1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮሮና ስጋት የጋረደው የስደተኞች ጉዳይ

ዓርብ፣ ሰኔ 19 2012

በዓለም ዙሪያ የኮሮና ወረርሽን ከተከሰተ በኋላ የስደተኞች ጉዳይ ዓብይ ርዕስ መሆኑ ቀንሷል። በዓለም ላይ ስንት ሰዎች በበሽታው ተያዙ?  ስንት ሰዎች ሞቱ­?  እያልን ስንጨነቅ እና መረጃ ስናሰባስብ በሌላ በኩል በዓለም ላይ 80 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። አብዛኞቹ ደግሞ ወጣቶች ናቸው።

https://p.dw.com/p/3eNZv
Seenotrettungsschiff Sea Watch 3 nimmt Flüchtlinge vor libyscher Küste auf
ምስል picture-alliance/dpa/Sea Watch

የኮሮና ስጋት የጋረደው የስደተኞች ጉዳይ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጎርጎሮሲያኑንን ሰኔ 20 ቀን የዓለም የስደተኞች ቀን ሲል ከሰየመ ዘንድሮ 20 ዓመት ሞላው። የድርጅቱ ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ 80 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከሀገራቸው ወይም ከሚኖሩበት ቀያቸው ሳይወዱ ተገደው መፈናቀላቸውን የዘንድሮውን የዓለም የስደተኞች ቀን አስታከው በሰጡት መግለጫ ገልፀዋል። አስደንጋጩ ነገር ግን ጉቴሬዝ እንዳሉት  10 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑት ባለፈው ዓመት ብቻ የተፈናቀሉ ናቸው። ድሮም በችግር ለሚሰቃዩት ስደተኞች የዘንድሮው ዓመት ደግሞ ሌላ ፈተና ይዞላቸው መጥቷል። ኮቪድ 19ን። የድረሱልን ጥሪም በተለያዩ ሀገራት ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ዘንድ ይሰማል። በ 30ዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኘው ሰይድ ከነዚህ አንዱ ነው። ዛሬ በሱዳን ሀገር በስደት ላይ ይገኛል። ከሀገሩ የተሰደደው በፖለቲካ ምክንያት ነው።  « ባለፉት 27 ዓመታት የዘር ማጥቃት ይደርስብን ነበር። ሁል ጊዜ እስር ቤት ከመግባት እና ከመጨናነቅ እስቲ ወጣ ማለት ይሻላል ብለን ነው።  »  ሰይድ ሲሰደድ ብቻውን አልነበረም። ሰይድ የኮሮና በሽታ የለም ከሚሉት ሰዎች አንዱ ነው። እሱ እንደሚለው ሰዎች ሆን ብለው ስደተኞች ላይ በደል ለመፈፀም የሚጠቀሙበት ዘዴ ነው። ወጣቱ ከሀገሩ ከወጣ 10 ዓመት ገደማ ሆነው። ከእሱ በኋላ የተሰደዱ ሌሎች ጓደኞቹ እንዲሁ በፖለቲካ ጉዳይ  ወደ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ሳውዲ ዓረቢያ፣ ሊቢያ እና ካታር ተሰደው እንደሚገኙ ይናገራል። አሁን ግን በጣም እያሳሰበው ያለው ሊቢያ ያሉት የጓደኞቹ ሁኔታ ነው።  « ከእስር ተለቀናል ወይ በባህር እንሄዳለን ወይ ደግሞ ወደእዛ እንመጣለን ብለውኝ ነበር። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ስልካቸው አይሰራም።»

Grichenland Flüchtlinge im Hafen von Piräus
የሶሪያ ስደተኞች በግሪክምስል Getty Images/AFP/L. Gouliamaki

በዓለም ላይ ባለፉት ዓመታት በፖለቲካ ፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በጦርነት ምክንያት የሚሰደደው ሰው ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል። ሌላው ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ችግር ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰሞኑን እንዳስታወቀው ኢትዮጵያ በጎርጎርሳውያኑ 2020 ማብቂያ ላይ ግማሽ ሚሊዮን በሚደርሱ ተመላሽ ስደተኞች ልትጨናነቅ ትችላለች ። ለዚህም ምክንያቱ የዓለም ስጋት በሆነው የኮሮና መረርሽኝ ስራ አጥ በመሆናቸው ነው። ቱርክ አራት ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ስደተኞችን በማስጠለል ቀዳሚዋ ሀገር እንደሆነች የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት (UNHCR) ይጠቁማል። ከነዚህም  3,7 ሚሊዮኑ የሶርያ ስደተኞች ናቸው። በኮሎምቢያ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ የቬንዙዌላ ስደተኞች ይገኛሉ። ኢትዮጵያም ብትሆን  ስደተኞችን በመቀበል ከዓለም በ10ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። በሀገሪቱ ከ735 ሺ በላይ ስደተኞች ተጠልለው ይገኛሉ። አብዛኞቹም ከዛው ከጎረቤት ሀገራት ናቸው። 

Kolumbien UNHCR-Camp in Maicao
የቬንዙዌላ ስደተኞች ኮሎምቢያ ውስጥምስል picture-alliance/AA/J. Torres

ጀርመን ደግሞ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ 1,2 ሚሊዮን ስደተኞች ይገኛሉ።  ከነዚህ አንዱ ኢትዮጵያዊው አብዲ ነው። አብዲ እኢአ በ 97 ዓመተ ምህረት በነበረው የፖለቲካ ችግር ነው ከሀገር የወጣሁት ይላል። ዛሬ የሚኖርበት ጀርመን ሀገር እስከሚደርስ ብዙ ሀገራትን ማቋረጥ ነበረበት። አብዲ ምንም እንኳን ጀርመን ሀገር ሲኖር 9 ዓመት ሊሞላው ቢሆንም የሚኖረው በጀርመንኛ « ሀይም» ተብሎ በሚጠራው የስደተኞች ማቆያ ነው። በዚህ  ቆይታው ስራ ይሰራ ነበር። አሁን ግን አይሰራም። እሱ እንደሚለው ጉዳዩን የሚመለከተው አካል ሆን ብሎ ወረቀቱን እንዳያገን ከስራ እንዲባረር አድርጓል።
ጀርመን ሀገር ኮረና ከተከሰተ በኋላ ተገን የሚጠይቀው ሰው ቁጥር ቀንሷል። በግንቦት ወር ለምሳሌ ካለፈው ዓመት በ 3777 የቀነሰ ነበር። ለመቀነሱ በምክንያትነት የሚጠቀሰው በኮሮና ምክንያት በርካታ የአውሮፓ ህብረት ሀገራት ድንበራቸውን በመዝጋታቸው ነው።  ቀድመው የገቡት እንደ አብዲ ያሉትም ቢሆኑ የተገን ጥያቄያቸው እስካሁን መፍትሄ አላገኘም።  እስካሁን የልደት ማስረጃዬን ያልሰጠኋቸው ይመልሱኛል በሚል ስጋት ነው ይላል አብዲ፤ እንደሰጋው ሀገሩን በአንድ ወር ውስጥ ለቆ እንዲወጣ ደብዳቤ ደርሶታል። ይሁንና አሁንም እንዳይመልሱት እየታገለ ነው። «  ከዚህ ሀገር ላለመውጣት ፣ ኮሮናም ስላለ የትም ሀገር መሄድ አይቻልም እና እሱን ጠበቃ ይዤ እየተከራከርኩ ነው የምገኘው።» አብዲ በሱዳን እና ሊቢያ አድርጎ ነው ጣሊያን ኃላም ጀርመን የገባው። በጉዞው ላይ ብዙ ባህር ላይ የሞቱ ሰዎች አይቷል። ብዙ በደልም ደርሶብኛል ይላል። ጀርመን ከገባ እና ቋንቋ ከተማረ በኋላ ለ ሶስት ዓመታት ምግብ ቤት ውስጥ የአብሳዩ ረዳት ሆኖ ይሰራ ነበር። ከዛም አንድ ትልቅ መጋዘን ውስጥ ሰርቷል። በስራውም ትሁት ስለነበር መስሪያ ቤቱ ቋሚ አድርጎት ነበር። ነገር ግን የስደተኞቹን ጉዳይ የሚመለከተው አካል ይህ እንዲሆን አልፈቀደም ይላል።  ስራ አጥ ከሆነ አሁን አምስት ወር ሆኖታል። « እኔ ብቻ አይደለሁም። በጣም ብዙ ሰው ነው እየተሰቃየ ያለው። በይ በጊዜ ሂድ ብለውኝ ቢሆን ኖሮ ይሻል ነበር።»

Libyen Migranten und Flüchlinge im Mittelmeer
ምስል picture-alliance/AP/S. Palacios

የጀርመን የስደተኛው ምክር ቤትም ልክ እንደ UNHCR ተገን ጠያቂዎች የተገን ጥያቄ አቅርበው ለዓመታት በተስፋ መጠበቅ እንደሌለባቸው ይስማማል። ይሁንና 
እንደ አብዲ ውጤቱን ለዓመታት የሚጠባበቁ 200 000 ገደማ ስደተኞች ጀርመን ውስጥ ይገኛሉ።  

ልደት አበበ

ሂሩት መለሰ