1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮሪያ ልሳነ ምድር፤ ምላጭ ይሳብ ይሆን?

ሰኞ፣ መጋቢት 23 2005

የሶል-ዋሽግተኖች የዉጊያ ዛቻ-ቀረርቶ፣ ፉከራ-ማስጠንቀቂያዉ ግሟል።ኑክሌር የታጠቀ በሚሊዮን የሚቆጠር ጦሯቸዉ የዉጊያ ዝግጅት፣ ልምምድ ተጧጥፏል። ሚሳዬል፣ መድፍ ታንክ-ጠመንጃቸዉ ተቀባብሏል።ምላጭ ይሳብ ይሆን?

https://p.dw.com/p/187n8
A North Korean flag flies before missiles displayed during a military parade to mark 100 years since the birth of the country's founder Kim Il-Sung in Pyongyang on April 15, 2012. The commemorations came just two days after a satellite launch timed to mark the centenary fizzled out embarrassingly when the rocket apparently exploded within minutes of blastoff and plunged into the sea. AFP PHOTO / Ed Jones (Photo credit should read Ed Jones/AFP/Getty Images)
የሰሜን ኮሪያ ሚሳዬልምስል Ed Jones/AFP/Getty Images



በዚያ ምድር ጦርነትም ሠላምም የለም።ሥድሳ ዓመት አለፈዉ።ዛሬም በርግጥ ጥይት አልጮኸበም። ለሥድሳ ዘመን ከሌለዉ ሠላም እኩል ያልነበረዉ ጦርነት ግን ለዳግም ትንሳኤዉ ይደገስለት ይዟል።የኮሪያ ልሳነ ምድር።የፒዮንግዮንግ፣ የሶል-ዋሽግተኖች የዉጊያ ዛቻ-ቀረርቶ፣ ፉከራ-ማስጠንቀቂያዉ ግሟል።ኑክሌር የታጠቀ በሚሊዮን የሚቆጠር ጦሯቸዉ የዉጊያ ዝግጅት፣ ልምምድ ተጧጥፏል። ሚሳዬል፣ መድፍ ታንክ-ጠመንጃቸዉ ተቀባብሏል።ምላጭ ይሳብ ይሆን? ዳራ፣ ሰበብ ምክንያቱን እየጠቃቀስን ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

ድሮና-ዘንድሮ፥-

አንድ ናት።ኮሪያ። ሁለትም ናቸዉ ሰሜንና ደቡብ።ተደጋጋፊ ግን ጠላትም። ኮሚንስትና ካፒታሊስት። እነሱም አንድም፣ ሁለትም፣ ተደጋጋፊ-ተጠፋፊም ነበሩ።የሐገራቸዉ ዉልዶች።የሐገሮቻቸዉ አብነቶች።በዕድሜ የአያት እና ልጅ ያክል በአርባ-ሰባት ዓመት ይራራቃሉ።ሁለት፣ ሁለት ስም አላቸዉ።በ1875 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ሕዋንግሄ ግዛት ሲወለድ ወላጆቻቸዉ ያወጡለት ሥም ስይንግ-ማን ርሔ የሚል ነበር።


በወጣትነት ዘመኑ የጃፓን ቅኝ ገዢዎችን መቃወም ሲጀምር የሱና የብጤዎቹ ትግል፥ የትዉልድ ግዛቱን ቀርቶ ሐገሩን ለሁለት በገመሠ-ዉጤት ያሳርጋል፣እሁለት የመግመስ፣ የመጠላላት፥ መወጋጋቱን ሒደት እተዉናለሁ ብሎ አስቦ፣ ገምቶም፥ አልሞም አያዉቅም።በስሙ ላይ ግን ዪ ሴዩንግ-ማን የሚል ደረበበት።

ዘንድሮ የፕሬዝዳንትነቱን ሥልጣን የያዙት ወይዘሮ ፓርክ ጌኡን-ሕዬ ፥ ሲቀርብ እንደ ልጅ የአባታቸዉን፣ ሲጀመር የአባታቸዉ አለቃን የስይንግማንን ሥልጣን ከመያዛቸዉ እኩል መርሕ-አስተምሕሮታቸዉንም ይጋሩ ይሆናል።ዘመኑ ግን እሩቅ ነዉ።ካባታቸዉ ጋር-ሐምሳ፣ ከስይንጌማን ጋር ሥልሳ-ስምንት ዘመን ያራርቃቸዋል።

ፓርክ ዛሬ እንዳሉት ግን የዘመን ርቀት፣ የትዉልድ ለዉጥ፥ የፆታ ልዩነት፥ የሐብት ዕድገት፥ የዕዉቀት ብሥለት፥የቴክኖሎጂ ምጥቀትም የመጠፋፊያ መሳሪያ፥ ዘዴዉን አረቀቀዉ እንጂ የዚያን ምድር ዕዉነት አልቀየረዉም።

«የሠሜን ኮሪያን ድንገተኛ እና መብረቃዊ ጠብ አጫሪነት በተመለከተ፥ የጦር ሐይሎች ጠቅላይ አዛዥ እንደመሆነ መጠን ሰሜን ኮሪያን በቀጥታ የሚጋፈጠዉን ጦራችንን ዉሳኔና እርምጃ አምናለሁ።»

ሰሜንን የሚጋፈጠዉ ፓርክ የሚያዙት ጦር ብቻ አይደለም።ከሴይንግማን ጀምሮ ዘንድሮ ከወይዝሮ ፓርክ የደረሰዉን የሶል መንግሥትን የመሠረተዉ፥ ላለፉት ስልሳ-ሥምንት ዓመታት ያን መንግሥት በተጠንቀቅ የሚጠብቀዉ የአሜሪካ ጦር ጭምር እንጂ።

ድሮ፥-

በ1942 ተራራማ ቀበሌ የተወለደዉ ኪም ሶንግ ጁ ከትዉልድ መደሩ አጠገብ ከምትገኘዉ ትልቅ ጥንታዊ ከተማ መንግሥት አቆማለሁ፣ የአንዲት ሐገሩን ሁለትነት፣ ጠላትነት፥ የሕዝቧን መጠፋፋት እዘዉራለሁ ብሎ ማሰብ ቀርቶ ማለምም አይችልም ነበር።


ሲጎረምስ፣ የታላቁን የሴይንግማንን አላማ-አለማዉ አድርጎ ትልቅዬዉ ያጋመሰዉን ትግል ተቀየጠ።ያኔ ግባቸዉ አንድ ነዉ።ሐገር ሕዝባቸዉን ከጃፓን ቅኝ አገዛዝ ነፃ ማዉጣት።የትግል ሥልት፥ ፍልስፍና ዘዬያቸዉ ግን ሁለት ሆነ።ትልቅዬዉ የአደባባይ አመፅ፣ የፖለቲካዊ መድረክን-ቀዳሚ፣ የነፍጥ ትግልን ተከታይ ሲያደርግ፣ ትንሹ ተቃራኒዉን ግን የነማኦን ሥልት መርጦ ጃፓኖችን በነፍጥ ሊፋለም ጫካ ገባ።

አባቱም ተከተሉት።አሉትም፥- «እነሆ ከእንግዲሕ፥ ኪም ኢል ሱንግ ብዬሐለሁ።» የሚፀሐየዉ ወይም ፀሐይ የሚሆነዉ እንደማለት ነዉ-ፍቺዉ።ምን ታይቷቸዉ ይሆን? ብቻ ወጣቱም፥ አንጋፋዉም የነፃነት ታጋይ በጃፓን ቅኝ ገዢዎች መታሰር፣ መገረፍ፣ መሰቃየትን ከዘመን ደረጃዉ ልዩነት በስተቀር እኩል ቀምሰዉታል። ግፍ መከራዉን ሽሽት-በመሰደድም አንድ ናቸዉ።


የተሰደዱበት ጊዜ ግን ይለያያል።የተሰደዱበት ሥፍራ ደግሞ ይቃረናል።ትልቁ (ከእንግዲሕ አንቱ ናቸዉ) በሻይንጋይ አድርገዉ ዩናይትድ ስቴትስ ገቡ።ከብዙ ዓመታት በሕዋላ ትንሹ ሶቬት ሕብረት ።የነሱም፣ የሐገራቸዉም፣ የሕዝባቸዉም አንድነት በሁለትነት፣ ትብብር፣ መደጋገፋቸዉ በተቃርኖ፣ ወዳጅነታቸዉ በጠላትነት መለወጡም ያኔ ተጠነሰሰ።


1945 ገና የሰላሳ ሰወስት ዓመት ወጣት ነበር።ግን የሶቬት ሕብረት ጦር በጊዚያዊነትም ቢሆን የፒዮንዮንግ ቤተ-መንግሥትን አስረከባቸዉ።እና አንቱ ናቸዉ።«ትንቢት ይቀድሞ ለነገር ብሎ» ብሂል በኮሪያኛ ካለ፥ አበትዬዉ ሁለተኛ ሲሰይሟቸዉ የተነበዩት ያኔ ይገለጥ ገባ።ፀሐይ ተባሉ። ፀሐይም ሆኑ።ለሚወዷቸዉ ብርሐን፥ ሙቀት እየፈነጠቁ፥ የሚጠሏቸዉን ያቃጥሉ፣ ያነዱት ገቡ።

ዘንድሮ፥

ኪም ጆንግ ኡን እንደ ፒዮንግዮንግ ቤተ-መንግሥት ሁሉ የአባት አያታቸዉን ፍልስፍና፥ አስተሳሰብ የአመራር ሥልት መዉረሳቸዉ ምንም አያጠራጥርም።የዘመኑ ርቀት ግን እጅግ ነዉ።ለዚያ ምድር ፖለቲካ ግን ኪም ኢል ሱንግም፥ ኪም-ጆንግ ኢልም፥ ኪም ጆንግ ኡንም አንድም ሰወስትም ነበሩ።ናቸዉም። ፀሐይ፥ ብርሐን፥ ሙቀት ቃጠሎ።ባለፈዉ ቅዳሜ ደግሞ የኪም ጆንግ ኡን ቴሌቪዥን ጣቢያ የፀሐይዋን ጭላጭል ብርሐን ደፍቆ-ቃጠሎዋን አረዳ።

«ከዚሕ ጊዜ ጀምሮ የሰሜንና-እና የደቡብ ግንኙነት የጦርነት ጊዜ ግንኙነት ነዉ።በሁለቱ ወገኖች መካካል ያለዉ ጉዳይ በሙሉ የሚበይነዉ በጦርነት ጊዜ ሕግ ነዉ»

እንደገና ድሮ፥

ሁለቱም ሐገር-ሕዝባቸዉን መዉደዳቸዉ ከጃፓኖች ቅኝ አገዛዝ ነፃ ለመዉጣት ካደረጉት ትግል፥ ከከፈሉት መስዋዕትነት በላይ ሌላ ዋቢ መጥቀስ አሰልቺ ነዉ።ሶቬየቶች ከሩሲያ አምጥተዉ ፒዮንግዮንግ ቤተ-መንግሥት የዶሏቸዉ ኪም ኢል ሱንግም፥ አሜሪካኖች ካሜሪካ አጉዘዉ የሶል ቤተ-መንግሥትን ቁልፍ የሰጧቸዉ ስይንግማንም የሚወዱትን ሐገር ሕዝባቸዉን አንድ ለማድረግ የየአለቆቻቸዉን ፍቃድ ለማግኘት መለመን፥ መለማመጥ የጀመሩትም ሥልጣን በያዙ ማግሥት ነዉ።

የሁለቱም ልምና ተማፅኖ፥ የሁለቱም ሿሚ፥ አዛዝዦች ሥልት ከሰላማዊ መንገድ ይልቅ አንዱ ሌላዉን በሐይል ደፍልቆ በማስገበር ሁለት የሆነችዉን ሐገር አንድ አድርጎ ለመግዛት ያለመ መሆኑ እንጂ፥ ዉዴታዉ በጥላቻ የመመረዙ ዚቅ።እና የዚያ ምድር፥ የዚያ ሕዝብ፥ ምናልባትም የሰላም ወዳዱ ዓለም የሥልሳ-ዓመት ጭንቅ።

ባለፈዉ ሳምንትም እንዲሕ ተጀመረ። አሜሪካኖች ከደቡብ ወዳጆቻቸዉ ጋር የጦር ልምምድ ያደርጉ ገቡ።ሐሙስ ደግሞ ከ 1953 ወዲሕ ብዙም የማይታየዉ የአሜሪካ የኑክሌር ቦምብ ተሸካሚ አዉሮፕላን በኮሪያ ልሳነ-ምድር ሰማይ ላይ በረረ።ቢ-ሐምሳ ሁለት።ዘንድሮ ሰወስተኛዉን ኑክሌር ቦምብ መታጠቃቸዉን ያወጁት የፒዮንግዮንግ ገዢዎች የዋሽግተኖችኖችን መልዕክት ለመረዳት ሁለቴ ማሰብ አላስፈለጋቸዉም።

«ቢ-ሐምሳ ሁለት በደቡብ አየር ክልል መብረሩ ፉፁም ጠብ ጫሪነት ነዉ።ይሕ እርምጃ እጅግ አደገኛ፥ ጦርነት መቆስቆስም ነዉ።»

የፒዮንግ ቴሌቪዥን ጣቢያ ፎከረ።የዋሽግተኖች ዛቻ ከሶሎች ቀድሞ፥ የፒዮንግዮንጎችን ቀጠለ።መከላከያ ሚንስትር ቻንክ ሔግል

«ከደቡብ ኮሪያ እና በዚያ የዓለም ክፍል ካሉን ወዳጆቻችን ጋር ያለንን ቃል ኪዳን ለመጠበቅ በፅናት እንቆማለን።በደቡብ ኮሪያም ሆነ በሌሎቹ ላይ የሚሰነዘር ጥቃትን ያለምንም ማመንታት እንመክታል።ለሚፈጠረዉ ለማናቸዉም ነገር ዝግጁዎች ነን።መዘጋጀትም አለብን።»

ዋሽግተኖች የዛቻ-ፉከራ በሩን ከከፈቱላቸዉ በሕዋላ ከመከላከያ ሚንስቴር ቃል አቀባይ እስከ ፕሬዝዳት ፓርክ የሚገኙት የሶል ባለሥልጣናትም አሰለሱ።

«በደብ ኮሪያ እና በሕዝቧ ላይ አንዳች ትንኮሳ ቢፈፀም፥አፀፋዉ ፖለቲካዊ እድምታን ከግምት የማያስገባ-ፈጣን እና ከባድ ነዉ የሚሆነዉ።»

ሰሜንም ነጋሪቱ ይጎሰም፥ ፍከራ-ቀረርቶዉ ባደባባይ ይቀልጥ ያዘ።ፒዮንዮግ ዮንግ-ትናንት


ስይንግማን ርሔ የፒዮንግ ዮንግ ጠላቶቻቸዉን ደፍልቀዉ፥ ኪም ኢል ሱንግ ባንፃሩ የሶል ባላንጦቻቸዉን ጨፍልቀዉ አንዲቱን ኮሪያ ለመግዛት የነበራቸዉ ሐሳብ እንዲያፀድቁላቸዉ፥ የዋሽንግተን፥ እና የሞስኮ አዛዞቻቸዉን ድጋፍ፥ ፍቃድ ለመጋኘት በየፊናቸዉ እንደባተሉ 1949 ተጋመሠ።

ሐሪ ኤስ ትሩማን፥ የሶልን፥ ጆሴፍ ስታሊንም የፒዮንግዮንግን ተፃራሪ ሐሳብን እኩል ቢጋሩትም አንዳቸዉ የሌላቸዉን አቅም እስኪለኩ ወይም ሐሳባቸዉን ገቢር የሚደርጉበትን ሰበብ እስኪያገኙ ተደፋፍጦ መኖሩን ነበር የመረጡት።


ኪም ኢል ሱንግ ግን ከዚያ በላይ መታገሥ አልቻሉም።መጋቢት ሰባት 1949 ሞስኮ።ጓድ ጆሴፍ «መላዋን ሐገሪቱን በጦር ሐይል ነፃ ለማዉጣት ሁኔታዉ አስፈላጊ እና የሚቻልም ያደርገዋል።» አሉ-አሉ ኪም።

«ሐሳብሕ ጥሩ ነዉ ጓድ» ብለዉ ጀመሩ የታላቂቱ ሐገር ታላቅ አብዮታዊ መሪ ጆሴፍ ስታሊን፥ ወፍራም ሲጋራቸዉን እየማጉ። ሞስኮና ዋሽግተኖች ኮሪያን ይገዛ የነበረዉን የጃፓንን ጦር ለሁለት ቀጥቅጠዉ ባሰወጡ ማግሥት፥ ኮሪያን ለሁለት ሲገምሱ የተዋዋሉትን ስምምነት ሲጠቃቅሱ፥ የሰሜን ኮሪያን ወታደራዊ አቅም ደካማነት፥ የሕዝቡን የንቃተ ሕሊና ዝቅተኛነት በኮሚንስታዊዉ የግድምድሞሽ ቃላት ሲያስረዱ ቆዩና ጠላቶቻችን ነገር ፈልገዉን ቢሆን ኖሮ እያሉ ቀጠሉ «እርምጃችሁን ማንም ይገነዘበዉ፥ ማንም ይደገፈዉ ነበር።»

ኪም ኢል ሱንግ ስታሊንን ሲለማመጡ ቤጂንግን የተቆጣጠሩት ማኦ ዜዱንግ ከስታሊን ቀድመዉ ለኪም ደረሱላቸዉ።ሰሜን በደቡብ ላይ ዘመተ።ፕሬዝዳት ሐሪ ኤስ ትሩማን ሰሜኖችን የሚገፉት ቻይና እና ሞስኮዎች መሆናቸዉን አልተጠራጠሩም።ሐምሌ ሐያ-ሰባት 1950።«ዉጊያዉን አሁን ካልተቋቋም ነዉ የሚያደርጉትን መናገሩ አስፈላጊ አይደለም።»

ከኢትዮጵያ እስከ ቱርክ፥ ከብሪታንያ እስከ ካናዳ አሜሪካኖችን ተከትሎ ኮሪያ ልሳነ ምድር የገባዉ የበርካታ ሐገራት ጦር፥ ከሰሜን ኮሪያና ከቻይኖች ጦር ጋር ይተላለቅ ገባ።የማኦ፥ የስታሊን፥ የኪም፥ የትሩማን፥ የሴይንግማን እብሪት እስኪተነፍስ ከአምስት መቶ ሺሕ በላይ ወታደር አለቀ።ከሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ሰላማዊ ሰዉ ረገፈ።አሸናፊም፥ ተሸናፊም የለም።1953 ዉጊያዉ ቆመ።ጦርነቱ ግን ቀጠለ።ዛሬ በሥልሳ ዓመቱ እንደገና እየተግፈጠፈጠ ነዉ።

ስታሊንም የስታሊኗ ሶቬየት ሕብረትም የለችም።የስታሊንን ቤተ-መንግሥት የያዙት ፕሬዝዳት ቭላድሚር ፑቱን የዋሽግተን-ሶል፥ የፒዮንግዮንግ ፖለቲከኞች የዉጊያ ዛቻ ፉከራቸዉን እንዲቆሙ መጠየቅ፥ ማሳሳበቻዉ ግን አልቀረም።

ሺ ፒንግ የማኦን ወንበር ገና በቅጡ አልተለማመዱትም።ቢለማመድቱንም ዳን ሺዎፑንግን እንጂ ማኦን ይሆናሉ ተብሎ አይጠበቅም።አካባቢያቸዉ ሲተረማማሰ እጃቸዉን አጣጥፈዉ ይቀመጣሉ ማለት ግን ከጅል ያስቆጥራል።ኦባማ ሩዘቬልት ወይም ትሩማን አይደሉም።ልክ እንደትሩማን ደቡብ ኮሪያ በሰፈረዉ የአሜሪካ ጦር ላይ ተጨማሪ ጦር፥ ቢ-ሐምሳ ሁለት እና ኤፍ ሃያ-ሁለት ተዋጊ አዉሮፕላኖችን ጨምሮ ዘመናይ ጦር መሳሪያ ወደ ኮሪያ ልሳነ-ምድር እያስጋዙ ነዉ።

ኪም ጆንግ ኡን የአያታቸዉን ሥልጣን የያዙት የአያታቸዉ መቶ ሺሕ ጦር ወደሚሊዮን ካደገ፥ በባሕር ሰርጓጅ ጀልባ፥በፈጣን ጄት፥ በአብራሪ አልባ አዉሮፕላን፥ የአሜሪካ ግዛትን ሳይቀር ሊመታ በሚችል የሩቅ ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳዬል፥ ከሁሉም በላይ በኑክሌየር ቦምብ ከተጠናከረ በሕዋላ ነዉ።አስተዋይ፥ አርቆ አሳቢ አመራር ካልገታዉ፥ አደጋዉ ካለፈዉ፥ ከሚነገር ከሚተረከዉም የከፋ ነዉ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

FILE - In this July 25, 2010 file photo, the Nimitz-class USS George Washington, bottom, and the South Korean navy's 14,000 ton-class large-deck landing ship Dokdo Ham, top, leave for the U.S.-South Korea joint military exercises at the Busan port in Busan, south of Seoul. On the heels of North Korea's attack on Yeonpyeong island that killed four people _ two of them civilians _ the Obama administration has sent the aircraft carrier to the Yellow Sea, between Korea and China, to take part in a previously planned joint exercise with South Korea starting Sunday, Nov. 28, 2010. (AP Photo/ Lee Jin-man, File)
የአሜሪካ አዉሮፕላን ተሸካሚምስል AP
A B-52 bomber armed with cruise missiles is shown in this undated file photo. The B-52 has never been used for its initial potential: dropping hydrogen bombs on a cold war enemy. But the Air Force has found other reasons to keep it around -- for conventional bombing, photographic reconnaissance, and launching missiles. (AP Photo/U.S. Air Force)
B-52ምስል AP
REFILE - ADDING POOL TO BYLINE South Korea's President Park Geun-Hye speaks in front of photographs of sailors who died, during an event marking the third anniversary of the sinking of a South Korean naval vessel by what Seoul insists was a North Korean submarine, at the national cemetery in Daejeon March 26, 2013. 46 sailors died when the Cheonan corvette sunk. REUTERS/Kim Jae-Hwan/Pool (SOUTH KOREA - Tags: POLITICS ANNIVERSARY MARITIME MILITARY)
ፓርክምስል Reuters
North Korean leader Kim Jong-un speaks during a mass parade to celebrate founder Kim Il-sung's 100th birthday in Pyongyang in this still image taken from video April 15, 2012. Kim Jong-un led celebrations on Sunday to mark the centenary of the birth of his grandfather, the founder of the world's only Stalinist monarchy, "Eternal President" Kim Il-sung. REUTERS/KRT via Reuters TV (NORTH KOREA - Tags: MILITARY POLITICS ANNIVERSARY) FOR EDITORIAL USE ONLY. NOT FOR SALE FOR MARKETING OR ADVERTISING CAMPAIGNS. THIS IMAGE HAS BEEN SUPPLIED BY A THIRD PARTY. IT IS DISTRIBUTED, EXACTLY AS RECEIVED BY REUTERS, AS A SERVICE TO CLIENTS. NORTH KOREA OUT. NO COMMERCIAL OR EDITORIAL SALES IN NORTH KOREA
ኪምምስል Reuters
U.S. Military Police guard North Korean soldiers, captured Sept. 4, 1950, at the Naktong river front line, in a provisional prisoners of war camp near Suwon. In the background U.S. tanks are moving forward. (AP Photo) ------ Enttaeuschte Nord-Koreanische Gefangene sitzen in einem von amerikanischen MP's bewachten provisorisch mit Stacheldraht errichteten Gefaengnis, nachdem sie am 4. September 1950 an der Front beim Fluss Naktong gefangengenommen wurden. Im Hintergrund sind vorrueckende US amerikanische Panzer zu sehen. (AP Photo)
ያለፈዉ ጦርነት ዉጤትምስል picture alliance/AP Images
North Korean soldiers march in front of flower waving civilians during a mass military parade in Pyongyang's Kim Il Sung Square to celebrate 100 years since the birth of the late North Korean founder Kim Il Sung on Sunday, April 15, 2012. North Korean leader Kim Jong Un delivered his first public televised speech Sunday, just two days after a failed rocket launch, portraying himself as a strong military chief unafraid of foreign powers during festivities meant to glorify his grandfather. (Foto:David Guttenfelder/AP/dapd)
የሰሜን ኮሪያ ጦርምስል AP
South Korean new officers chant slogans during the joint commission ceremony of 5,780 new officers of the army, navy, air force and marines at the Gyeryong military headquarters in Gyeryong on March 8, 2013, south of Seoul. An enraged North Korea responded to new UN sanctions with fresh threats of nuclear war on March 8, vowing to scrap peace pacts with South Korea as it upped the ante yet again after its recent atomic test. AFP PHOTO / KIM JAE-HWAN (Photo credit should read KIM JAE-HWAN/AFP/Getty Images)
የደቡብ ኮሪያ ጦርምስል KIM JAE-HWAN/AFP/Getty Images

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ