ሆኖ ሁሉም የኅብረቱ አባል ሃገራት ይህንን ማዕቀብ ተግባራዊ ማድረጋቸው እያጠያየቀ ነዉ። በሌላ በኩል ከሩስያ ጋር የኤኮኖሚ ትስስር ያላቸው ጀርመንን የመሳሰሉ ሃገራት ይህ ማዕቀብ ሌላ ችግር እንዳያስከትልባቸው መስጋታቸው አልቀረም። የዕለቱ ዝግጅታችን በክሪምያ ቀዉስ ምክንያት ፤ በስጋት ላይ ስለ ወደቀዉ የጀርመን ሩስያ ኤኮኖሚ ግንኙነት ላይ ዘገባ ይዞአል። የክሪምያ ግዛት ህዝብ ከዩክሪይን ለመገንጠል ባለፈዉ እሁድ በህዝበ ዉሳኔ ካረጋገጠ በኋላ፤ የክሪሚያ ምክር ቤት በግዛቱ የሩስያ መገበያያ «ሩብል» እስከ ጎርጎረሳዊዉ ጥር 1/ 2016 ዓ,ም ድረስ ከዩክሪኑ የመገበያያ ገንዘብ «ሃርቪና» ቀጥሎ እንደ ሁለተኛ የመገበያያ ገንዘብ እንደሚያገለግል ትናንት ይፋ አድርጓል። የሩስያ ማዕከላዊ ባንክ በበኩሉ በክሪምያ የመገበያያዉ ገንዘብ ሩብል በሰፊዉ እንዲገባ ድጋፍ እንደሚሰጥ ያስታወቀበት ውሳኔው እስካሁን በዓለም ገበያ ላይ ይህ ነው የሚባል ለዉጥ አላመጣም፣ በዩሮ ምንዛሪ እና በነዳጅ ዋጋ ላይ አነስተኛ ጭማሪ ብቻ ነዉ የታየበት፤ እንድያም ሆኖ የክሪምያ ቀዉስ በዓለም ኤኮኖሚ ላይ ትልቅ ለዉጥ ሊያስከትል ይችላል የሚለዉን ስጋት አጉልቶታል።
የአክስየን ገበያተኞች እንደሚሉት፣ የክሪሚያ ህዝበ ውሳኔ እና መዘዙ በፊናንሱ ገበያ ላይ ተፅዕኖ ማሳረፉ አይቀርም። በዚህ አኳያ በተለይ ጀርመን እና ኦስትርያ ተጠቃሽ ናቸዉ። ሁለቱ ሃገሮች ከሩስያ ጋር ባላቸዉ የጠበቀ የኤኮኖሚ ትስስር ምስራቅ አዉሮጳን ከአዉሮጳዉ ህብረት ሃገራት ጋር የሚያገኛኑ ድልድይ ሃገሮች በመሆናቸዉ ነዉ የሚታወቁት።
ፖለቲከኞች የአዉሮጳዉ ኅብረት የዩክሬይን ግዛት ክሪምያን ይዛለች በሚሉዋት ሩስያ ላይ ጠንካራ ማዕቀብ በመጣል ድርጊቱ ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ መሆኑን ማሳየት አለበት ባሉበት ወቅት፤ የኤኮኖሚ ጉዳይ ባለሞያዎች፤ ትልቅ ቀዉስ ላይ የማይጥልና፤ ሌላ አለመግባባት ላይ የማያደርስ ማዕቀብ ይጣል ሲሉ የመፍትሄ ሃሳብ ሰጥተዋል። በጀርመን የንግድ ባንክ የኤኮኖሚ ጉዳይ ዋና ተጠሪ ዮርግ ክሬመርግ እንደሚሉት በሩስያ ላይ የሚጣለዉ ቅጣት ሃገራቱን ለበለጠ ቀዉስ መዳረግ እንደሌለበት እና ምዕራባዉያት ሃገራት በኤኮኖሚዉ ጉዳይ ከሩስያ ጋር ቅራኔ ዉስጥ የሚያስገባ ምንም አይነት ፍላጎት እንደሌላቸዉ ተናግረዋል። በጀርመን ኢንዱስትሪ እና የንግድ የዉጭ ኤኮኖሚ ጉዳይ ምሁር ፎልከር ትራየር በበኩላቸዉ የክሪምያ ቀዉስ በኤኮኖሚዉ ላይ በቂ ጥፋት አስከትሎአል ባይ ናቸዉ ።
«የጀርመን እና ሩስያ የንግድ ግንኙነት አሁንም ተጎድቶአል። የትልልቅ ማዕለ ንዋይዎች ሥራ ተደናቅፎአል። ከሩስያ በቧንቧ የሚተላለፍ ጋዝ ስምምነትም ገቢራዊ መሆን አይችልም። በሌላ ሩስያ ዉስጥ ያለዉ የጀርመን ምጣኔ ኃብት ከፍተኛ ነዉ። በሩስያ ዉስጥ ከ20 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወርተናል»
እንደ ትራይር በክሪምያዉ ቀዉስ የጀርመን እና የሩስያ የኤኮኖሚ ትስስር ጉዳት ላይ ወድቋል። እንድያም ሆኖ በሩስያ የሚገኙ የጀርመን የንግድ ተቋማት አደጋ ላይ የወደቁ አይመስልም። ለምሳሌ « ቢ ኤ ኤስ ኤፍ » በሚል አፅህሮቱ የሚታወቀው ግዙፉ የኬሚካል አምራች ድርጅት ቅርንጫፍ፤ ቪንተር ሼል ፤ በከፊል ከግዙፉ የሩስያዉ ጋዝ አምራች ጋዝ ፕሮም ጋር ልዉዉጥን ይፈልጋል። የቪንተር ሼል ዋና ተጠሪ ራይነር ዜለ እንደሚሉት ስምምነቱ ተደርሶአል፤ አሁን የቀረዉ ተግባራዊ የሆነዉ የልዉዉጡ ሥራ ሂደት ብቻ ነዉ። በዚህም ቪንተር ሼል የተሰኘዉ የግዙፉ ኬሚካል አምራች ቅርንጫፍ ራሱን ከጀርመን የጋዝ ሻጭ እና አከፋፋይ ነጋዴዎች መለየት ይፈልጋል። የጀርመን የጋዝ ማከፋፈያ በሩስያዉያን እጅ መሆኑ ጥሩ ላይሆን ይችላል። በሌላ በኩል ጥቅምም አለዉ ሲሉ፤ በጀርመን የኢንዱስትሪ እና የንግድ የዉጭ ኤኮኖሚ ጉዳይ ምሁር ፎልከር ትራየር ያስረዳሉ፤
«በሌላ በኩል በልዉዉጡ አንዱ አንዱ ላይ የሚኖረዉ ጥገኝነት ስለሚቀንስ ሁኔታዉ ጥሩ ነዉ ብያ አምናለሁ። ስለዚህም ሩስያዉያን ጀርመን ዉስጥ ቢነግዱ፤ በጀርመን ማህበረሰብ ኤኮኖሚ ላይ ትልቅ ዉድቀት ያደርሳሉ የሚል እምነት የለኝም። ምክንያቱም በሁኔታዉ መልስ ልንሰጥ እንደምንችል ያዉቃሉና»
የጀርመን ንግድ ባንክ ዋና ተጠሪ ዮርግ ክሪመር በበኩላቸዉ የክሪምያ ቀዉስ በጋዝ ንግዱ ላይ ተፅኖ ያሳድራል የሚል ምንም አይነት ስጋት እንደሌለ ይገልፃሉ። ክሪመር ሩስያ በተጣለባት ማዕቀብ ሳብያ ወደ ጀርመን ጋዝ የምታስተላልፍበትን ባንቧ ትዘጋለች የሚል እምነትም የላቸዉም። ምክንያቱም የሩስያ ኤኮኖሚ በብዛት በጋዝ ንግድዋ ላይ ጥገኛ በመሆኑ ነዉ። ክሪመር ሩስያ የጋዝ ማመላለሻ ቧንቧዉን ብትዘጋ ፤ ጋዝ መሸጥ የሚፈልጉ ሌሎች በመካከለኛዉ ምስራቅ አልያም ሰሜን አፍሪቃ የሚገኙ ሃገራት በመኖራቸዉ ይህን ያህል ስጋት ላይ የሚጥል ጉዳይ አይደለም ባይ ናቸዉ። በሌላ በኩል በጀርመን የክረምቱ ወራት እጅግ ቀዝቃዛ የሚባል ስላልነበረ፤ አሁንም በሀገሯ ያለዉ የጋዝ ክምምችት እጅግ እጅግ አጥጋቢ ነዉ ሲሉ ገልፀዋል።
እንድያም ሆኖ በርካታ ታዛቢዎች እንደሚሉት ሩስያ ላይ ከፍተኛ ማዕቀብ ቢጣል፤ የጋዝ ንግዷን በማቋረጥ ማስፈራርያ እና እንደመያዣ ታደርገዋለች ሲሉ ጥርጣሪያቸዉን ይገልጻሉ። « ኤ ኦ ን » የተሰኘዉ የጀርመን የኤሌትሪክ እና የ ጋዝ አቅራቢ ድርጅት ዋና ተጠሪ ዮሃንስ ቴሰን እንደሚሉት ከ 40 ዓመት ጀምሮ ሩስያ የጋዝ ንግዷን በተባለዉ መንገድ እና ሰዓት ያለምንም እክል ማቅረብዋ ይታወቃል። እስከ ዛሪ ይላሉ ዮሃንስ ቴሰን ሩስያ የምትሸጠዉን ጋዝ እንደ ስትራቴጅያዉ መሳርያ ስትጠቀምበት አላየሁም። እንድያም ሆኖ ይላሉ ክሪመር በመቀጠል፤ ተጠቅማበት ታዉቃለች፤ ነገርግን ይህን ያደረገችዉ ጫና ማሳደር በምትችለዉ ሃገራት ላይ ብቻ ነዉ፤ ለምሳሌ በዩክሪይን ላይ ። ለምዕራባዉያን ሃገራት ግን ሩስያ የምትሸጠዉን ጋዝ በትክክል አስተላልፋለች። ይህ ደግሞ ሊደንቅ የሚገባ ጉዳይ አይደለም ምክንያቱም የሩስያ ኤኮኖሚ በጋዝ ንግድዋ ላይ የተመሰረተ ነዉ። ሩስያ ለንግድ ወደ ዉጭ ሃገራት ከምትልካቸዉ ነገሮች መካከል የጋዝ ንግድዋ 70 በመቶዉን ያጠቃልላል። የሩስያ ኤኮኖሚ ከምዕራባዉያኑ ጋር ሲነፃፀር ደካማ በመሆኑ በጋዝ ኃይል አቅሟ ምዕራባዉያኑን ሃገራት ማስበርገግ እንደማትችልም ተመልክቶአል። የሩስያ እና የጀርመን የተሳሰረ የንግድ ግንኙነት ስላላቸዉ ደስታኛ መሆናቸዉን የሚገልፁት፤ በጀርመን የኢንዱስትሪ እና የንግድ የዉጭ ኤኮኖሚ ጉዳይ ምሁር ፎልከር ትራየር ፤ ,
«አንዳችን በአንዳችን ላይ ያለንንን ተፈራራቂ የሆነ የኤኮኖሚ ጥገኝነት በፀጋ ነዉ የምንቀበለዉ። ምክንያቱም ጥገኝነቱ በጨመረ ቁጥር ተቀምጠን ስምምነት ለመድረስ መከራከር እንደምያስፈልገን እናዉቃለንና፤ በዚህም ወደ ስምምነት የሚያደርሰንን በር ጨምረን አንዘጋዉም። ሁልግዜ መስማምያ የምናገኝበት መስመር አለን»
እንድያም ሆኖ ይላሉ በወቅታዊዉ የክሪሚያ ቀዉስ ምክንያት ከሩስያ ወደ ጀርመን የሚያልፈዉ የጋዝ ቧንቧ ለግዜዉ ተዘግቶአል። «የጋዝ ማከማቻዉ ሙሉ ስለሆነ፤ ለ 45 ቀናት የሃገሪቱን የኃይል ፍላጎት በዚሁ መሸፈን ይቻላል።ኖርዊይም ብትሆን ጋዝ ልትሸጥልን ትችላለች። በጨሃይና በነፋስ ኃይል ኤሌክትሪክ አመንጭቶ በከሰል እና በአቶም የሚመነጨዉን ኃይል ለመቀነስ የወጣዉን መረሃ-ግብር ግቡን ለማሳካት ግን ያለ ሩስያ ጋዝ ሊሞከር አይችልም» ባለፈዉ እሁድ የዩክራይን ግዛት ክሪምያ ልሳነ ምድር ከሩስያ መቀላቀል አለመቀላቀል ህዝበ ዉሳኔ በምትሰጥበት ዕለት «ኤርቨ» በመባል የሚታወቀዉ በጀርመን ታዋቂዉ የጋዝ እና ነዳጅ አቅራቢ ኩባንያ ቅርንጫፍ «ዴ አ » ለአንድ የሩስያ ባለኃብቶች ቡድን ከአምስት ቢሊዮን ይሮ በላይ በሚሆን ገንዘብ ሊሸጥ መዘጋጀቱን ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።
ከክሪሙ ቀዉስ ባሻገር ይህ የንግድ አካሄድ በፖለቲካዉ አኳያ በደንብ መመርመር ያለበት ጉዳይ መሆኑ ተመልክቶአል ። እንደ ግዜፉ የጋዝ እና የነዳጅ ዘይት አቅራቢ ኩባንያ « አር ኤ ቬ » ገለፃ ፤ የክሪም ቀዉስ በዚህም አለ በዝያ የሽያጩን ስምምነት የሚቀለብሰዉ አይሆንም። በሩስያ 6200 የጀርመን ድርጅቶች የሚገኙ ሲሆን እነዚህ ድርጅቶች በጠቅላላዉ የሃያ ሚሊዮን ይሮ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰሳቸዉ ተጠቅሶአል።

Eon Johannes Teyssen Vorstandsvorsitzender des Energiekonzerns Eon
ምስል picture-alliance/dpa
Hans-Werner Sinn
ምስል dapd

አዜብ ታደሰ
አርያም ተክሌ