1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮሶቮ ነጻነትና የኤኮኖሚ ዕድገት ዕጣዋ

ረቡዕ፣ የካቲት 12 2000

የቀድሞይቱ የሰርቢያ ክፍለ-ሐገር የኮሶቮ ብዙሃን አልባኖች ለዓመታት ሲያልሙለት የቆየውን የብቻ መንግሥት ምሥረታ በአንድ ወገን የነጻነት አዋጅ ባለፈው ዕሑድ ዕውን አድርገዋል። ታዲያ ሰርቢያ ነጻነቱን መቃወሟ፤ ውሎ አድሮም ማዕቀብ ልትጥል መቻሏ፤ የኮሶቮን የወደፊት የፖለቲካና የኤኮኖሚ ሂደት መፈታተኑ አልቀረም።

https://p.dw.com/p/E0cN
ምስል picture-alliance/ dpa

የዓለም ሕብረተሰብ ተገንጧይዋ ክፍለ-ሐገር በተባበሩት መንግሥታት ጥላ ሥር በተዳደረችባችው ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ለአካባቢው ልማት ከሃያ ሚሊያርድ ዶላር በላይ አፍሷል። ግን ኮሶቮ አሁንም ለዕድገት የሚያበቃ የምጣኔ-ሐብት መሠረት እንደሚጎላት ነው የመስኩ አዋቂዎች የሚናገሩት። ኮሶቮ የተደቀነባትን የኤኮኖሚ ፈተና ልትወጣው ትችላለች ወይ? በዚህ ረገድ የነጻነቱስ ትርጉም እስከምን ነው?

ኮሶቮ ሰሞኑን ነጻነቷን በማወጅ የራሷን መንግሥታዊ ሕልውና ይፋ ብታደርግም ገና የተባበሩት መንግሥታት ዓባል ለመሆን አልቻለችም። የአንድ ወገኑ የነጻነት አዋጅ ምንም እንኳ የአሜሪካንና የቀደምቱን የአውሮፓ ሕብረት ድጋፍ ቢያገኝም የሰርቢያ ተቃውሞ ሕጋዊ አተረጓጎሙን ሲበዛ ነው ያከበደው። የጸጥታው ም/ቤት የቤልግሬድ አጋር በሆነችው በሩሢያ ተቃውሞና በቻይና ስጋት ሳቢያ በጉዳዩ ከአንድነት ላይ መድረስ አልቻለም። ይህ ደግሞ ጊዜው እየገፋ በሄደ ቁጥር የኤኮኖሚውን ሁኔታ እያከበደው የሚሄድ ነው የሚመስለው።

የኮሶቮ መሪዎች የሚያልሙት ነጻነታችው ትርጉም አግኝቶ የአውሮፓን ሕብረት አንዴ በዓባልነት በመቀላቀል የፖለቲካና የኤኮኖሚ ሕልውናቸውን ለማረጋገጥ ነው። ሆኖም ለሕብረቱ ዓባልነት የሚያበቃውን መስፈርት አሟልቶ ከዚህ ግብ ለመድረስ ከወቅቱ ጭብጥ ሁኔታ ስሌት ብዙ ዓመታት እንደሚፈጅ አንድና ሁለት የለውም። ኮሶቮ ዛሬ በባልካኑ አካባቢ ድሆች ከሚባሉት አንዷ ናት። የክፍለ-ሐገሪቱ አጠቃላዩ ብሄራዊ ገቢ በነፍስ-ወከፍ ሲታሰብ ከ 1.100 ዶላር አይበልጥም። እያንዳንዱ ነዋሪ ባለፈው ዓመት ለአጠቃላዩ ምርት ያደረገው አስተዋጽኦ እንግዲህ በአማካይ ይህን ያህል መሆኑ ነው።

እርግጥ ይህ ከዝቅተኛው የሕዝብ ቁጥር አንጻር ከፍ ያለ ይመሰል እንጂ በትክክለኛ ንጽጽር ከኢትዮጵያ ወይም ከዛምቢያ አይበልጥም። በቅርቡ የአውሮፓ ዓባል ከሆኑት ከቡልጋሪያና ከሩሜኒያ አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት ሲነጻጸር ደግሞ እንዲያውም በአሥር ዕጅ ዝቅ ይላል። የልማት ተሥፋን የሚያዳብር ጽኑ የኤኮኖሚ መሠረት አለ ለማለት አይቻልም። ሌላው ችግር የኤኮኖሚው ዕርምጃ ከወሊዱ የተፋጠነ ዕድገት፤ ማለት ከሕዝቡ ቁጥር መናር ጋር ተስተካክሎ የማይራመድ መሆኑ ነው። ይህም የራሱ መዘዝ ይኖረዋል።

ዛሬ ሁለት ሚሊዮን ገደማ ከሚጠጋው የኮሶቮ ነዋሪ ሲሦው ከ 14 ዓመት ዕድሜ በታች የሚገኝ ነው። በረጅም ጊዜ አምራች ሃይል የማፍራት ጠቀሜታ ቢኖረውም በአጭርና በመካከለኛ ጊዜ ግን የሥራ አጥነትን ችግር ማጠንከሩ የሚቀር አይመስልም። በያመቱ በሥራ ፍለጋ የሙያ ገበያውን የሚያጣብቡት ነዋሪዎች ቁጥር እየጨመረ መምጠቱ ታይቷል። የአካባቢው የፖለቲካ ሣይንስ ተመራማሪ ቤህሉል ቤጋጅ እንደሚሉት ከሆነ ሁኔታው ብዙም የሚያበረታታ አይደለም።

“ከኮሶቮ ሕዝብ ግማሹ በቂ ምግብ ባለማግኘት የተጎዳ ነው። 15 በመቶው ጨርሶ የሚበላው ነገር የለውም። 330 ሺህ ገደማ የሚጠጋው ደግሞ ሥራ የለውም። ከዚሁ ሌላ 75 ሺህ በጡረታ ዕድሜ ላይ የሚገኙና 25 ሺህ የሚሆኑት መምሕራን በኑሮ ሁኔታቸው ደስተኞች አይደሉም”

ኮሶቮ የግሉ የኤኮኖሚ ዘርፍ ያን ያህል የተስፋፋባት አይደለችም። በመሆኑም ታላቁ ቀጣሪ ወይም አሠሪ መንግሥት ነው። ከአካባቢው ሁኔታ ሲነጻጸር ከፍተኛ ደሞዝ ከፋዮች ቢኖሩ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች ብቻ ናቸው። በግሉ የምጣኔ-ሐብት ዘርፍ ደግሞ ከግማሽ የሚበልጡት አነስተኛ ነጋዴዎች ሲሆኑ ግፋ ቢል በዝቅተኛ ደሞዝ ሶሥት ሠራተኞች መቅጠር ቢችሉ ነው። ስለዚህም እዚህም-እዚያም ቋሚ ያልሆነ ሥራ እየሰራሩ በውጭ ሃገራት ከሚኖሩ ዘመዶቻቸው በሚላክ ገንዘብ የሚተዳደሩት ብዙዎች ናቸው።

በዩ.ኤስ.አሜሪካ፣ በጀርመን፣ በስዊስና በሌሎች በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉ አገሮች የሚሰሩት የኮሶቮ አልባኖች 375 ሺህ ገደማ ይጠጋሉ። የኮሶቮው የኤኮኖሚ ባለሙያ ኢብራሂም ሬቼፒ እንደሚሉት እነዚሁ ወደ ትውልድ አገራቸው የሚልኩት ገንዘብም በቀላሉ የሚገመት አይደለም።

“ገንዘቡ 450 ሚሊዮን ኤውሮ ገደማ ይጠጋል። ይህም ከጠቅላላው የኮሶቮ በጀት 50 በመቶው መሆኑ ነው። ያለዚህ የገንዘብ ምንጭ እንዴት መኖር እንደምንችል አላውቅም። ወደ አገር የምናስገባው ምርት 1.5 ሚሊያርድ ኤውሮ የሚያወጣ ሲሆን ወደ ውጭ የምንሸጠው 150 ሚሊዮን ቢደርስ ነው”

እንደ ኢብራሂም ሬቼፕ የወደፊቱ ተሥፋ ለውጭ መዋዕለ-ነዋይ አቅራቢዎች ገበዮችን በመክፈትና በድንበር ልቅ መሆን ላይ ጥገኛ ነው። እንበል ዋና ከተማይቱ ፕሪሽቲና ውስጥ ሥራ ያጣ ሰው ወደ ቦስና ወይም ወደ ጀርመንና ሌሎች አገሮች ተሻግሮ መሥራት እንዲችል ማድረግ ያስፈልጋል። ችግሩ የአውሮፓ ሕብረት ይህን መሰሉን ከኤኮኖሚ ችግር የመነጨ ፈለሣ የማይደግፍ መሆኑ ላይ ነው። ፕሪሽቲና ውስጥ የሚገኙ የሕብረቱ ባለሥልጣናት በርካሽ ጉልበትና በአነስተኛ ግብር የኮሶቮን የተፈጥሮ ሃብት ማጠቀሙ ይበጃል ባዮች ናቸው።

የተፈጥሮው ጸጋም በጥቂቱ የሚገመት አይደለም። በኮሶቮ ከርሰ-ምድር ውስጥ ከሃያ ሚሊያርድ ቶን የሚበልጥ ፎስፈርና ዚንክ፤ እንዲሁም 15 ሚሊያርድ ቶን የማዕድን ከሰልና ያንኑ ያህል ኒኬል ተከማችቶ እንደሚገኝ ነው የሚነገረው። ሌሎች ብረታ-ብረትና የእርሻ ምርቶች የውጭ ንግዱ የገቢ ምንጭ እንዲሆኑም ለማድረግ ይታሰባል። ታላቁ የወደፊት ተሥፋ የተጣለው ደግሞ በተለይ በኤነርጂው መስክ ላይ ነው። እርግጥ በወቅቱ የኮሶቮ የኤነርጂ ተቋም በየዕለቱ የሚያመርተው 800 ሜጋ-ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ብቻ ነው።

በአንጻሩ ውስጣዊው ፍጆት አንድ ሺህ ሜጋ-ዋት ገደማ ይጠጋል። ድሃው የሕብረተሰብ ክፍል የኤሌክትሪኩን ዋጋ ለመክፈል የማይችል በመሆኑ ደግሞ ከጎረቤት አገሮች ሃይል መግዣ የጎደለውን ለማሟላት የሚሆን ገንዘብ የለም። ይሁንና ሶሥተኛ የከሰል ሃይል ማመንጫ ጣቢያ በመገንባት ችግሩን ለመፍታት ነው የሚታሰበው። የኩባንያው ቃል-አቀባይ ኔዚር ሢናኒን እንዳስረዱት ዓለምአቀፍ የግንቢያ ጨረታ በቅርቡ የሚወጣ ይሆናል።

“በ 60ኛዎቹ ዓመታት የታነጸው አሮጌው የሃይል ማመንጫ ጣቢያ ኮሶቮ-ኤ ከእንግዲህ የሚያገለግለው ለሰባት ዓመታት ብቻ ነው። ኮሶቮ-ቢ ደግሞ እስከ 2024 መስራቱን ይቀጥላል። ከዚያ በኋላ ኮሶቮ ሰፊ የከሰል ሃብቷን በመጠቀም የኤሌክትሪክ ሃይል ወደ ውጭ መሸጥ ትችላለች። ለዚህም ነው ሶሥተኛው ማመንጫ ጣቢያ የሚታሰበው”

ሢናኒን አያይዘው እንዳሉት በ 2014 ዓ.ም. ገደማ ግንቢያው የሚጠናቀቀው ኮሶቮ-ሢ 2.100 ሜጋ-ዋት ሃይል ማምረት የሚችል ይሆናል። የሚገለገለውም በሰሜን ሣይሆን በአካባቢው በደቡብ ያለውን ከሰል ነው። ዕቅዱ ኮሶቮ የኤኮኖሚ ነጻነቷን ለማረጋገጥ በምታደርገው ጥረት እንደ አንድ ተጨማሪ ዕርምጃ ሆኖ ነው የሚታየው። ምክንያቱም ብዙሃኑ አልባኖች ሰርቦች ሰፍረው በሚገኙበት ሰሜናዊ ዳርቻ የሚገኘውን የተፈጥሮ ሃብት መቆጣጠር አይችሉም። በሌላ በኩል ሰርቢያ ከቀድሞዎቹ የዩጎዝላቭ ሬፑብሊኮች ከማቄዶኒያና ከክሮኤሺያ ጋር ዋነኛዋ የንግድ ተለዋዋጭ ሆና መታየቷ ይቀጥላል።

እርግጥ ቤልግሬድ የኮሶቮን መገንጠል አስመልካታ ያሰማችውን የኤኮኖሚ ማዕቀብ ዛቻ ዕውን ካደረገች የኤነርጂው ዋጋ ንረት ቢቀር አሥር በመቶ መጨመሩ የማይቀር ነው። ይህ ደግሞ ከአሁኑ ከአውሮፓ-ሕብረት ደረጃ የደረሰው የፕሪሽቲና የዋጋ ንረት አንጻር ሲታሰብ የባሰ ሸክም ነው የሚሆነው። በአጠቃላይ የኮሶቮ የኤኮኖሚ ዕርምጃ ውጣ-ውረድ የበዛው ሣይሆን የሚቀር አይመስልም።