1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮሪያ ልሳነ-ምድር ቁርቁስ

ሰኞ፣ ኅዳር 20 2003

ባለፈዉ ሳምንት ሮብ የሰሜን ኮሪያ ጦር ዮንፕዮንግ የተሰኘችዉን የደቡብ ኮሪያ ደሴት በመድፍ ደብድቦ-ሁለት ወታደሮችንና ሁለት ሰላማዊ ሰዎች መግደሉ እንደተሰማ-የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ የትሩማንን ቃል-ምግባር በስልሳ ሁለተኛ አመቱ ግን በዘመኑ ቋንቋ-ለመድገም አላመነቱም።

https://p.dw.com/p/QL93
የሰሜን ኮሪያ የጦር መሪዎችና መሪያቸዉምስል AP

29 11 10


የዘመኑን ምርጥ-መሳሪያ ምናልባትም ኑክሌር ቦምብ-የታጠቀ ከአንድ-ሚሊዮን ተኩል የሚበልጥ ምርጥ ጦር ሰሜን-ደቡብ እንደተፋጠጠ፥ እንደ ተፏከረ፥አንደተታኮሰበት ነዉ።ጦርነት ግን የለም።የአለም ሐብታም-ትላልቅ ሐገራት መሪዎች፥ እንደመከሩ-እንደዘከሩበት ምርጥ ዲፕሎማቶቻቸዉ እንደተወያዩ ሠላም እንደሰበኩበት ነዉ።ሠላም ግን የለም።ሐምሳ-ሰባት ዘመኑ።የኮሪያ ልሳነ-ምድር።ሰሞኑንም-አዲስ ደም አስገብሮ-እንዳዲስ ሥለሰላም ያስጮሕ-ያሰልፍ ይዟል።የሰሞኑ ክስተት መነሻ፥ ያለፈዉ ማጣቃሻ፥ ምክንያቱ መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።

Versammlung von Marine-Soldaten in Südkorea
የደቡብ ኮሪያ ጦርምስል AP

ኮሪያን ከ1910 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ጀምሮ ቅኝ የምትገዛዉን የጃፓንን ጦር በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ማብቂያ-ሰሜንና ደቡብ አቃርጠዉ ቀጥቅጠዉ-ያባረሩት ሶቭየት ሕብረትና ዩናይትድ ስቴትስ-የሚሹትን ሁሉ በሚሹት መንገድ አከናዉነዉ አገባደዱ።1948ም ተጋመሰ።

ፒዮንግዮግ ላይ ኪም ኢል-ሱንግ የሚመሩት ኮሚንስታዊ መንግሥት ያቆሙት ጆሴፍ ስታሊን ቀዩን ጦር-በ1948 ከሰሜን ኮሪያ ማስወጣት ሲጀምሩ-ሐሪ ኤስ ትሩማንም ሶል-ላይ የሚመሰረተዉን መንግሥት ዶክተር ስይንግማን ርሔ-እንዲመሩ ተስማሙ።ዋና ፀሐፊ ኪም ኢል ሱንግ «የአሜሪካ ኢንፔሪያሊስት አሸንጉሉት» የሚሉትን የስይንግማንን-መንግሥት መነቃቅሮ-ድፍን ኮሪያን በቀዩ ባንዲራ ሥር ለመግዛት የአሜሪካ ጦር አካባቢዉን ለቅቆ የሚወጣበትን ዕለት በንቃት ከመጠባበቅ በላይ-የሚያስቀድሙት አልነበረም።

አላማ-ፍላጎታቸዉን ከግብ ለማድረስ የሶቬት ሕብረት ጦር ትቶላቸዉ የሔደዉን የጦር መሳሪያ ለአዲሱ ጦራቸዉ እያስታጠቁ፥ የቤጂንግን ቤተ-መንግሥት ለመቆጣጠር ዕለታት ከቀራቸዉ ከቻይና ኮሚንስቶች ጋር ያላቸዉን ወዳጅነትም ያጠናክሩ ገቡ።

ሐምሌ-1948 በተደረገዉ ምርጫ የፕሬዝዳትነቱን ሥልጣን የያዙት-ዶክተር ስይንግማን የሰሜን ጠላታቸዉን ሕልም-አለማ በተገላቢጦሹ መፈለግ-ማለማቸዉ-አልቀረም።ኪም ኢል ሱንግ ለስታሊን እንዳደረጉት ሁሉ ስይንግማንም አላማ-ፍላጎታቸዉን ለሐሪ ኤስ ትሩማን አማክረዉ ነበር።ይሁንና በቅጡ-ያልደረጀዉ የደቡብ ኮሪያ ጦር የሰሜን ኮሚንስት ጠላቱን ደፍሮ የስይንግማንን ልብ እንደማያረካ ጠንቅቀዉ የሚያዉቁት ትሩማን የደቡብ ኮሪያ ወዳጃቸዉ አዲሲቱን ሐገራቸዉን ከመከላከል ባለፍ ወደ ሰሜን መከጀላቸዉን እንዲቆሙ ነበር-የመከሯቸዉ።

ዩናይትድ ስቴትስ ጦርዋን ከደቡብ ኮሪያ ስታስወጣ ግን ሰሜን ኮሪያዎች እንደዛቱት ደቡብን ካጠቁ ዩናይትድ ስቴትስ እጇን አጣጥፋ እንደማትቀመጥ ፕሬዝዳት ሐሪ ኤስ ትሩማን በግልፅ አወጁ። የትሩማን መልዕክት ከሶል፥ ከፒዮንግዮንግም ይልቅ ለሞስኮ እና ለቤጂንጎች ያለመ ነበር።ከሁለት አመት በሕዋላ ያ ምድር ዳግም ጦርነት ሲለኮስበት ትሩማን በርግጥ ቃላቸዉን አላጠፉም ነበር።

ባለፈዉ ሳምንት ሮብ የሰሜን ኮሪያ ጦር ዮንፕዮንግ የተሰኘችዉን የደቡብ ኮሪያ ደሴት በመድፍ ደብድቦ-ሁለት ወታደሮችንና ሁለት ሰላማዊ ሰዎች መግደሉ እንደተሰማ-የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ የትሩማንን ቃል-ምግባር በስልሳ ሁለተኛ አመቱ ግን በዘመኑ ቋንቋ-ለመድገም አላመነቱም።
«ደቡብ ኮሪያ የኛ ተባባሪ ናት።ከኮሪያዉ ጦርነት ጀምሮ ተባባሪያችን እንደሆነች ነች።በዚሕ ወዳጅነት መሠረት ደቡብ ኮሪያ የሚደርስባትን ጥቃት በፅናት እንደምንመክትላት እናረጋግጣለን።»

መልዕክቱ ለፕሬዝዳት ሊ ምቶንግ-ባንግ ወይም ለኪም-ጆንግ ኢል ብቻ አልነበረም።ለቤጂንግ መሪዎችም ጭምር እንጂ።ኦባማ ቃል-በገቡ በሰወስተኛዉ ቀን ጆርጅ ዋሽንግተን የተሰኘችዉን አዉሮፕላን ተሸካሚ መርከብ-ወደ ኮሪያ ልሳነ-ምድር አዘመቱ።የሁለቱ ወዳጆች ጦር ከሰሜን ጠላታቸዉ አፍንጫ ሥር-ከምድር ከባሕር ሚሳዬል-ቦምቡን ያዥጎደጉደዉ ገባ።የጦር ልምምድ።አሉት።

ሰሜን ኮሪያን ከደቡብ ጋር ከሚያዋስነዉ መስመር አንድ መቶ ሐምሳ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚደረገዉ የጦር ልምምድ አላማ፥-አንድ የተለማማጁ ጦር ቃል አቀባይ እንዳስታወቀዉ የሁለቱ ሐገራት ጦር ሰሜን ኮሪያን ለመመከት ዝግጁነቱን ለማጠናከር ነዉ።
«የዚሕ ልምምድ አላማ ሰሜን ኮሪያን ለመቋቋም ያለንን ብቃትና ቁርጠኝነት ለማጠናከር ነዉ።በተጨማሪም የራሳችንን ግዛት ደሕንነት (ጥበቃን) ለማሻሻልና የዩናይትድ ስቴትስንና የደቡብ ኮሪያን ወዳጅነት ለማጠናከር ነዉ።»

Südkorea Insel Yeonpyeong Konflikt mit Nordkorea Dossierbild 1
የሰሜን ጦር የደበደባት ደሴትምስል AP

ድሮ።ዶክተር ስይንግማን ርሔ ሐምሌ-1948 የደቡብ ኮሪያን የፕሬዝዳትነት ሥልጣን ሲይዙ-ለበዓለ-ሲመታቸዉ ከጋበዟቸዉ እንግዶች ዋነኛዉ እስከዚያ ድረስ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያን ይገዛ የነበረዉ የአሜሪካ ጦር አዛዥ ነበሩ።ጄኔራል ዳግላስ ማክ አርተር።ደቡብ ከሚል ቅፅል ጋር እንደ ሐገር የቆሞችዉ የአዲሲቱ ሐገር አዲስ ፕሬዝዳት-የፒዮንግያንግ የጦር ዝግጅት እንዳሳሰባቸዉ በድግስ ፌስታዉ መሐል ለትልቁ እንግዳቸዉ ሹክ አሏቸዉ።

የሁለተኛዉ አለም ጦርነት ጄኔራል የሶል ወዳጃቸዉን ለማረጋጋት ሚስጥር መጠበቅ አላስፈለጋቸዉም። በደቡብ ኮሪያ ላይ የሚፈፀም ጥቃት በካሊፎርኒያ ላይ ከተፈፀመ ጥቃት እኩል እንደሚቆጥሩት ተናገሩ።«ካሊፎርኒያን ከጥቃት መከላከል ያለብኝን ያሕል-ደቡብ ኮሪያንም እከላከላለሁ» አሉ እዉቁ አሜሪካዊ ጄኔራል።

የተፈራዉ አልቀረም።የሶቬት ሕብረትና የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮች ለቀዉ ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ-በሰበብ አስባቡ ሲቆራቆሱ የቆዩት ሰሜንና ደቡብ ኮሪያ ሰኔ-ሃያ-አምስት 1950 የሰሜን ኮሪያ ጦር ከደቡብ ጋር የሚለየዉን ድንበር ሲጥስ ወትሮም ያልጠፋዉ እሳት ያን-ምድር ያጋየዉ ገባ።ጄኔራል ማክአርተር ለደቡብ ወዳጃቸዉ የገቡትን ቃል-ለማክበር ወይም ፕሬዝዳት ትሩማንን ለማስፈቀድ ከስድስት ቀን በላይ አልፈጀባቸዉም ነበር።

ሐምሌ አንድ።የአሜሪካ ጦር ከደቡብ ኮሪያ ጎን ሊዋጋ ዳግም ዘመተ።የኢትዮጵያን ጨምሮ አሜሪካ የመራችዉና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያዘመተዉ የሃያ-አንድ ሐገራት ጦር ለደቡብ ኮሪያ ወግኖ-ሶቬት ሕብረትና ቻይና ከሰሜን ኮሪያ ጎን ቆመዉ ይተላለቁ-ገቡ።ሁለት አመት ያስቆጠረዉ ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠር ሕወት፥አካል-አጥፍቷል።በቢሊዮነ-ቢሊዮናት የሚገመት ንብረት አዉድሟል። አሸናፊም-ተሸናፊም ግን አልነበረም።

ጦርነቱ በ1953 በተኩስ አቁም ዉል ቆመ እንጂ ዘላቂ የሰላም ዉል-አስካሁን አልተበጀለትም። ከሁለተኛዉ የአለም ጦርነት በሕዋላ የብዙ ሐገራት ዜጋ ሕይወት የጠፋ-ደም የፈሰሰበት፥ጦርነት እንደተጀመረ-ጄኔራል ማክ አርተር መጀመሪያ ያደረጉት የሰሜንና የደቡብ ኮሪያ ጦር የሚዋጋበትን አካባቢ መጎብኘት ነበር።መዘዙ እንደ እስከ ዛሬዉ ሁሉ ዛሬም-ጦር ሲያማዝዝ ደግሞ ደቡብ ኮሪያ የሠፈረዉ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር አዛዥ ጄኔራል ዋልተር ሻርፕ ጄኔራል ማክአርተር መጀመሪያ ያደረጉትን ደገሙት።በመድፍ የተመታችዉን ደሴት ጎበኙ።ማክ አርተር ያሉትንም ደገሙት።

«በደረሰን መረጃ እና እዚሕ በአካል ተገኝቼ ባየሁት መሠረት ሰሜን ኮሪያ ይሕን ደሴት ደብድባለች።ይሕ የተኩስ አቁም ስምምነቱ መጣሱን በግልፅ አመልካች ነዉ።»

ከቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍፃሜ በሕዋላ ከአብዛኛዉ አለም የተገለችዉ ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ቦምብ ለመስራት አንድ ሁለት ማለት ከጀመረች ወዲሕ ከምዕራቡ አለም ከፍተኛ ጫና እየተደረገባት ነዉ። ኑክሌር ለመታጠቅ የምታደርገዉን ሙከራ እንድታቆም ለማሳመን «የስድስትዮሽ» በተሰኘዉ ቡድን አማካይነት በየጊዜዉ መደራደር-መወያየቷ አልቀረም።ድርድሩ በተለይ በፕሬዝዳንት ቢል ክሊንተን ዘመን ከአግባቢ ደረጃ ላይ ቢደርስም የፕሬዝዳት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ መስተዳድር ሥልጣን ከያዘ በሕዋላ ግን የተጀመረዉ ሁሉ በጅምር ቀርቷል።

ሰሜን ኮሪያ የዛሬ ሁለት አመት ግድም ከድርድሩ ከወጣች ወዲሕ ትኩረቱን በኢራቅ፥ በአፍቃኒስታን ጦርነት፥ በኢራን የኑክሌር መርሐ-ግብር፥ እና ደግሞ በምጣኔ ሐብት ድቀት ላይ ያደረገዉ ምዕራቡ አለም በተለይ የፕሬዝዳት ኦባማ መስተዳድር የኮሪያን ልሳነ-ምድር ጉዳይ «በይደር» የተወዉ መስሏል።የምዕራቡ አለም ቸልተኝነት በምጣኔ ሐብት ችግር፥ በማዕቀብ፥ ከሌላዉ አለም በመገለል የምትማቅቀዉን ሰሜን ኮሪያን ለሚመሩት ኮሚንስቶች አንዳዶች እንደሚሉት ዉሳጣዊ ችግራቸዉን ዉጪያ የሚያደርጉበትን ሥልት እንዲያሰላስሉ ሳያደርግ አልቀረም።

ከጥቂት አመታት በፊት-የኑክሌር ቦምብ መሞከራቸዉን አስታዉቀዉ ነበር።ባለፈዉ መጋቢት ደግሞ የሰሜን ኮሪያ ጦር የዉሐ-ክልሌን ጣሰ ያለዉን አንድ የደቡብ ኮሪያን መርከብ መትቶ፥ አርባ ስድስት የደቡብ ኮሪያ የባሕር ሐይል ባልደረቦችን ገድሎ ነበር።ካንድ ወር በፊት ደግሞ አዲስ የኑክሌር መርሐ-ግብር መጀመራቸዉን ለአሜሪካ የኑክሌር ባለሙያ አሳይተዉ ነበር።ባለፈዉ ሳምንት መድፍ አስተኮሱ።

የፖለቲካ አዋቂዎች እንደሚሉት ሰሜን ኮሪያ በተከታታይ የሰነዘረችዉ ጥቃትና ማስፈራራት ተደማጭነቷን ለማሳየት በዉጤቱም የደቀቀዉን ምጣኔ ሐብቷን የምትጠግንበትን አቅም ምዕራቡ እንዲከፍላት ነዉ።ሌሎች ደግሞ እድሜ-በሽታም የተጫጫናቸዉ የሐገሪቱ መሪ ኪሚ-ጆንግ ኢል ሥልጣናቸዉን ለሃያ-ሰባት አመት ልጃቸዉ ለማዉረስ የጀመሩትን እቅድ ገቢር በማድረጉ ሒደት የዉስጥ ተቃዉሞ እንዳይነሳ አቅጣጫ ለማስቀየር ወይም ለማፈን ነዉ።

ሰሜን ኮሪያ-ግን ያደረገችዉን ሁሉ ያደረገችዉ የደቡብ ጠላቷን ትንኮሳ ለመከላከል እንደሆነ በተደጋጋሚ እየተናገረች ነዉ።ከደቡብ በኩል የተሰነዘረ ጥቃት ወይም ትንኮሳ ሳይኖር በተለይ ሰሜን ኮሪያ የደቡብን መርከብ ለማጥቃት ሆነ ደሴቲቱን ለመደብደብ መድፈሯን ብዙዎች ይጠራጠራሉ። የሰሜን ኮሪያ የቅርብ ወዳጅ የምትባለዉ ቻይና ምክንያቱ ምንም ሆነ ምን የጋመዉን ዉጥረት ለማስወገድ አብነቱ የስድስትዮሽ ወደሚባለዉ ድርድር መመለስ ነዉ ባይናት።

«የስድስትዮሹ ድርድር ተካፋዮች የሚያደርጉትን ዉይይትን እንደገና መጀመር አለባቸዉ ብለን እናምናለን።የኮሪያ ልሳነ ምድርን ሰላምና መረጋጋት ለማስጠበቅ እና የሰሜን ምሥራቅ እስያን ደሕንነት ለማስከበር ስድስቶቹ ሐገራት ሐሳብ ቢለዋወጡ ጥሩ ነዉ።»

ጃፓን-የቻይና ተቀናቃኟን ሐሳብ አልጠላችዉም።ዩናይትድ ስቴትስም የቻይኖችን ሐሳብ አልተቃወመችዉም።ደቡብ ኮሪያም «በጥልቀት አስብበታለሁ» ከማለት ባለፍ ሐሳቡን ዉድቅ አላደረገችዉም።ከሶል በግልፅ የሚሰማዉ ግን ሌላ ነዉ።ባለፈዉ መጋቢት የሰሜን ኮሪያ ጦር አርባ-ስድስት የደቡብ ኮሪያ የባሕር ሐይል ባልደረቦችን ሲገድል የደቡብ ባሕር ጦር አዛዥ ያሉት ብዙም አልተሰማ ነበር።በቀድም ግን አዛዡ ዮ ናክ-ጁን ዛቱ።
«የሰሜን ኮኢሪያ ለፈፀመችዉ ወረራ መቶ-እንዲያዉ ሺሕ እጥፍ ዋጋ ትከፍላታለች።»

USA Nordkorea Südkorea Flugzeugträger George Washington im Hafen von Busan
የዩናይትድ ስቴትስ አዉሮፕላን ተሸካሚ-መርከብ ጆርጅ ዋሽንግተንምስል AP

የስድስትዮሽ የተሰኘዉን ድርድር «ዋጋ ቢስ» በማለት ያቋረጠችዉ ሰሜን ኮሪያ ድርድሩ እንዲጀመር የቤጂንግ ወዳጆችዋ ላቀረቡት ጥያቄ የሰጠችዉ መልስ በግልፅ አይታወቅም።የዩናይትድ ስቴትስና የደቡብ ኮሪያ ጦር የጋራ ልምምድ ሲጀምር የምድር-ለምድር ተምዘግዛጊ ሚሳዬሎችዋን ማጥመዷ ግን ተሠምቷል።ከሶል ለሚሰማዉ ዛቻ-የዛቻ አፀፋ ለመስጠትም አልሰነፈችም።

«የዩናይትድ ስቴትስና የደቡብ ኮሪያ ጠብ ጫሪነት እስከቀጠለ ድረስ፥ ጦራችን ያለምንም ማስጠንቀቂያ ለሁለተኛ ወይም ለስወተኛዉ ጊዜ ለመደብደብ አያመነታም።»
የሰሜን ኮሪያ ቴሌቪዥን።የኮሪያ ልሳነ ምድር-እንደሮዉ ዘንድሮም ለዉጊያ ይዛት፥ ይፎከር ይተኮስበታልም።ጦርነት በርግጥ የለም።የስድስት፥ የሁለት የሰወስትዮሽ እየተባለ ሠላም-ድርድር ይነገርበታል።ሠላም ግን አያዉቅም።

ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ