1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኮትዲቯር ዉዝግብ የሽምግልናዉ ጥረት

ረቡዕ፣ ጥር 11 2003

አንድ የአፍሪቃ መሪ ባግቦ መወገድ አለባቸዉ ሲል ኦዲንጋ የመጀመሪያዉ ናቸዉ።አንድ የአፍሪቃ መሪ የሐይል እርምጃ መወሰድ የለበትም ሲል ደግሞ ዶ ሻንቶስ የመጀመሪያዉ ናቸዉ።

https://p.dw.com/p/QtXb
ዋታራና ኦዲንጋምስል AP

የኮትዲቯር ተቀናቃኝ ፖለቲከኞችን እንዲሸመግሉ የአፍሪቃ ሕብረት የሰየማቸዉ የኬንያ ጠቅላይ ሚንስትር ራይላ ኦዲንጋ ያደረጉት ሙከራ መክሸፉን አስታወቁ።በኮትዲቯሩ ምርጫ ተሸነፍዋል የሚባሉት የሐገሪቱ ፕሬዝዳት ሎራ ባግቦንና ማሸነፋቸዉ የተመሠከረላቸዉ አላሳኔ ዋታራን ባለፈዉ ሰኞና ማክሰኞ ያነጋገሩት ኦዲንጋ እንደሚሉት የድርድሩ አማራጭ ከእንግዲሕ አብቅቷል።ባግቦን በጦር ሐይል እንደሚያስወግዳቸዉ የሚዝተዉ የምዕራብ አፍሪቃ የምጣኔ ሐብት ማሕበረሰብ ዛሬም እንደዛተ ነዉ።የባግቦ ወዳጅ የሚባሉት የአንጎላዉ ፕሬዝዳት በበኩላቸዉ የሐይል አማራጭ መፍትሔ አይሆንም ባይ ናቸዉ።ነጋሽ መሐመድ ዝርዝሩን አጠናቅሮታል።

የኬንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ራይላ ኦዲንጋ እንደ አፍሪቃ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ፥ የኮትዲቯርን ተቀናቃኝ መሪዎች ሲያነጋግሩ የሰሞኑ ሁለተኛቸዉ ነዉ።የምዕራብ አፍሪቃ የምጣኔ ሐብት ማሕበረሰብ ከወከላቸዉ ከሌሎች ሰወስት መሪዎች ጋር ሆነዉ ያደረጉት የመጀሪያዉ ጥረት ያመጣዉ ዉጤት አልነበረም።ተስፋ ግን አልቆረጡም ነበር።

የመጀመሪያዉ ዙር ድርድር በከሸፈ በሁለተኛዉ ሳምንት ዳግም ወደ አቢዣን የሔዱትም ከመሔዳቸዉ በፊት እንዳስታወቁት ዉዝግቡን በድርድር ለመፍታት ተስፋ አለ-ከሚል እምነት ነበር።ሔዱ።ሎራ ግባግቦን አነጋገሩ።እንደገና ተስፋ አለ-አሉ።

«ከፕሬዝዳንት ባግቦ ጋር ጠቃሚ ዉይይት አድርገናል።ባለፈዉ ጊዜ እዚሕ በነበርንበት ወቅት ያነሳናቸዉን ጉዳዮች አንስተናል።በዉይይቱ የመግባባት እመርታ አሳይተናል።የመወያያት ሐሳብን አንስተናል።ይሕ ግን በርግጥ ከተወሰኑ ቅድመ-ሁኔታዎች ጋር የሚከወን ነዉ።ከፕሬዝዳት ዋታራ ጋር ለመወያየትና ከሌለኛዉ ወገን ጋር የደረስንበትን ስምምነት ለማስረዳት ቀጠሮ አለን።»

Elfenbeinküste Wahl und Unruhen Flash-Galerie
የተመድ ሠራዊትምስል AP

ኦዲንጋ ከሁለተኛዉ የኮትዲቯር ፕሬዝዳት ከአላሳኔ ዋታራ ጋር የነበራቸዉ ቀጠሮ-ዉይይት ተከበረ።ተደረገም።ጠብ ያለ ነገር-ግን የለም።ለፖለቲካ-ዲፕሎማሲዉ ወግ ሽምግልና ድርድር እየተባለ የሚድበሰበዉ ጉዳይ ገቢራዊ ፍቺዉ አንድ-ቢበዛ ሁለት ነዉ።ባግቦ-ሥልጣን መልቀቅ አለባቸዉ፥ ዋታራ ደግሞ ባግቦን ላለ መጉዳት መወንጀል ቃል-ይገባሉ።

ወትሮም በምርጫ ተሸንፈኸል መባሉን እንቢኝ ያሉት ባግቦ-አሁንም እንቢኝ አሉ።እና ኦዲንጋ የሟሸሽ ተስፋቸዉን ይዘዉ አክራ-ጋና ገቡ።እስከ ዛሬ ፕሬዝዳት በጣም ከወረደ-ሌለኛዉ ወገን እያሉ በአክብሮት ይጠሯቸዉ የነበሩ-ባግቦን ሚስተር ይሏቸዉ-ያዙ።ሁለተኛ ሙከራቸዉ ከሸፈ።

«ከሚስተር ባግቦና ከተመራጭ ፕሬዝዳት አላሳኔ ዋታራ ጋር እስከ ሌሊት ድረስ የቀጠለ ጥልቅ ዉይይት ብናደርግም፥ ከስምምነት ለመድረስ የሚያስፈልገዉ ለዉጥ ገቢራዊ አለመሆኑን ሳስታዉቅ እያዘንኩ ነዉ።»

ኦዲንጋ በተለይ የዋታራና ደጋፊዎቻቸዉ ያሉበትን ሆቴል የከበበዉን ጦር ከአካባቢዉ ለማራቅ ባግቦ ለሁለተኛ ጊዜ የገቡትን ቃል-ለሁለተኛ ጊዜ አፈረሱት-በማለት ባግቦን ቃል አባይ አድርገዋቸዋል።

«እገዳዉ እንደሚነሳ ሚስተር ባግቦ ትናንት ቃል-ገብተዉልኝ ነበር።ቃላቸዉን ግን አጠፉት።በሁለት ሳምንት ዉስጥ ለሁለተኛ ጊዜ።»

አለም አቀፉ ማሕበረሰብ አይንሕ ላፈር ያላቸዉን ባግቦን ከሥልጣን በጦር ሐይል ለማስወገድ ካለፈዉ ታሕሳስ ጀምሮ የሚዝተዉ የምዕራብ አፍሪቃ ማሕበረሰብ ዛቻ ፉከራዉን ገቢር-ማድረግ አለማድረጉ-ወይም የሚያደርግበት መንገድ ግራ እንዳጋባ ነዉ።ማሕበረሰቡ ግን አሁንም እንደዛተ ነዉ።

የኬንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር እንደሚሉትም ባግቦን ለማስወግድ የከንግዲሁ አማራጭ «ማዕቀቡን ጠበቅ-ለጦር ሐይሉ ርምጃ ታጠቅ-» ነዉ።የባግቦ ወዳጅ እየተባሉ የሚታሙት የአንጎላዉ ፕሬዝዳንት ሆሴ ኤድዋርዶ ዶ ሻንቶስ እንደሚሉት ግን የሐይል እርምጃ ተቀባይነት የለዉም።

«በሐይል፥በዛቻና ማስፈራራት ወይም በሽብር የሚመጡ መፍትሔዎች ተቀባይነት የላቸዉም።እንዲሕ አይነት ርምጃዎች አለም አቀፍ መርሕን የሚጥሱ፥ የሕዝቡን ሰላም የሚያብጡና የብልፅግና እርምጃዎችን የሚያሰንክሉ ናቸዉ።»

Elfenbeinküste Protest
ተቃዉሞምስል AP

ባግቦ ሥልጣን አለቅም ማለታቸዉን የአፍሪቃ ሕብረት ቢቃወምም-አንድ የአፍሪቃ መሪ ባግቦ መወገድ አለባቸዉ ሲል ኦዲንጋ የመጀመሪያዉ ናቸዉ።አንድ የአፍሪቃ መሪ የሐይል እርምጃ መወሰድ የለበትም ሲል ደግሞ ዶ ሻንቶስ የመጀመሪያዉ ናቸዉ።

ነጋሽ መሐመድ
ሒሩት መለሰ