1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ቴክኒክአፍሪቃ

አሜል ስንታየሁ

ዓርብ፣ ነሐሴ 7 2013

የዛሬው የወጣቶች ዓለም እንግዳችን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር የ15 ዓመት ወጣት ነው።  የኮምፒውተር አፕሊኬሽንስ ወይም መተግበሪያዎችን ሰርቷል። እንዴት እና ምን አይነት? ጠይቀነዋል።

https://p.dw.com/p/3ytnc
Still Amiel Sintayehu App-Entwickler

አሜል ስንታየሁ 15 ዓመቱ ነው። ዘንድሮ የሰባተኛ ክፍል ትምህርቱን አጠናቆ ወደ ስምንተኛ ክፍል ተሸጋግሯል። በዕረፍት ጊዜው  የኮምፒውተር መተግበሪያዎችን መጠቀም ብቻ ሳይሆን እንዴት እንደሚሠሩ መመራመር እና መረዳት ያስደስተዋል። ከዚህም አልፎ የራሱ የሆኑ አፕሊኬሽንስ ወይም መተግበሪያዎችን መሥራት ጀምሯል። « አይነስውራንም ይሁኑ ማንኛውም በድምፅ መጠቀም የሚፈልጉ ሰዎች ሊገለገሉበት የሚችሉበት አይነት አፕሊኬሽን ነው» መተግበርያው ለምሳሌ ቀንን፣ ሰዓትን  ለመሳሰሉ ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣል። ከዚህም ባሻገር በድምፅ የሚነገረውን ነገር ወደ ፁሁፍ ይቀይራል። ለጊዜው መተግበሪያው የሚሰራው በእንግሊዘኛ ቋንቋ ብቻ ነው። መተግበሪያው ወደፊት በአማርኛ የሚሠራበትን መንገድ አሜል እያመቻቸ እንደሆነ ገልፆልናል። ወጣቱ በዚህ መተግበሪያ አላበቃም። እስካሁን አራት መተግበሪያዎችን አጠናቆ አምስተኛውን እየሠራ ነው። እነዚህም የፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ እና ባዮሎጂ ትምህርቶችን የሚያቃልሉ ናቸው።


ትናንሽ የኮምፒውተር ጨዋታዎችን ወይም መተግበሪያዎችን መሥራት በተለይ በአደጉት ሀገራት የሚገኙ ልጆች እና ታዳጊ ወጣቶች ዘንድ እጅጉን እየተለመደ መጥቷል። ይህንንም ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ ኢንተርኔት ላይ በነፃ እና የሚከፈልባቸው የተለያዩ የመማሪያ መርሃ ግብሮች ይገኛሉ። ለሁሉም ግን ፍላጎት ወሳኝ ነው።  ለ“ሰው ሰራሽ አስተውሎት” (Artificial intelligence) ትልቅ ፍላጎት አለኝ» የሚለው አሜል ይህንን መተግበሪያ ለመስራት ሰዎችን ቢያማክርም መተግበሪያዎቹን የሰራው ግን ብቻውን እንደሆነ ነግሮናል።  እስካሁን የሰራቸውን መተግበሪያዎች ሰዎች በነፃ መጠቀም ይችላሉም ይላል። ይህንንም ማግኘት የሚችሉት https://amieldev.web.app/ የሚለው ገፁ ላይ ነው። አሜል ስራ ከሌለው ሙሉ ቀኑን የሚያጠፋው ኮምፒውተር ላይ ነው። 

ሰሞንኑን የወጣ አንድ የጀርመን ፖስትባንክ ጥናት እንደሚጠቁመው እድሜያቸው ከ16 እስከ 18 ያሉ  ወጣቶች በአማካይ በሳምንት 70 ሰዓት ያህል ጊዜያቸውን ኢንተርኔት ላይ ያሳልፋሉ። ይህ ቁጥር የኮሮና ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት በ2019 ዓም 58 ሰዓት ነበር።  ይህም ቁጥር ከፍ ያለው ከወረርሽኙ በኋላ ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው እና ተማሪዎች ትምህርታቸውን የሚከታተሉት በኢንተርኔት የርቀት ትምህርት ስለነበረ ነው። በዚህ መጠይቅ የተሳተፉት 1000 ወጣቶች በፍቃደኝነት እንደተናገሩት አብዛኛውን ጊዜያቸውን ማለትም በሳምንት 44 ሰዓት ገደማ የሚያሳልፉት ከእጅ ስልካቸው ጋር ነው። ኢትዮጵያዊው አሜልም ይሁን የክፍል ጓደኞቹ አብዛኛውን ጊዜያቸውን ስለ ኮምፒውተር እና ቴክኖሎጂ ማውራት ያስደስታቸዋል። « በዚህ ዘመን ቴክኖሎጂ የማይወድ ወጣት የለም የሚለው አሜል ወደፊት quantum computing መማር ይፈልጋል። 

Still Amiel Sintayehu App-Entwickler

ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች

የኮምፒውተር መተግበሪያዎችን የሚሠራው አሜል የ You Tube ቻናልም አለው። እዛ ላይ  ጥቂትም ቢሆኑ  በምስል የተቀነባበሩ እንደ የኅዋ መጓጓዣዎችን እና ክዋክብትን የመሣሠሉ አርእስትን የሚያብራሩ አጫጭር ቪዲዮዎችን ሰርቷል።  እሱም መተግበሪያዎቹን ለመስራት በብዛት You Tube ይጠቀማል። ወጣቱ ለቴክኖሎጂ ፍቅር እንዲያድርበት የገፋፋው ደግሞ የፊዚክስ ትምህርት ነው።
ብዙ ጊዜውን ኢንተርኔት ላይ የሚያሳልፈው አሜል የአሁኑ ትውልድ ኢትዮጵያ ውስጥም ያለ ኢንተርኔት እና ቴክኖሎጂ አገልግሎት የማይታሰብ እንደሆነ ይናገራል። ኢንተርኔር የሚጠቀሙ ወጣቶች ትርፍ ጊዜያቸውን በከንቱ እንዳያባክኑም አሜል የሚመክረው አለ። « እኔ የማስበው ለምሳሌ የገቢ ምንጭ ለማድረግ ልንጠቀምበት እንችላለን። ሌላው ደግሞ ሱስ ከሚያስይዙ አፕሊኬሽኖች መራቅ አለባቸው። ሶስተኛው ነገር ደግሞ ወጣቱ ፍላጎት የሚያድርበትን ነገር ፈልጎ ኦንላይን ላይ ገንዘብ እራሱ ሳንከፍል ትምህርት መማር ይችላሉ። ስራ ሁሉ ማግኘት ይችላሉ» ሲል የተለያዩ የኮምፒውተር መተግበሪያዎችን የሰራው የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት እንግዳችን አሜል ስንታየሁ ይመክራል። 

ልደት አበበ

ማንተጋፍቶት ስለሺ