1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የክርስቶስ የልደት በዓል አከባበር በጀርመን ፍራንክፈርት

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 29 2011

በመላው ኢትዮጵያውን  ዘንድ በአደባባይ በፍቅርና በአንድነት የሚከወን የአብሮነት ባህል የሚጎለበትበት እንዲሁም እንደ ገና ባሉ ባህላዊ ጨዋታዎች ታጅቦ የሚከበር አኩሪ ባህላዊ እሴታችን በመሆኑ ከሌሎች አውደ አመቶች ለየት ያለ ድባብ አለው፡፡

https://p.dw.com/p/3B9NS
Äthiopische Genna Market  Weihnachtsfeier in Frankfurt
ምስል DW/E. Fekade

ልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ የቅዳሴ የጸሎት እና የምሥጋና ሥርዓቶች ተከናውነዋል

በዓሉ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በጾም በሱባኤ በልዩ ልዩ ሐይማኖታዊት ሥነስርዓቶች እና በየአብያተክርስቲያኑ ለፈጣሪ አምላክ በሚቀርብ ምስጋና የጸሎት የወረብ ዝማሬ እና ሽብሸባ ሥርዓተ-አምልኮ የሚከናወንበት ክብረበዓልም ነው የእየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ገና ፡፡ የዘንድሮው የገና በዓል በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማና አካባቢዋ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ትላንት ከዋዜማው ጀምሮ በተለያዩ የክርስትና አማንያን ዘንድ በኃይማኖታዊ ሥርዓተ አምልኮ በጸሎት በዝማሬ እና በምስጋና እንዲሁም ደማቅ ባለ ባህላዊ ሥርዓት እየተከበረ ይገኛል:: በትላንትናው ዕለት ምሽት እስከ ንጋት ድረስ የገና ጾም ማብቂያ እና የእየሱስ ክርስቶስን የልደት ብስራት አስመልክቶ በየአብያተክርስትያናቱ ልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ የቅዳሴ የጸሎት እና የምሥጋና ሥርዓቶች ተከናውነዋል::

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የጀርመን እና አካባቢዋ አድባራት ዋና አስተዳዳሪ እንዲሁም የምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ቤተክርስትያን ዋና አስተዳዳሪ መልአከ መዊ ቀሲስ ልሳነ ወርቅ ከ 27 ዓመታት በላይ በአገር ውስጥ እና በውጭ ተከፋፍሎ የቆየው ሲኖዶስ የተዋሃደበት እና አማንያኑም አንድነታቸው መልሶ የተጠናከረበት ወቅት መሆኑ የዘንድሮውን በዓል ልዩ ድምቀት እንደሰጠው ገልጸውልናል :: የገና በዓል የሰላም እና ፍቅር ተምሳሌት መሆኑን በማስታውስም በአገራችን አሁን ላይ ጎልቶ የሚስተዋልው ዜጎችን ማፈናቀል የብሄር ግጭት እና የደቦ ጥቃት አብቅቶ ፍቅር እና ሰላም ማስፈን የሁሉም ዜጋ ሃይማኖታዊ እና የሞራል ግዴታ ነው ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል:: የእየሱስ ክርስቶስ መወለድ ምስጢሩ ፍቅርን ለማስተማር እና የሰው ልጅ በሃጢአቱ ምክንያት ከፈጣሪ እግዚአብሄር ጋር ተፈጥሮት የነበረውን መራራቅ በይቅርታ እና ምህረት ለማስታረቅ የተገባ አምላካዊ ቃል ኪዳን በመሆኑ የክርስትና ዕምነት ተከታይ ምዕመናንም ሆኑ መላው ሕዝባችን ከጥላቻ እና ጸብ እንዲርቅ መክረዋል:: የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያንም የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አስተዳደር የጀመረውን የፍቅር እና የአንድነት መርህ በመደገፍ በየአጥቢያው በእርቅ እና ሰላም ዙሪያ ጠንክራ እንደምትሰራ ነው መልአከ መዊ ቀሲስ ልሳነ ወርቅ  ያብራሩት::

በኢትዮጵያ ላለፉት 3 ዓመታት በተለይም ለአካል ጉዳተኞች እና ለሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች በግልም በቡድንም የበኩሉን ድጋፍ ሲደርግ የቆየው በጀርመን ፍራንክፈርት የኢትዮጵያውያን ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን ማህበርም ጊንሃይም በሚገኘው የቅዱስ ፋሚሊያ ቤተክርስትያን የገና በዓል መስዋዕተ ቅዳሴ አከናውኗል:: የማህበሩ ዋና አስተባባሪ አቶ አንቀጻዊ ምስጋኑ እየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት ወቅት የተፈጠረውን ክስተት ከአገራችን የለውጥ ሂደት ጋር ለማነጻጸር ሞክረዋል::

በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 2:16 እንደተገለጸው በእግዚአብሄር እና በሰው ልጆች መካከል ለዘመናት የነበረውን የጥል መጋረጃ ቀዶ ኃጢአታችንን በደሙ በመዋጀት በምድር ሰላምን ሊያነግስ የዓለም አዳኝ በቤተልሄም ከተማ ይወለዳል የሚለው የትንቢት ቃል መፈጸሙ እውን ሲሆን የሰላም ትርጉሙ ያልገባው ንጉስ ሄሮዶቱስ መንፈሱ በከፍተኛ መናወጥ ውስጥ እንደወደቀ አቶ አንቀጻዊ ያብራራሉ:: እናም ቤተልሄም ከተማን ጨምሮ በመላው የእስራኤል ምድር ሁለት ዓመት እና ከዛ በታች ዕድሜ የነበራቸው ወንድ ህጻናትን ያለ ምህረት ያስገደለበት አሳዛኝ የታሪክ አጋጣሚ አሁን በአገራችን የመጣውን የሰላም ለውጥ ተከትሎ የንጹሃንን ሕይወት በግፍ ከሚገድሉ እና ከሚያፈናቅሉ ሰዎች አሳዛኝ ክስተት ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው በመጥቀስ አጥፊዎች ወደ ሕሊናቸው እንዲመለሱም ምክራቸውን አስተላልፈዋል::

በፍራንክፈርት የኢትዮጵያውያን ካቶሊካዊት ቤተክርስትያን ማህበር አባላት የዘንድሮውን የገና በአል በጾም እና በልዩ ሱባኤ ያከበሩበትን ምክንያት ለአገራችን ሰላም ፍቅር እና አንድነት በመመኘት እንደሆነም ገልጸውልናል:: የክርስቶስ የልደት በዓል ገናን ጨምሮ ልዩ ልዩ አውደ ዓመቶችን በጋራ ተሰባስበው ልክ እንደ አንድ ቤተሰብ እንደሚያከብሩ ያወጉንም ነበሩ :: በአገራችን እየተካሄደ ያለው የለውጥ ጅማሮ  አስደስቶናል የሚሉት ምዕመናኑ በስደት ከማናውቃቸው ሰዎች ጋር ተከባብረን እየኖርን ለዘመናት ተዋልደን የጋራ አገር ከመሰረትን ወገኖቻችን ጋር አንዳንዶች መቻቻል አቅቶን ግጭት ውስጥ የምንገባበት ምስጢሩ እንቆቅልሽ ሆኖ ዛሬም ድረስ እንዳልተፈታላት ወጣት ኤልሳቤጥ ክፍለማርያም ነግራናለች::

በጀርመን ነዋሪ የሆኑ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስትያን ምዕመናን የገናን በዓል እንደወትሮው ሁሉ በጎርጎሮሳውያኑ የዘመን አቆጣጠር ከ 2 ሳምንት በፊት በልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓት አክብረዋል:: ያም ቢሆን በፍራንክፈርት የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስትያን ዋና ሰብሳቢ እና ፓስተር ዶክተር እሸቱ ግሩም ኢየሱስ የሰላም አምላክ መሆኑን በማስታወስ የልደት በዓሉን ምስጢር ስናከብር ሕዝበ ክርስትያን እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከብሄር ግጭት ከጥላቻ እና ከሁከት እርቆ እንደቀድሞው በሰላም በፍቅር እና በአንድነት ይኖር ዘንድ መንፈሳዊ ምክራቸውን አስተላልፈዋል::  መልካም በዓል !

እንዳልካቸዉ ፈቃደ

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ