1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮሶቮና የሰርብያ ቀዝቃዛ ጦርነት መፍትሄ ያገኝ ይሆን?

ሰኞ፣ ሚያዝያ 21 2011

በኮሶቮና በሰርብያ መካከል ያለዉን ዉዝግብ ለመፍታት በጀርመኗ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልና በፈረንሳዩ ፕሬዚደንት ኤማኑዌል ማክሮ የሚመራ ጉባዔ በርሊን ላይ ተካሄደ። ጉባኤዉ የቦስንያ ሄርዞጎቪና፤ አልባንያ፤ሰሜናዊ መቄዶንያ እና የቦሲንኒያ እና ስሎቪንያ የመንግሥት ተጠሪዎች እንዲሁም የአዉሮጳ ኅብረት የዉጭ ጉዳይ ተጠሪ ተገኝተዋል

https://p.dw.com/p/3HfDL
Bulgarien EU-Balkan-Gipfel in Sofia | Merkel & Thaci & Vucic
ምስል Reuters/V. Donev

ስድስት የምዕራብ ባልካን ሃገራትን ለማቀራረብ ጀርመን እና ፈረንሳይ ከሃገራቱ ተወካዮች  ጋር በርሊን ላይ ዛሬ ጉባዔ ተቀመጡ።  በጀርመኗ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል እና በፈረንሳዩ ፕሬዚደንት ኤማኑዌል ማክሮ የሚመራዉ ይህ ጉባዔ የቦስንያ ሄርዞጎቪና፤ አልባንያ፤ሰሜናዊ መቄዶንያ እና የአዉሮጳ ኅብረት አባል ሃገር የሆኑት የቦሲንኒያ እና ስሎቪንያ የመንግሥት ተጠሪዎች እንዲሁም የአዉሮጳ ኅብረት የዉጭ ጉዳይ ተጠሪ ፌሬድሪካ ሞጎሮኒን ያካተተ መሆኑ ታዉቋል።  ጉባዔዉ በተለይ በተወዛጋቢዎቹ ሰርብያና ኮሶቮ ላይ ያተኮረ መሆኑ ነዉ የተነገረዉ። በጉባዔዉ የሁለቱ ሃገራት ተጠሪዎች በቅድምያ ሃሳብ እንዲለዋወጡ እንደሚደረግ ቢነገርም ስምምነት ላይ ይደርሳሉ ተብሎ ግን አንደማይጠበቅ ተነግሮአል። የቀድሞ ይጎዝላቭያ አካል የነበረዉ በኮሶቮ የአልባንያ ዝርያ በሚበዛበት አዉራጃ በጎርጎረሳዉያኑ 2008 ዓ.ም ከሰርብያ መገንጠሉን ቢያዉጅም የቤልግራዱ መንግሥት እስካሁን እዉቅና አለመስጠቱ ዉዝግቡን እንዳካረረዉ ተመልክቶአል። በሰርቢያና በኮሶቮ መካከል ያለዉን ዉዝግብ ለመፍታት ከመንፈቅ በፊት ጀምሮ ጥረት ቢደረግም እስካሁን ግን ምን ዉጤት አለመገኘቱ ይታወቃል።