1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮለኙ የፊልም ፊስቲቫልና ኢትዮጵያዉያኑ

ሐሙስ፣ መስከረም 12 2009

ዘንድሮ ለ 14ኛ ጊዜ በምዕራብ ጀርመንዋ በኮለኝ ከተማ በመካሄድ ላይ ያለው የአፍሪቃ ፊልም ፊስቲቫል የሁለት ኢትዮጵያዉያን የፊልም ስራዎችን ጨምሮ በአፍሪቃና ከአፍሪቃ ዉጭ የሚኖሩ አፍሪቃዉያን ፊልሞች የቀረቡበት እና የፊልም ባለሞያዎቹ ክህሎት የታየበት መድረክ ነው ።

https://p.dw.com/p/1K6jb
Videostill AFRIPEDIA
ምስል Teddy Goitom

በኮለኙ የፊልም ፊስቲቫል «አፍሪፒዲያ» በሚል የቀረበዉ ዘጋቢ ፊልም ላይ ጋናዊትዋ ወጣት ሙዚቀኛ በግል ጥረትዋ ለሙዚቃዉ መድረክ እንዴት እንደበቃች ከሚያሳይ ፊልም ላይ የተቀነጨበ ሙዚቃን በዝግጅቱ መጀመርያ ላይ ይደመጣል።

14. Afrika Film Festival Teddy Goitom
በፊልሙ ላይ ታሪክዋ የቀረበዉ የሴኔጋልዋ የፋሽን ልብስ ቅድ ባለሞያምስል Teddy Goitom

የ43 ዓመቱ ቴዲ ጎይቶም ዜግነቱ ስዊድናዊ ሲሆን የተወለደዉ እየሩሳሌም ነዉ። ጎይቶም ከእናቱ ሃገር ከኤርትራ፤ ከአባቱ አገር ከኢትዮጵያ ተለይቶ በስዊድን መኖር ከጀመረ ደግሞ 32 ዓመት ሆኖታል። በኮለኝ በየዓመቱ በሚዘጋጀዉ የፊልም ፊስቲቫል ላይ፤ የባልደረባችን የማንተጋፍቶት ስለሺን «ግርታ» የተሰኘዉ ፊልምን ጨምሮ የቴዲ ጎይቶም «አፍሪፒዲያ» የተባለዉ አምስት ዘጋቢ ፊልሞችን የያዘዉ የፊልም ፕሮጀክት ዘንድሮ በፊስቲቫል ከቀረቡት ፊልሞች መካከል ይገኙበታል። አፍሪፒዲያ የሚል ርዕስ የተሰጠዉ አምስት ፊልሞችን የያዘዉ ማዕቀፍ የፊልም ሥራ አዋቂዉ ቴዲ ጎይቶም ከሁለት ባልደረቦቹ ጋር አፍሪቃ ዉስጥ የሰራቸዉ ፊልሞች ናቸዉ። ፊልሞቹ በደቡብ አፍሪቃ ፤ አንጎላ፤ ጋና ፤ ሴኔጋልና፤ ኬንያ የሚገኙ ወጣት ከያንያን፤ የልብስ ቅድ ፋሽን ሰራተኛ፤ የፎቶግራፍ ባለሞያ፤ እንዲሁም ልዩ ልዩ የፈጠራ ትዕርኢትን በጎዳና ላይ የሚያቀርቡ ወጣቶችን፤ ታሪክ እና ወደነዚህ ሥራዎች እንዴት እንደገቡ የሚተርኩ ናቸዉ። የአፍሪቃዉያን ወጣቶች ልዩ የፈጠራ ክህሎትን የሚተርከዉን ፊልም በኮለኝ ያቀረበዉ የፊልም ስራ አዋቂ ቴዲ ጎይቶም እንደሚለዉ የአፍሪቃን ገፅታ በፊልሜ መቀየር እፈልጋለሁ።

«ይህ የእኔና የሁለት ባልደረቦቼ ኃሳብ ነዉ ። «አፍሪፒዲያ» የተሰኘዉን የተለያየ ዘጋቢ ፊልምን ያካተተዉን ፕሮጀክት ለመስራት ሃሳቡ የመጣዉ፤ ለመታየት እድል ያልገጠመዉ ወይም ወይም ዓለም የማያዉቀዉን የአፍሪቃን ሌላ ወገንን፤ ታሪክን ለዓለም ለማሳየት ነዉ። ስዊድን ባድግም እኔን ሰዎች አሁንም ሲያገኙኝ በ1982 ዓ,ም በኢትዮጵያ ስለነበረዉ ረሃብና ድርቅ ብቻ የሚያሚያስቡና የሚያስታዉሱ አሉ። የሚታያቸዉ ከሲታ ህፃናትና ድርቅ ረሃብ ችግር ብቻ ነዉ። አሁንም ስለአፍሪቃ በበርካታ ሃገራት ዉስጥ ያለዉ እምነት አንድ ዓይነት ገጽታ ነዉ። በሌላ በኩል በቴሌቭዝን የሚታየዉ የስኬት ገፅታም ቢሆን አፍሪቃዉያኑ ምን ዓይነት ችግርና ፈተናን ተጋፍጠዉ ለዉጤት ላይ እንደደረሱ የሚያዉቅ የለም።»

በዚህም ይላል ጎይቶም በመቀጠል ፤ ከአህጉሪቱ ጋር ያለኝን ግንኙነት አላቋርጥም።

Videostill AFRIPEDIA
ቴዲ ጎይቶምምስል DW/A. Tadesse

«በዚህም ምክንያት እኔ አህጉሪትዋ ዉስጥ ባልኖርም ከአፍሪቃ ጋር ግንኙነቴን ማቋረጥ አልፈልግም፤ ፊልምን አስደግፊ ምን ልሰራ እችላለሁ ብዬ እራሴን ጠየኩ። ከዝያም ነዉ አፍሪቃ ዉስጥ የሚታየዉን ክህሎት፤ አስደናቂ ፈጠራ ከአፍሪቃ ጋር የሚያገናኘን ጥሩ መስመር ነዉ ስንል ከባልደረቦቼ ጋር በጋራ ሃሳብ ያመጣነዉ። በዚህም ነዉ «አፍሪፒዲያ« የተሰኘዉን ተከታታይ ዘጋቢ ፊልም ለመስራት የጀመርነዉ።»

ቴዲ ጎይቶም በአሁኑ ወቅት እዚህ ጀርመን በኮለኝ ፊልም ፊስቲቫል ላይ ተገኝቶ ስለፊልሙ ማብራርያ ሰጥቶአል ፤ ኢትዮጵያዊም ኤርትራዊም እንደሆን ተናግሮአል ።

«በርግጥ ያደኩትና የእድሜዬን አብዛኛዉን ጊዜ ያሳለፍኩት። ከእናቴና ከእንጀራ አባቴ ጋር ነዉ። በልጅነቴ ወደ ስዊድን የመጣሁት። እና በኢትዮጵያ የነበርኩበትን የልጅነት ጊዜዬን በርግጥ ብዙ አላስታዉስም። በስዊድን ስኖር 32 ዓመት ሆኖኛል። በርግጥ እዚህ ስኖር ኢትዮጵያንም ኤርትራንም እየሄድኩ ጎብኝቻለሁ ፤ ዘመድ ጥየቃም ሄጃለሁ። አሁን የምኖረዉ ስዊድን ይሁን እንጂ ገሚሱን ጊዜዬን የማሳልፈዉ ግን በኒዮርክ ነዉ። በዝያ በአንድ አዲስ ሙዚየም በተጀመረ «ኢንክ» በሚባል ፕሮጀክት ላይ ተሳታፊ ነኝ። »

የፊልም ስራ አዋቂዉ ቴዲ ጎይቶምን ስለአገርህ ስለኢትዮጵያ አልያም ስለኤርትራ ምንም ፊልምን ሳትሰራ ምነዉ ወደ ሌሎች አፍሪቃ ሃገራት መሄድህ ስል ጠይቀነዉ ነበር።

«አማርኛ መናገር ያልቻልኩበት ዋናዉ ምክንያት፤ ያደኩት ከእናቴ ጋር በመሆኑ ነዉ። እናቴ ደግሞ ኢርትራዊ ናት። ትግሪኛ መነጋገር እችላለሁ። እንዳለመታደል ሆኖ አባቴ በሕጻነት ዘመኔ አብሮኝ አልነበረም። ቢሆንም ግን አማርኛ ቋንቋን እወዳለሁ፤ አማርኛ ቋንቋ ይገባኛል፤ ለመናገርም እሞክራለሁ፤ ለመማርም ጉጉት አለኝ! ለዚህ ቃለ ምልልስ ግን በአማርኛ ለመመለስ ትንሽ ያሳፍረኛል። ምክንያቱም በአማርኛ ቋንቋ መግለጽ የምፈልገዉን ነገር እንደምፈልገዉ እናገርበታለሁ ብዬ ስለማላምን ነዉ። »

Deutschland 14. Afrika Film Festival Köln
በፊልሙ ላይ ታሪክዋ የቀረበዉ የጋና ሙዚቀና ዋያላምስል Teddy Goitom

ጎይቶም በኮለኝ ከተማ የፊልም ፊስቲቫሉ ከመጀመሩ ከአንድ ቀን በፊት የደረሰዉ አሁን ከሚኖርበትና በቀጣይ የፊልም ስራዉን በስፋት ከሚሰራበት ከኒዮርክ ከተማ ነዉ።

«ኢንክ» የተባለዉ ፕሮግራም፤ ሥራን ለማስጀመር የሚረዳ ዓይነት ፕሮግራም ነዉ። ይህ ፕሮግራም ለአንድ ዓመት እገዛን ይሰጣል፤ እኔ የአንድ ዓመት እገዛ ተሰጥቶኝ አሁን ለቀጣይ ሦስት ዓመታት ተራዝሞልኛል። በዚህ ፕሮግራም ላይ «አፍሪፒዲያ» የተባለዉን ፕሮግራሜን ለማጎልበትና «በድረ-ገፅ መድረክን ለማግኘት የሚራዳ ነዉ። ይህ ድረ-ገፅ የፊልም ሥራዎች የሚታዩበትና የተለያዩ ተቋማት፤ ድርጅቶች፤ ማኅበራት፤ በአፍሪቃ ሃገራትና በሌሎች ክፈለዓለማት የሚገኙ የተለያዩ ክህሎቶች ያሉዋቸዉ አፍሪቃዉያን ባለሞያዎችን በቀላሉ የሚያገኙበት መድረክ ይሆናል።ይህ በአሁኑ ወቅት እኔና ባልደረቦቼ በኒዮርክ እየሰራንበት ያለዉ ፕሮጀክት «አፍሪፒዲያ» ከሚለዉ ሥራችን የቀጠለ ነዉ። በሽዎችና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ክህሎት ያላቸዉ አፍሪቃዉያን የኪነ-ጥበብ ሰዎች ሥራቸዉን መዝግበን የምናስቀምጥበት ከያንያኑ የሚገናኙበትና ራሳቸዉን የሚያስተዋዉቁበት መድረክም ይሆናል።

የፊልም ስራ አዋቂዉ ቴዲን ምነዉ አምስት አፍሪቃ ሃገራት ላይ ፊልም ስትሠራ ኢትዮጵያን አልያም ኤርትራን መርሳትህ ብለነዉ ነበር።

በርግጥ ይህን ፕሮጀክት በጎርጎረሳዉያኑ 2009 ዓ,ም መጀመር ያሰብነዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ነበር። ለምሳሌ በዝያን ወቅት አዲስ አበባ እያለን ታዋቂዋን የፎቶግራፍ ባለሞያ አይዳ ሙሉነህ የፎቶግራፍ ትምህርት ቤት ስትጀምር አግኝተናት ነበር። ሌሎች በርካታ ሰዓልያንና ከያኒዎችንም አግኝተን ነበር። ግን በዝያን ጊዜ ስለስራችን ብዙ ጥናትና ዝግጅትን አላደረግን ነበር። ከከያኒያኑና ከሰአሊያኑ አልያም ከፎቶ ባለሞያዎቹ ጋር ተገናኝተን ሃሳብ ተቀያየርን እንጂ ምንም ዓይነት ፊልም ቀረጻን አላካሄድንም ነበር። ኢትዮጵያ ሄደን ዘጋቢ ፊልም ለመስራት እቅድ አለን። በርግጥ ከአንድ ሙዚቃ ባንድን በተመለከተ እንዲሁም ላሊበላ ሄደን ዘጋቢ ፊልሞችን ቀርፀናል፤ በአዲስ አበባ ካለዉ ጎተ ተቋም ጋርም ቀረፃ አካሂደናል፤ ኢትዮጵያዊ እንደመሆኖኔ መጠንም ስለኢትዮጵያ አንድ ፊልም መስራት እንዳለብኝ ይሰማኛል ፤ ስለዚህ በቅርቡ ኢትዮጵያ ላይ የተቀረፀ አንድ ፊልምን እናያለን»

Videostill AFRIPEDIA
ማንተጋፍቶት ስለሺምስል DW/M. Sileshi

የባልደረባችን የማንተጋፍቶት ስለሺ ፊልም የፊታችን ሰኞ ከ 1500 በላይ ሰራተኞች በሚገኙበት በቦኑ የዶቼቬለ ራድዮ ጣብያ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ይታያል። በኮለኙ የፊልም ፊስቲቫል ላይ አፍሪቃዉያኑ የፊልም ዳይሬክተሮች ፊልሞቻቸዉን ለማቅረብ እንዴት ይሆን የሚመረጡት ፤ የዛሬ 24 ዓመት ይህን ፊስትቫል ማዘጋጀት የጀመሩት አስተናባሪው ጀርመናዊዉ ካርል ሮስል በፊስቲቫሉ ላይ የምናሳየዉን ፊልም ይላሉ፤

«የምናሳያቸዉን ፊልሞች የምናገኘዉና የምንመርጠዉ በተለያዩ መንገዶች ነዉ። የፊልም ባለሞያዎች የሰርዋቸዉን ፊልሞች በሴዴ ይልኩልናል። በአፍሪቃ የሚገኙ የፊልም ባለሞያዎች የሰርዋቸዉን ፊልሞች በፖስታ ይሉኩልናል አልያም ፤ ፊልሙ የሚገኝበትን የድረገፅ አድራሻ ይልኩልንና እንመርጣለን። ለምሳሌ ባለፈዉ ዓመት ከሱዳን ፤ከኬንያ፤ ከሞሮኮ በርካታ ፊልሞች ይደርሱናል። ከአፍሪቃዉያን የፊልም ሥራና ሰራተኞች ጋር ስንሰራ 24 ዓመት ስለሆነን በርካቶቹን አፍሪቃዉያን የፊልም ሰራተኞች እናቃቸዋለን፤ አዲስ ፊልም ሲያወጡ ቶሎ እናዉቃለን።»

ካርል ሮስል እንደሚሉት አፍሪፒዲያ የተሰኘዉ ዘጋቢ ፊልም ለምሳሌ

«አፍሪፔዲያ» የተሰኘዉን የተሰኘዉን አምስት ዘጋቢ ፊልሞች መርጠን በጀርመንና ተርጉመን ለተመልካች አቅርበናል። ይህ ፊልም በጦርነት ረሃብ ችግር የምትጠራዉን አፍሪቃን ሳይሆን የአፍሪቃ ሌላ ገጽታን ነዉ የሚያሳየዉ። በፊልሙ በአፍሪቃ ነዋሪ የሆኑ ከፍተኛ ክህሎት ያላቸዉ ሰዎች የተለያዩ አስደናቂ ነገሮችን ሲሰሩ ሲፈጥሩ ይታል። እነዚህ ወጣቶች እድላቸዉን ሌላ ቦታ ለመፈለግ ያልተነሱ በዝያዉ በሚኖሩበት ሃገር ከፍተኛ ተከታዮች ያልዋቸዉ የራሳቸዉን የሙዚቃ ፤ የልብስ ቅድ ፋሽን፤ የአሳሳል ፤ የፎቶግራፍ አነሳስ ክህሎትን ያገኙና ያሳዩ ናቸዉ።» በአፍሪቃዉያኑ የተሰራዉ ፊልም ከታየ በኋላ ተመልካቾች የተለያዩ ጥያቄዎችን ያቀርባሉአስተያየቶችንም ይሰጣሉ፤ ከተመልካቾች አንዲት አስተያየት ሰጪ ፤ እንዲህ ነበር ያሉት፤

14. Afrika Film Festival Köln Teddy Goitom
ቴዲ ጎይቶምምስል DW/A. Tadesse

«በጀርመንም ሆነ በስዊድን በስደተኛ ቀዉስ ላይ ባለንበት በአሁኑ ጊዜ የአፍሪቃ ገፅታ ስላሳያችሁን እጅጉን እንመሰግናለን ። ለአብዛኞች ጀርመናዉያን ስለ አፍሪቃዉያንን፤ ያላቸዉ አመለካከት ከዚህ የተለየ ነዉ። አፍሪቃ ማለት እጅግ ሰፊ አህጉር መሆኗ ይዘነጋል። ተጎጂና ድሃ አፍሪቃዉያንን አልያም ስደተኞች ጀልባ ላይ ተቀምጠዉ ችግር ላይ ሆነዉ ሳይሆን ተስፋ አብቦ የሚታይበት ገፅታና የአፍሪቃዉያን ክህሎትን ስላሳያችሁን እጅግ እናመሰግናለን። » ለዝግጅቱ የተባበሩንን የፊልም ሰራተኞች እያመሰገንን፤ ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን ።

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ